7ኛው ንጉስ ሆይ… 4ኛውን መንግስት ይፍቱልን! /ዳዊት ከበደ...

7ኛው ንጉስ ሆይ… 4ኛውን መንግስት ይፍቱልን! /ዳዊት ከበደ ወየሳ/

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከስልጣን የወረዱት በ1967 ዓ.ም. ነው። በዚያኑ አመት የክረምት ወራት በእስር ላይ ሳሉ የሞት ጽዋን ተጎነጩ። ህዝቡም በሹክሹክታ ዜና እረፍታቸውን ከማውራት ውጪ፤ ስለሞትና አሟታቸው ብዙም ሳይባል ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ተፋፋመ። እናም በዚህን ጊዜ ወንድ ልጅ ተጸነሰ፤ ተወለደ፤ ስሙንም አብይ አሉት። ሰባተኛው ንጉሥ እንደሚሆን ለእናቱ በህልም  ወይም  በራዕይ ተነገራቸው። በ’ርግጥም ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እረፍት በኋላ፤ ጄነራል አምዶም፣ ብ/ጄነራል ተፈሪ በንቲ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን፣ አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ… በአጠቃላይ ስድስት የአገር መሪዎች ስልጣነ ወንበሩን ያዙ። በትንቢቱ መሰረት ሰባተኛው ንጉሥ፤ ጦር ሳያዘምት፣ ዘውድ ሳይጭን በትረ ስልጣኑን ተቆጣጠረ። “ኢትዮጵያን በጠመንጃ ሳይሆን በበትር የሚገዛ ሰው ይመጣል። በዚያን ግዜ ሰላም ይሰፍናል። ህዝቡን ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የነበሩ መሪዎችም እንደጉም ደመና ተነው ይጠፋሉ። እንደጎርፍ ውሃም ተጠራርገው ይሄዳሉ…” እያለ ይቀጥላል – ትንቢቱ። በዚህ ትንቢት ላይ የሼኽ ሁሴን ጅብሪልን ትንቢቶች ከጨመርን፤ “አጃኢብ!” እያሰኘ የተባለው ቀን መድረሱን ያረጋግጥልናል። እኛ ግን የትንቢቱን ነገር ወደጎን አቆይተን፤ ሰባተኛው ንጉሥ… አራተኛውን መንግስት እንዲፈቱልን እንጠይቃለን።

 በአንድ አገር ውስጥ ሶስት የመንግስት ምሰሶዎች አሉ። እነሱም ህግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ ናቸው። አራተኛው መንግድት ግን ነጻው ፕሬስ ወይም ሚዲያ ነው። ይህ እንደአራተኛ መንግስት የሚታይ አካል በአንድ አገር ውስጥ ከሌለ፤ የሃይል ሚዛኑን የሚፈትሽ እና የሚቆጣጠር (Check and Balance) የሚያደርግ አካል አይኖረንም። ይህ ማለት ደግሞ የመንግስት ሹመኞች ህዝቡን እየበደሉ ሲያስለቅሱት፤ ቢያንስ ህዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት በደለኞችን የሚያጋልጥበት መድረክ እንዳይኖረው ማድረግ ማለት ነው።

  በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከፍተኛ የመንግስት ሹመኞች ማለት የአንድ ፓርቲ ውክልና ያላቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የዳበረ ጡንቻ ያላቸውና ከነሱ የፖለቲካ ድርጅት ውጪ የሚገኝን ዜጋ ባገኙት አጋጣሚ የሚጨፈልቁ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠውልናል። ህዝቡ በደል ሲደርስበት ድምጹን የሚያሰማበት ነጻ መድረክ እስከሌለው ድረስ፤ ህዝብ እና መንግስት፤ እየተጣሉና እየተጣጣሉ… በጨለማ ውስጥ የ’ውር ድንብር ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ይህ እንዳይሆን አራተኛው መንግስት የህግ ከለላ ተደርጎለት፤  በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ዳግመኛ ሊወለድ ይገባዋል።

 እንደእውነቱ ከሆነ… በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻው-ፕሬስ እንዳያንሰራራ የሚፈልጉት፤ የግል እና የወል ጥቅማቸው እንዳይነካ የራሳቸውን አጥር የሚያጥሩ ሰዎች ናቸው። በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሙግት የገጠሙ የመኖራቸውን ያህል፤ ይህንን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ መብት ለመገደብ እና ለማፈን ብዙ የደከሙ እና የማሰኑ የስልጣን ጥመኞችና ጥቅመኞች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። አባባሉን ለማጠናከር ያህል… በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር፤ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች… የእስር እና የስደት ብቻ ሳይሆን የህይወት ዋጋ ጭምር ሲከፍሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ነጻነት ለማፈን ህግና ደንብ አውጥተው ነጻውን ጋዜጠኛ ለማሰር እና ለማንገላታት ተግተው የሚሰሩ፤ እጃቸውን በግፍ የታጠቡ ሰዎች መኖራቸውን ልብ ይበሉ።

