ህወሓት/ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ሲገባ አቶ ሌንጮ ለታ በፀሀፊነት ይመሩት የነበረው “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” በአጋርነት አብሮ መግባቱ ይታወቃል። ኦነግ በወቅቱ ይደረጉ በነበሩ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ የራሱ የማይናቅ ሚና እንደነበረውም ይነገራል። በተለይም በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው “የጎሳ ፌዴራሊም” ስርዓት እንዲዘረጋ ዋነኛ አቀንቃኝ እንደነበረም ይጠቀሳል።
ከ83 ጀምሮ ዛሬ “ኦሮሚያ ክልል”እየተባለ በሚጠራው በደኖ፣ ጋራሙለታና በተለያዩ ቦታዎች ለተፈፀመው የአማራ ተወላጆች እልቂት ኦነግን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሌላ ፓርቲ መስርተው ሰሞኑን ሀገር ቤት የገቡት አቶ ሌንጮ ለታ በደኖ የሚባል ቦታ ረግጠው እንደማያውቁና ማስረጃ ከቀረበባቸው ግን ማንኛውንም ህጋዊ ውሳኔ እንደሚቀበሉ ለቢቢሲ አማርኛ በሰጡት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ቃለ-መጠይቁ በጽሁፍ እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል፦
__________
”በደኖ የሚባል ቦታን ረግጨው አላውቅም” አቶ ሌንጮ ለታ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለአስርት ዓመታት የቆዩትና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር መስራች የሆኑት ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ጥያቄዎችን ወደፊት በማስቀደም ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠርም በሽግግር መንግሥት ምስረታው ተሳታፊ ነበሩ። ለረጅም ዓመታት በስደት የቆዩት አቶ ሌንጮ ከሦስት ዓመት በፊትም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘ ፖርቲንም አቋቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ አገር ቤት ባለው ፓለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ተመልሰዋል። በመጪው ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውና ከኦነግ ጋር ተያይዞ በሚቀርብባቸው አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እያደረጋችሁት ያለው ድርድር በምን መንገድ እየሄደ ነው?
አቶ ሌንጮ፡ ድርድር ልለው አልችልም። ውይይት ነው እያካሄድን ያለነው። አሁን እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ደካማና ጠንካራ ጎኑን እንዲሁም እኛ ልናበረክተው የምንችለው አስተዋፅኦ ምን ሊሆን ይችላል? በሚለው እየተወያየን ነው። ውይይቱ ጅማሮ ላይ ነው ሰፊ ጉዳዮችም አልተነሱም። እኛ ለብዙ ዓመታት ከዚህ አገር ተገልለን ባዕድ አገር ከመኖራችን አንፃር፤ እንዲሁም በስደት በነበርንበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ለውጥ በመከሰቱ ይህንን ለመረዳት እየሞከርን ነው። ያንን ሳንረዳ የሚረባ አስተዋፅኦ ልናበረክት አንችልም።
ከመንግሥት ጋር እያደረጋችሁት ያለው ውይይት በጥሩ መንገድ ከሄደ ምን ለማድረግ ታስባላችሁ?
አቶ ሌንጮ፡ እንደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ እንፈልጋለን። በአሰራሩ መሰረት መመዝገብ እንዲሁም ቢሮ መክፈት እንፈልጋለን። በእነዚህም ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደናል። የተፈጠረው ሁኔታ አበረታች ነው። ለመሰማራት ዝግጁ ነን።
ለአስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመሳተፍዎ አንፃር የእርስዎ አስተዋፅኦ ምንድን ነው?
አቶ ሌንጮ፡ይሄን ያህል አይደለም። ትልቁ አስተዋፅኦ የምለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን በማቋቋም ተሳትፌያለሁ። ደርጅቱም የኦሮሞን ሁኔታ በመለወጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። በኋላ ሁኔታዎች እንደፈለግነው አልሆኑም እንጂ አዲስ ምዕራፍ ከፍቶ ነበር። ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለመሸጋገር ምን ያስፈልጋል በሚለው ላይ እናተኩራለን። ስላለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንነታረካለን፤ ጥቅሙ የረባ አይደለም።
ወደኋላ ዞር ብለው ሲመለከቱ ባደረጉት ነገር የሚፀፅትዎት ነገር አለ?
