/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (MeTEC) ከ9 ቢሊዮን በላይ ብር ማባከኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።የምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን ያለፉት ዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ዛሬ ሲገመግም ከፍተኛ ገንዘብ እንደባከ ማረጋጉን አስታውቋል።ተቋሙ የገበያ ጥናት ሳያደርግ ከ9 ቢሊዮን በላይ ብር የሚገመቱ የተለያዩ ማሽኖች መለዋወጫ እቃዎችና መሳሪያዎችን በማምረት አከማችቶ እንዲቀመጡ ማድረጉን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ሜቴክ(MeTEC) እየተባለ ባጭሩ በእግሊዝኛ የሚጠረው የመከላከያ ተቋም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊደግፍ በሚችል መልኩና በጥናት ላይ ተመስርቶ እየሰራ አለመሆኑን አባላቱ በግምገማው ላይ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶን ለማጠናቀቅ ረጅም ጊዜ እየወሰደበት እንደሚገኝም ተገልጿል።
ሜቴክ በየጊዜው ለምክር ቤቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ወጥነት የጎደላቸውና የሚዋዥቁ ናቸው ተብሏል።ለአብነትም የያዮ ማዳበሪያ ፕሮጀክት አፈጻጸም ሪፖርት ተዓማኒነት የጎደለው ሲሆን የኦሞ ከራዝ ቁጥር 1 እና የበለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ከ90 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቁ ከአንድ ዓመት በፊት የተገለጸ ቢሆንም በ2010 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግን ከዓምናው ያነሰ ሆኖ ሪፖርት መቅረቡን ተጠቅሷል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊደግፍ በሚችል መልኩና በጥናት ላይ ተመስርቶ ባለመስራቱ 4 ነጥ4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የእርሻ መሳሪያዎችና የመለዋወጫ እቃዎች በአዳማ የእርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ ክምችት ውስጥ እንዲቀመጥ ማድረጉ ተገልጿል።በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክምችት ክፍል ደግሞ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ መለዋወጫዎች ያለስራ በመቀመጣቸው ለብክነት እየተዳረጉ መሆኑ ተጠቅሷል።
ተቋሙን ላለፉት በርካታ ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩት የህወሓቱ ብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የህዝብና የሀገርን ሀብት ሲዘርፉ ቆይተው በህግ ሳይጠየቁ የስልጣን መልቀቂያ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅርበው ተቀባይነት በማግኘቱ በሌላ ሰው መተካታቸው ይታወሳል።