 በአንድ ወቅት የአንድ የኢህአዴግን ከፍተኛ ባለስልጣን ታናሽ ወንድም የሆኑት፤ አቶ አሰፋ አብርሃ በመንግስት ላይ ኪሳራ የሚያስከትል ተግባር ለመፈጸማቸው መረጃ አስደግፈን በጋዜጣችን ላይ ትንታኔ ሰጠንበት። በሳምንቱ “የክቡር ሚንስትሩን ክብር እና ዝና ነክታችኋል” ተብለን ለእስር ተዳረግን። እኚህ ከፍተኛ ባለስልጣን የመንግስት ንብረት የሆነው ኮካኮላ ካምፓኒ ወደግል ንብረትነት ሲሸጋገር፤ ወዳጅ እና ዘመዶቻቸውን በእንዴት አይነት ሁኔታ  ክፍያ እንዲደረግላቸው በማዘዝ የፈጸሙትን ጥፋት በዝርዝርነበር ያቀረብነው። አቃቤ ህጉ… መረጃችንን መሰረት አድርጎ በሚንስትሩ ላይ ክስ መመስረት ሲገባው፤ በተቃራኒ “የክቡር ሚንስትሩን ስም እና ዝና የሚያጎድፍ ተግባር ፈጽማችኋል።” ተብለን ለእስር ተዳረግን። (*ከአገር ከወጣን በኋላ… ኢህአዴግና ሚንስትሩ ሲጣሉ እኛ ስንጽፈው ውሸት በተባለው ዜና ክስ ተመስርቶባቸው፤ መታሰራቸውን እናስታውሳለን)

 በዚህ ጉዳይ ታስረን በነበረበት ወቅት ግን ለእድሜ ልክ የሚበቃ ትምህርት የምናገኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ከእስር ቤቱ ሊቅ ጋር ተገናኘን። የእስር ቤቱ ሊቅ ግዜውን የሚያጠፋው እስረኞችን በማማከር፤ ብዙዎች እንዲፈቱ በመርዳት ነበር። በመቆየት ብዛት ሊቁ በምን ምክንያት እንደታሰረ የሚያወጋ እስረኛ ጠፋ። እሱ ግን የህግ ምክር አገልግሎት ስራውን ቀጠለበት። ሊቁ በእስረኛው ዘንድ ተወዳጅ ነው። እስረኛው ይወደዋል፤ ያከብረዋል። አንድ ምሽት ላይ ከሊቁ ጋር የምናወራበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በጨለማ ውስጥ… ጥግ ጥግ ይዘን ቁጭ ብለን ሳለ፤ ሊቁ እኛ ወደተቀመጥንበት ጥግ መጣ።

 “ይሄን ጨለማ ታየዋለህ?” አለኝ ሊቁ።

“ጨለማ ምኑ ይታያል?” መልሼ ጠየኩት።

“ግዴለም የምጠይቅህን መልስ!” አለኝና “በጨለማ ውስጥ ጨለማን ታያለህ?” ሲል መልሶ ጠየቀኝ።

 “አላየውም!” አልኩት።

“አየህ ይህ ጨለማ የአገራችን ምሳሌ ነው።” የሚል ትንታኔ ካደረገልኝ በኋላ፤ “አይኖችህን ጨፍን!” የሚል ትእዛዝ አስከተለ።

“በጨለማ ውስጥ አይን መጨፈን ምን አመጣው?” ብዬ መከራከር ልጀምር ስል፤ በጭላንጭል ውስጥ እያዩ ሁኔታውን እንደድራማ የሚከታተሉ እስረኞች፤ የሊቁ መጨረሻ ስላጓጓቸው “የሚልህን ለምን አታደርግም?” ማለት ጀመሩና፤ በጨለማው ውስጥ አይኔን ጨፈንኩ።

“ሁለት እጆችህን ዘርጋ” አለኝና ሁለት እጆቼን ዘረጋሁለት።

ሊቁ ድምጹን ከፍ አድርጎ ንግግሩን ቀጠለ። “በአንደኛው እጅህ ላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አስቀምጥልሃለሁ።” አለኝ።

“እሺ” አልኩት።

“ሁለተኛው እጅህ ላይ ሃሳብህን በነጻነት ለመግለጽ የተጠቀምክባቸውን የፕሬስ ውጤቶች አስቀምጥልሃለሁ። እነማን ነበሩ?” አለኝ።

እኔም ቀጠልኩ… “ሩህ፣ ፈለግ፣ ሞገድ፣ ፊያሜታ…” እያልኩ ስዘረዝር ሁሉንም በየተራ በሌላኛው እጄ ላይ አስቀመጠልኝ።

በመጨረሻም “የዘረጋከውን እጅ መልሰህ ጨብጥ” አለኝ ሊቁ።

ያለኝን አደረኩ። ከዚያም ጠየቀኝ። “በእጅህ ውስጥ ምንድን አለ?” ሲለኝ፤ በሃሳብ ያስቀመጥነውን የፕሬስ ነጻነትና የፕሬስ ውጤቶች ዘረዘርኩለት።

