ዶክተር አብይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ እንደሚሰበሰብ ተገለጸ።
36 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነገ ግንቦት 28 እና 29/2010 ዓ.ም ስብሰባውን እንደሚያካሂድ ተጠቁሟል። ስራ አስፈጸሚው በዚሁ ስብሰባው “የተለያዩ ስራ አፈጻጸሞችንና የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን” እቅድ የሁለት ዓመት ተኩል አፈፃፀምን በጥልቀት እንደሚገመግም ድርጅቱ በፌስ ቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡
ኢህአዴግ ዶ/ር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ ከመረጠ በኋላ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑም ታውቋል።
ነገ ማክሰኞና ዕሮብ የሚካሄደው የአገዛዙ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ “መደበኛ ስብሰባ” እንደሆነ ቢገለፅም በዶክተር አብይ የአመራር አሰጣጥ ያልተደሰተው የህወሓት ቡድን “ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ስብሰባ” እንዲጠራ ሲወተዉቱ መሰንበቱን ውስጥ አዋቂዎች ሲገልፁ ቆይተዋል።