እንደመር እያሉ ግዛት መቀነስ /ቴዎድሮስ ጸጋዬ/

እንደመር እያሉ ግዛት መቀነስ /ቴዎድሮስ ጸጋዬ/

ዛሬም አገር ተክዳለች፡፡ ኢትዮጵያችን የበደለችው ምንድነው?

 ይኸውና በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ፣ መሬታችንን ለወረረው፣ በጠብ አጫሪነቱ ሳብያ ለብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፍ፣ አካል መጉደልና መፈናቀል ምክንያት ለሆነው የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያውያንን ለመጨፍጨፉ ባድመን፣ ዛላምበሳንና ጾረናን በሽልማት መልክ አቅርቦለታል፡፡

 ይህ ነው “ኢትዮጵያ እኔ ነኝ፣ አንቺ ነሽ…” ማለት፡፡ መሬቱ አይደለም እንደማለት መሆኑ ነው እንግዲህ፡

 መመርመር ያለበት ኢህአዲግ ኢትዮጵያን በዚህ ልክ ለምን ይጠላል የሚለው ነው፡፡ መጠየቅ ያለበት ኢህአዲግ፣ (አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ) የኢትዮጵያን መሬት ሸጦ፣ ብሄራዊ ጥቅሟን ቸርችሮ የሚበቃው መቼ ነው; የእነኝያ ልጆቻቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች እንባ ከቁብ የሚጣፈው፣ ከአገሩ መሬት አንድ ጋት ሲቆረስ ከገላው የተቆረሰ ያህል የሚያምመው ኢትዮጵያዊ መሪ የምናገኘው መቼ ነው; መሬታችን ከየአቅጣጫው መቆረሱ የሚቆመው መቼ ነው? በአንድ በኩል በተገኘ መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያ እያሉ መጮህ፣ ከዝያ ግን በእርግጥ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የመቆም ሰአት ሲመጣ ለውርደቷ ድምጽ መስጠት ምን ይሉት ፈሊጥ እንደሆነ አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያን ግዛት ሀላፊነት በጎደለው መልኩ በመቸርቸር ወይም ከዚህ ድርጊት ጋር በመተባበር የሚገለጥ የሀገር ፍቅር አይገባኝም፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ… እያሉ መፈክር ማሰማት፣ ከዝያም ሀገሪቱ እንድታፍር የሚያደርግ ተግባር መፈጸም ግልብነት እንጂ ከቶ ብልህነት ሊሆን አይችልም፡፡ እንደመር እያሉ ግዛት መቀነስ አይዋጥልኝም፡፡

 1 ስርአቱ ኤርትራን ሲያስገነጥል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ሳያስጠብቅና ለማስጠበቅ ሳይጨነቅ የአገሪቱን ወደቦች በጓሮ በር ሸኘ፡፡

 2 የሻቢያና የህወሀት መርህ አልባ ግንኙነት ደፍርሶ ሻቢያን ጥጋብ ሲሰማው አገራችንን በወረረ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ደም ከፍለው ሕይወት ገብረው ምድራችንን ቢዋጁም በኢትዮጵያ ስልጣን የያዘው የኤርትራ መንግስት እራስን የመከላከል ጦርነቱ ከፍጻሜ እንዳይደርስ አጨነገፈ፡፡

3 ብዙ ሺህ ልጆቻችንን ሰውተን ያገኘነውን ድል አልጀርስ ላይ ሄዶ፣ የሰማእታቱን ደም ደመከልብ አድርጎ፣ በህግ ፊት ዋጋ በሌላቸው ውሎችና የህግ እሳቤዎች ምርኩዝነት እንደተሸነፈ ሁሉ ኮሳሳ ውል ይዞ መጣ፡፡ ይግረማችሁና የድንበር ኮሚሽኑ ከአገዛዙ ተሽሎ ጾረና ለኢትዮጵያ ትገባለች ቢል፣ አገዛዙ “ወዴት ወዴት፣ ጾረናማ የኤርትራ ነው” በማለት ስለኤርትራ ሞገተ፡፡ ብይኑ ሲሰጥም አሸንፍያለሁ ሲልም ህዝቡን ሳያፍር ቀጠፈ፡፡

4 ይህም ሳያንስ፤ አንዳችም አስገዳጅና አጣዳፊ ሁናቴ በሌለበት፣ የአልጀርሱ ስምምነት በተደጋጋሚ በሻቢያ ተጥሶ ፈራሽ ሊሆን እድል ባለበት ህዝብ ሳይማከር፣ አገር ሳይጠየቅ “እባካችሁ መሬታችንን ውሰዱ” ሲል ምህላውን አቅርቧል፡፡

ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል፣ ለወገኖቹ ህይወት ተገቢ ክብርና ክብደት የሚሰጥ፣ የሀገር ውርደትና ጥቃት የሚገድደውና ጤና ያለው ህሊና ባለቤት የሆነ ሁሉ በዚህ ልቡ እንደሚሰበር አልጠራጠርም፡፡

እናንት በዚህ ውሳኔ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳታፍሩ ለኖቤል የሰላም ሽልማት የምታጩ፣ እናንት ስለሀገራቸው ድንበርና ሉአላዊነት ለተሰዉ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ህይወት ግድ የሌላችሁ፣ እናንት ይህንን የአገዛዙን ውሳኔ እንደመልካም ዜና የምትቀሰቅሱና የምታራግቡ፣ የነኝያ ሰማእታት አጥንት እሾህ ሆኖ ገላችሁንና ህሊናችሁን ይውጋው፡፡

ኢትዮጵያ እንደሁ ቀና ማለቷ አይቀርም፡፡

 

LEAVE A REPLY