በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ፤ ከሰሞኑ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ያደረጉት ቃለ- ምልልስ እሰጥ አገባ ቀስቅሷል፡፡
በኦሮምኛ ከተደረገው ቃለ-ምልልስ የተወሰደ ነው ያሉትን ንግግር ወደ አማርኛ በመመለስ የተከራከሩ ወገኖች አቶ በቀለ እሳቸው ከወከሉት ህዝብ ውጪ ያለውን አካል ‹‹ባዕዳን›› በማለት ጠርተዋል፣ ‹መቀመጫቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ የፖለቲካ ቡድን አባላት ከእስር በመለቀቃቸው መከፋታቸውን አሳውቀዋል!› በሚል ይከሷቸዋል፡፡ አቶ በቀለ ግን፤ ‹‹የተናገርኩት ከአውድ ውጪ ተወስዶብኛል…ይሄም የሆነው ሆን ተብሎ ነው›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ቢቢሲ ለስራ ወዳቀኑበት ሀገረ አሜሪካ በመደወል አነጋግሯቸዋል፡፡ የሙሉ ቃለ-ምልልሱን የጽሁፍ ቅጂ እነሆ፡፡
ቢቢሲ፡-በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ እርስዎ አሉት ተብሎ የሰፈረው ‹የአሮሞ ልጆች በከፈሉት መስዋዕትነት የተጠቀሙት ባዕዳን ናቸው!› የሚል ነው፡፡በርግጥ በወቅቱ ሊያስተላልፉት የሞከሩት መልዕክት ምን ነበር?
በእርግጥ ከአሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር አንድ ቃለ-ምልልስ ሰጥቼ ነበር፡፡ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ባሉ ጉዳዮች ላይ አስተያየት እንድሰጥ ተጠይቄ፣ ስለ እስረኞች አፈታት እና ስለ አንዳንድ ነገሮች በሚነሳበት ወቅት አሁን ባለው መንግሥት ወይንም አስተዳዳር በቂ የሆነ አመኔታ እንደሌለን ገልጫለሁ። አስተዳደሩ ወጥነት ያለው ስራ እየተከተለ አይደለም።
ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰዎችን፣ እና የፖለቲካ ቡድኖችን እየለየ ፍትሃዊነት በሌለው መልኩ አንዳንድ እርምጃዎችን እየተገበረ እንደሆነ ተናግሬያለሁ። እንደሚታወቀው ከአራት ዓመታት ወዲህ ብዙ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ ውስጥ ተካሄደዋል። እንቅስቃሴው በአብዛኛው የተከናወነው በአሮሚያ ክልል ውስጥ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ነው። ብዙ ህይወት እና ንብረት የጠፋው፣ ሀገሪቱንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተው ሁኔታ በዚሁ ስፍራ የተከናወነ እንደሆነ ግልፅ ነው። ለዚህም ከፍተኛውን መሰዋዕትነት የከፈሉት፤ ለእስር እና ለቤተሰብ መበተን የተዳረጉት፣ አካላቸው የተጎዳው በአብዛኛው የኦሮሚያ ወጣቶች እንደነበሩ ማንም የሚክድ አይመስለኝም።