“አሁን የጨበጥከውን እጅ በየተራ ክፈት!” አለኝ። እኔም ይህንኑ ፈጸምኩ።

“አይኖችህንም ግለጥ!” አለኝ።

በጨለማ ውስጥ የተከደኑትን አይኖቼን ገለጥኳቸው።

“እጅህ ላይ ምን ይታይሃል?” አለኝ።

“ምንም!” አልኩት።

ሊቁ ድምጹን ዘለግ አድርጎ፤ ሌሎች እስረኞችም እንዲሰሙት ዲስኩር ማድረግ ጀመረ። “ጎበዝ ኢህአዴግ ማለት ይሄ ነው።” ብሎ ገና ሲጀምር፤ ነገሩ የገባቸው አንዳንድ እስረኞች መሳቅ ጀመሩ። ሊቁ ንግግሩን ቀጠለ። “ኢህአዴግ ባዶ ተስፋ እየሰጠ ያሞኘናል። አገር በጨለማ ውስጥ መሆኗ ሳያንስ፤ ‘አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛቹህ!’ ይለናል። ሊቁ ይሄን እያለ… ኢህአዴግ ለይስሙላ ሰጥቶ የነሳንን ነገሮች እያነሳና እየጣለ፤ እንቅልፍ እስከሚጥለን ድረስ ንግግሩን ቀጠለ።

 ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከእስር ተፈታን። ሊቁን እየተመላለስን ስንጠይቀው ቆየንና በመጨረሻ “እስረኛ ታሳምጻለህ” ተብሎ መወሰዱን እንጂ፤ የት እንደወሰዱት እንኳን ሳይታወቅ፤ ፈልገን አፈላልገን የሊቁ ደብዛ አጣነው። ኢህአዴግ ማለት ይሄ ነው – በጨለማ ውስጥ እያደባ፤ ህዝብን የሚያደማ ድርጅት ለመሆኑ የብዙ ሺህ ሰዎችን ታሪክ መዘርዘር የለብንም። የሆኖ ሆኖ ሊቁ ጠፋ… የሊቁ ምሳሌያዊ ንግግሮች ግን ዛሬም ከህሊናችን አልጠፉም፤ ባህር ማዶ ድረስ አብረውን ዘልቀዋል።

 እርግጥ ነው። ከድሮ ጀምሮ በተደጋጋሚ የምንለው ነገር አለ። “መንግስት መብት ይሰጣል እንጂ አያስከብርም። መብትን ማስከበር የያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነትና ግዴታ ነው።” ብዙዎች መብታችንን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ዜጋ መብት በማስከበር ሂደት ውስጥ ታስረን ተፈተናል፤ ወድቀን ተነስተናል።  ሆኖም ታስረን በተፈታን ቁጥር መብታችን እየተሸራረፈ፤ ወድቀን በተነሳን መጠን አቅማችን እየቀነሰ መምጣቱ አልቀረም። እውነት እውነት እንላችኋለን… ነጻው-ፕሬስ ስንሰደድ አብሮን ተሰደደ እንጂ፤ ስንፈታ አብሮን አልተፈታም።

 ልብ በሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን የመግለጽ መብት ተረጋግጦ፤ የፕሬስ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ፤ ህግ ሆኖ የወጣው በሽግግሩ መንግስት ዘመን፤ በአምስተኛው ንጉሥ ስም እና ፊርማ ነው። ይህን የፕሬስ አዋጅ ተከትለን፤ ብዙዎች የወጣትነት እድሜያችንን ፈጀን። ይህ የፕሬስ ነጻነት ከእጃችን እንዳይወጣ፤ ለመታፈን እና ለመታሰር እራሳችንን አዘጋጀን። በመቶዎች የምንቆጠር የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ በእሳት ተፈትነን፤ በወላፈኑ ተለብልበን… ከመቶ ሃምሳ በላይ የምንሆነው ከመሞት መሰንበትን፤ ከመታሰር መሰደድን መርጠን፤ ከአገር እንደወጣን… ወጥተን ቀረን።

 ገና ከጅምሩ… የፕሬስ አዋጁ በሽግግር መንግስቱ ዘመን መሸርሸር ጀመረ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የኤርትራን መገንጠል በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ፤ መንገድ ላይ የተቀበላቸው ቆመጥ ሳይሆን የወያኔ ሳንጃና ጥይት ነበር። ብዙዎች ተደብድበው ለአካለ ስንኩልነት ተዳርገው፤ የቀሩት ሰንዳፋ መታሰራቸውን እናስታውሳለን። ከሰልፈኞች

LEAVE A REPLY