/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በመቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ 2038 የሚመዝን የሜርኩሪ ማዕድን መያዙ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን እንደተናገሩት ሜርኩሪው በህገወጥ መንገድ በአውሮፕላን ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ሊጓጓዝ ሲል በተደረገ ፍተሻ መያዙን አስታውቀዋል።
የተያዘው ሜርኩሪ የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር እንዲረከብ መደረጉንም የጉምሩክ ባለስልጣን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡ ትክክለኛ ሜርኩሪ መሆኑንም በጂኦሎጂካል ሰርቬይና በማዕድን የምርምር ባለሙያዎች በምርመራ መረጋገጡ ተገልጿል። የሜርኩሪው ትከክለኝነት ስለተረጋገጠ ይዞ የተገኘው ግለሰብም በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ በድንበር አካባቢ የሚወጡ ገንዘቦች (ዶላር)፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ሌሎች የሀገሪቱ ሀብቶች እየሸሹ እንደሚገኙ በተለያየ ጊዜ ሲገለፅ ቆይቷል።