በቅርቡ እንኳ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት (ለማ መገርሳ) 40ሺ ሰዎች ከእስር መለቀቃቸውን ተናግረዋል። አሁንም እስር ቤት ውስጥ ያሉ መኖራቸውን ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ ወንጀል ተከሰው የነበሩ ሰዎች፣ በከፍተኛ ሃላፊነት የነበሩ ግለሰቦች በሚፈቱበት ወቅት ሌሎቹ እየተለዩ መቅረታቸው ከብሄር ውጪ ሌላ ዓይነት ‹‹ኤክስፕላኔሽን›› ወይንም ማስረጃ ሊገኝለት ባለመቻሉ፣ እኛ የሞትንለት (እኛ በምንልበት ወቅት የአሮሞ ወጣቶች ማለቴ ነው) በከፍለነው ዋጋ ተጠቃሚ አልሆንም ብያለሁ። ለምን እከሌ ተፈታ? እከሌ መፈታት አልነበረበትም? ማለቴ ሳይሆን፣ ተመሳሳይነት ወጥነት ያለው ስራ አልተሰራም፣ ትናንት ስንታገለው የነበረው ኢፍትሃዊነት አሁንም አለ፣ ዛሬም በዐይናችን እያነው ነው ለማለት ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ (ወደ ኢትዮጵያ) ከባዕድ ሀገር ታፍነው እና ተጠልፈው የመጡ አሉ፡፡ አንዱን ፈትቶ አንዱን ማስቀረት አለ። ከዚህ በላይ ኢፍትሃዊነት ለኛ የለም። ኢፍትሃዊነቱም በግልፅ በዘር መስመር የተፈጸመ ነው ብለን ስላመንን ወይንም ብዬ ስላመንኩ፣ የዚህ ስርዓት አካሄድ ፍትሃዊነት ያለው አይደለም፤ ትናንት ስንዋጋው የነበረውን ነገር ዛሬም መልሰው እየደገሙት ነው፣ መስተካከል አለበት ለማለት ያክል ነው እንጂ ሰዎች ለምን ተፈቱ ? እከሌ ለምን ተፈታ? የሚል አስተሳሰብ አልነበረም። ሁሉም ሰዎች ቢፈቱልን ደስ ይለናል፤ ከሰዎች መታሰር ጥቅም የሚያገኝ ያለ አይመስለኝም።
‹ሌሎች› ብዬ ያስቀመጥኩትን ‹ባዕዳን› በሚለው፣ በእንግሊዝኛው ደግሞ እጅግ በጣም አርቀው ‹ኤሊየን› በሚለው ተርጉመው ለዚህ ሁሉ ውዝግብ ምክንያት ለመሆን ችለዋል። ‹ኤሊየን› የሚለው ቃል ለማናችንም በጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ቃል ነው ተብሎ የሚታሰብ አይደለም። እጅግ በጣም አርቀው እና ጸያፍ በሆነ መልኩ ለኢትዮጵያዊ የማይገባውን ቦታና ስሜት ሰጥተው ነው የተረጎሙት፣ ይሄም የተደረገው ባለማወቅ ነው ብዬ አልገምትም፡፡
እኔ ‹ሌሎች› የምለው እኛ ከተደራጀንበት የፖለቲካ ፓርቲ ውጪ ያሉ ድርጅቶችን ወይንም ፓርቲዎችን ማለታችን እንጂ እኛ ኢትዮጵያዊያንን እንደ ባዕድ እንደመጤ እየቆጠርን አይደለም፡፡ በሀገራችን ማናችንም ባዕድ ልሆን አንችልም፣ በሰው ሀገርም በሌላ ሀገር መጤ ተብለን መኖር አንፈልግም፡፡
ቢቢሲ፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እንደሚታገል ሰው፤ እኛ እና እነሱ ብሎ መክፈል በራሱ አያስቸግርም ወይ? ይሄ አስተሳሳብ በራሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ የሚፈለገውን ዲሞክራሲ እና እኩልነት የሚያስተጓጉል እንቅፋት አይሆንም ወይ?