አቶ ሌንጮ፡ከአፄ ኃይለሥላሴ ወደ ደርግ ሥርዓተ-መንግሥት በነበረው ሽግግር ወጣቶች ነበርን። እኔም ሆንኩ እኩዮቼ የፈፀምናቸው ስህተቶች ነበሩ። ከደርግ ወደ ኢህአዴግም ስንሸጋገር ብልህነትንና ጥበብን የተካነ እርምጃዎች መውሰድ ሲኖርብን ያው በስሜታዊነት ተነድነተን ያደረግናቸው ነገሮች አሉ።
ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢትዮጵያ በፖለቲካ ዕውቀት ደሀ መሆኗን ነው። እኔ ተማሪ በነበርኩበት ወቅትም ሆነ በደርግ ወቅት ፖለቲካ ወንጀል ነበር። ፖለቲካ ህጋዊ የሆነው ባለፉት 27 ዓመታት ነው። ይህም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ ባህል እንድናዳብር ይሄን ያህል የረዳ አይመስለኝም።
ይሄ እንዳይደገም ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል መገንባት ላይ መሰማራት አለብን። ብቻችንን የምንሰራው ሳይሆን ሌሎች ድርጅቶችንም ጨምሮ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሊሆን ይገባል። አምባገነንነት ፈፅሞ እንዳይከሰት መረባረብ ያስፈልጋል።
ኦነግ በደኖ ላይ ከተከሰተው ግድያ ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳል። ጭፍጨፋውን ፈፅሟል እያሉ የሚያነሱት አካላት አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ሌንጮ፡በኢትዮጵያ ታሪክ ከሚያሳዝነው አንደኛው ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚነሳ ነገርና የፍትህ ጥያቄን ለመመለስ ተጠንቶ የሚቀርብ ሁኔታ የለም። ፕሮፓጋንዳ ነው? ወይስ የፍትህ ጥያቄ የሚለውን መለየት አይቻልም።
በመጀመሪያ ነገር እኔ በደኖ የሚባል ቦታን ረግጨው አላውቅም። ቦታው ላይ የነበረውንም ሰራዊት አላዘዝኩም። ሁለተኛ ገለልተኛ በሆነ አካል የተጠና ጥናት የለም። እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን ዝም ብለን ከማራገብ ጥናት ተደርጎ እልባት ቢደረግላቸው ይሻላል። በእንዲህ አይነት ጉዳይ ከመወነጃጀል እንዳይደገም ማተኮሩ ነው የሚበጀው።
ተጠንቶ ጭፍጨፋው ከኦነግ ጋር የሚገናኝ ቢሆን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነዎት?
አቶ ሌንጮ፡በእኛ ላይ በትክክለኛ መንገድ ተጠንቶ ማስረጃ ከቀረበ ያን ጊዜ ከኦነግ መሪዎች አንዱ ስለነበርኩ ማንኛውንም ህጋዊ ውሳኔ እቀበላለሁ።
በባለፉት ሦስት ዓመታት እንዲሁም የባለፉትን ሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንዴት ገመገሙት?
አቶ ሌንጮ፡ በእድሜዬ ይህ ሦስተኛው እድል ነው። ከአፄ ኃይለሥላሴ ወደ ደርግ የነበረው የሽግግር ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ መልክ አልነበረውም። ለተፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ጅምር መጨናገፍ ብዙ ኃይሎች ያበረከቱት አስተዋፅኦ አለ።
ከደርግ ወደ ኢህአዴግ ሽግግር ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ በፅሁፍ ቃልኪዳን ገብተን ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች እንደፈለግነው ሳይሆን ቀረ። እውነተኛ ዴሞክራሲም እውን ሳይሆነ ተጨናገፈ። በዚህ ወቅት ስህተት መፈፀም የለብንም። ይህ የመጨረሻ ሊሆን ይችላል። ሁሉም የሚመለከታቸው ኃይሎች እንዲሁም ህብረተሰቡን ጨምሮ ተረባርበን ዴሞክራሲን እውን ልናደርግ ይገባል።
ባለፉት ዓመታት ብሔርተኝነት በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም በተለያዩ አካባቢዎች ላሉት መፈናቀሎች አስተዋፅኦ እንዳደረገ አስተያየታቸውን የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ ጥሩ ነው የሚሉ አሉ። ይህንን የብሔርተኝነት ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሌንጮ፡ ብሔርተኝነት ማንም ግለሰብ ከመሬት ተነስቶ ሊፈጥረው የሚችለው ነገር አይደለም። ብሔርተኝነት የሚነሳው በምክንያት ነው። ብሔርተኝነትን ከመቃወም በፊት ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በግሌ ብሔርተኝነትን በፍራቻ መነፅር የሚያዩ ሰዎች ችግራቸው ይገባኛል፤ ነገር ግን የነሱን ያህል አልሰጋም።
መረዳት ያለብን ኦሮሞም ሆነ፣ አፋርም፣ ጉራጌም ሆነ የተለያየ ብሔር ያለው ግለሰብ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን ከተቻለ፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የብሔርን ማንነት በሚያንፀባርቅ መልኩ ከተዋቀረ ሁሉም ሰው ኢትዮጵያን ሲያያት ራሱን ለማየት ከቻለ ኢትዮጵያ ኃያል ሀገር ትሆናለች። ብሔርተኝነት እንደማንኛውም ፖለቲካዊ አቋም አደጋ ሊኖረው ይችላል፤ ሊጠቅምም ይችላል።