አንዳንድ እውነታዎችን መቀበል የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ፓርቲዎች በምን ሁኔታ ነው የተደራጁት ሲባል፣ ቀድሞ የነበረው ስርዓት የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ ባለመሆኑ አሁን ባሉበት መሰረት መደራጀት ግድ ሆነ፡፡ ወደፊት እነዚህ ነገሮች እየታሹ እና መስመር እየያዙ ሲመጡ አሁን በዚህ መልኩ የተደራጁ ፓርቲዎች ከስመው ወደ አንድ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ወይንም ሁሉንም ብሄሮች ወደ ሚያቅፍ ፓርቲ ይለወጣሉ በሚል ተስፋ ቅንጅት ፈጥረን ብዙ ስራ እየሰራን ነበር፤ አሁንም በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ኢፍትሃዊነቱ የሚቀጥል ከሆነ አንድ ፓርቲ ቆሜለታለሁ የሚለውን አንድ ህዝብ ይወክላል፡፡
ይሄ ማለት ግን ሌላውን ህዝብ አይወድም፣ ይጠላል፤ ባላንጣው ነው ማለት ሳይሆን በራሱ በኩል ያለውን ጉድለት ያካክሳል፣ በራሱ በኩል ያለውን ኢፍትሃዊነት ታግሎ በሌላ በኩል ካለው ተባብሮ እና አስወግዶ አንድ የጋራ ሀገር ይመሰርታል ነው እንጂ፤ እንደ ባለጋራ እየተያዩ የሚሄዱ ጣውንቶች የመሰለ ግንኙነት ይመሰርታል አይደለም፡፡
ለምሳሌ እኔ በመምህርነቴ የመምህራን ማህበር አባል ብሆን የወዝ አደሮችን ወይንም የሃኪሞች ማህበርን ለማጠፋት ወይንም ጥቃት ለማድረስ አይደለም፡፡ ነገር ግን እዚህ ባለው ነገር ላይ በአንድ በኩል ያለውን ኢፍትሃዊነት አንዱ ከሌላው በተሻለ ያለውን ተሰሚነት ተጠቅሞ ማስወገድ ከቻለ ሌላኛውም በተመሳሳይ ከዚያኛው ጎን ማስወገድ ከቻለ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው ኢፍትሃዊነት ይወገዳል፣ ወንድማማችነት ይመጣል፡፡ ሁሉም አካባቢውን በደንብ ያውቃል፣ የተሻለ ትኩረት ይሰጠዋል፣ ይከነክነዋል በሚል እንጂ ባዕዳን የሚኖሩበት፣ ግንኙነት የሌላቸው ሁልጊዜ ለመጋጨት የሚፈልጉ ቡድኖች የሰበሰበ ሀገር አድርገው ማየት በጣም ተገቢ አይደለም፡፡
እኛ ከዚህ በፊትም ስንሰራበት የነበረው መንፈስ ይሄው ነው፡፡ ዛሬ ማንም በምንም መልክ ሊያበላሽ ቢሞክርም፣ ለወደፊቱም ለመስራት የምንፈልገው እንደዚሁ ነው፡፡ ‹እኛ› ብለን የምንጠራው የአሮሞን ፍላጎት እና አቋም ለማስከበር የተደራጀን ማለቴ ነው፡፡ ‹ሌሎች› በምልበት ወቅት በድርጅት መልክ ተደራጅተው የሌላውን መብት ሊያስከብሩ የሚፈልጉ ትግል ላይ ያሉትን ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ‹እኛ› እና ‹እነሱ› የሚለው በዚህ መሰረት የተወሰደ እንጂ በጠላትነት የሚተያዩ ድርጅቶች ባዕድ እና የሀገር ሰው ለማለት ተፈልጎ አይደለም፡፡
‹እኛ› እና ‹እናንተ› ማለት የተለመደ ማንም ሰው ሊያስወግደው ቢፈልግም ሊወገድ የማይችል ዕውነታ ነው፡፡ ይሄ አንዱን ቡድን ከአንዱ ከመለየት አንጻር ታስቦ የተደረገ እንጂ ከጀርባው የተለየ ነገር እንደሌለው ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ በበኩሌ አሁን የሆነው በግለሰብ ደረጃ የተደረገ ዘመቻ ሆኖ ቢቀር ደስ ይለኛል፡፡ በሰዎች፣ በማህበረሰብ እና በቡድኖች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት አሳዛኝ ነው፡፡ ለዚያ ምንም መንገድ መክፈት አያስፈልግም፣ እኔ በበኩሌ ከአውድ ውጪ የተወሰደውን ትርጓሜ በዚህ መልክ እንዲስተካከል እና ህዝቡ እንዲያውቀው እፈልጋለሁ፡፡
ምንጭ~ቢቢሲ አማርኛ