ከኦሮሚያ ክልል የአማራ ተፈናቃዮች ገዳይ እያነጋገረ ነው

ከኦሮሚያ ክልል የአማራ ተፈናቃዮች ገዳይ እያነጋገረ ነው

“ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀለ የአማራ ተወላጅ የለም” የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በተለይም ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በፓርቲያቸው ከተሾሙ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የአማራ ተወላጆች ከበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ሲፈናቀሉ ቆይተዋል። በምዕራብ ሸዋ፣ በቡኖ በደሌ፣ በጅማ፣ በቄለም ወለጋ  ዞኖች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ከመኖሪያ ቀያቸው በመፈናቀል በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ቆቦ፣ ቡሬና በሌሎች ከተሞችም እንደሚገኙ በድምፅና በምስል የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ባለፈው ሳምንትም በቄለም ወለጋ ዞን ሰዮ ወረዳ የአካባቢው ወጣቶች ከአስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት የአማራ ተወላጆችን ቤት ለቤት እየዞሩ እየደበደቡና ንብረቶቻቸውን እየቀሙ “ሀገራችን” ልቀቁ ተብለው እንደተባረሩ አንድ ተፈናቃይ  መረጃውን በስልክ አድርሶናል።በሰዮ ወረዳ አስተዳዳሪዎች በርካታ በደል እንደደረሰባቸውና በዚህ ዓመት ብቻ ከ20 በላይ አማራዎች በዘራቸው ምንኒያት ብቻ  እንደተገደሉም የሰበሰብናቸው የተለያዩ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ስለሚፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የፌዴራል መንግስቱ እስካሁን ያለው ነገር ባይኖርም የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ሀላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ትናንት በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰራጩት መልዕክት የክልሉ መንግስትም ሆነ ህዝብ ማፈናቀል ባህሉ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የአማራ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል በሰላም እየኖሩ ነው ብለዋል። ተፈናቀሉ ተብሎ የሚወራውም ወሸት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ሀላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋም ከ15 ቀናት በፊት ባሰራጩት መልዕክት በምዕራብ ሸዋ ዞን የተፈናቀሉት ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት የያዙ አርሶ አደሮች መሬት በመነጠቃቸው ነው ማለታቸው ይታወሳል።

 በሌላ በኩል የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች ለተፈናቀሉ አማራዎች  መንግስት ምላሽ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ዛሬ ጠዋት በክልሉ ምክር ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ በአድማ በታኝ ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። አስተባብረዋል የተባሉ ተማሪዎችም መታሰራቸው ታውቋል። ከኢትዮጵያ ሶማሌ የተፈናቀሉትን ኦሮሞዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ በርስ በርስ ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች በአጠቃላይ  ከ1.2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በግለፅ ላይ ይገኛሉ።

የዶክተር ነገሪ በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰራጩት ሙሉ መልዕክታቸው የሚከተለውን ይመስላል፦

  “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ሌሎችን የማቀፍ እንጂ የማፈናቀል ባህል የላቸዉም፡፡

  ሰሞኑን አንዳንድ ሚዲያዎችና የዉጭ ተቋማት ከኦሮሚያ ክልል፣ ከቄለም ወለጋ ዞን፣ ከሰዲ ጨንቃ እና ሰዮ ወረዳዎች፡ ሰዎች እንደተፈናቀሉ አድርገው እያስወሩ ናቸው። እዉነታዉ ግን፣ በ1977 በአገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መጥተው በቄለም ወለጋ ዞን በስድስት ወረዳዎች ማለትም፦  ዳሌ ሰዲ፡ ሃዋ ገላን፡ ሰዮ፡ ላሎ ቅሌ፡ ጅማ ሆሮ እና ሰዲ ጨንቃ ወረዳዎች እንዲሰፍሩ የተደረጉት ወገኖቻችን ላለፉት 33 ዓመታት ቤተሰብና ንብረት አፍርተዉ አስከሁን ድረስ በሰላም እየኖሩ መሆናቸው ነው።

  በሰዲ ጨንቃ ወረዳ አምስት ቀበሌዎች ዉስጥ ቄጦ በመባል በሚጠራው አካባቢ የሰፈሩ ወገኖቻችን ሰሞኑን አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት ሳይሆን እንደሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች ሁሉ ከአካባቢዉ ህዝብ ጋር በሰላም መኖራቸውን የቀጠሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በእነዚህም ቀበሌዎች 1ኛ. በቄጦ 1 ቀበሌ 850 አባወራዎች (4935 ቤተሰብ)፤ 2ኛ. በቄጦ 5 ቀበሌ 810 አባወራዎች ( 5708 ቤተሰብ)፤ 3ኛ. በቄጦ 6 ቀበሌ 456 አባወራዎች (2302 ቤተሰብ)፤ 4ኛ. በቄጦ 7 ቀበሌ 623 አባወራዎች (3329 ቤተሰብ)፤ 5ኛ. በቄጦ 11 ቀበሌ 655 አባወራዎች (3072 በተሰብ) በድምሩ 3 ሺህ 394 አባወራዎች ወይም 19 ሺህ 346 ቤተሰቦች እየኖሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥም ሆነ ሰዮ ወረዳና ሌሎች ወረዳዎች ዉስጥ ከሚኖሩት አንድም ሰዉ አልተፈናቀለም፤ የሚያፈናቅላቸዉም አይኖርም፡፡

  በዚሁ በሰዲ ጨንቃ ወረዳ ከላይ ከተጠቀሱት ቀበሌዎች ዉጭ ባለው እጉ ኮፈሌ በተባለው ቀበሌ ውስጥ ከአካባቢዉ ህዝብ ጋር በሰላም ሲኖሩ ከነበሩ መካከል 42 አባወራዎች ቀደም ሲል በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች ተከስቶ የነበረዉን የፀጥታ ችግር በዜና በሰሙበት ወቅት ስጋት ዉስጥ እንደገቡ በመግለፅ ለመሄድ ባሰቡበት ወቅት፣ የአካባቢዉ ህዝብና የወረዳዉ አመራር እንዳይሄዱ ሲለምናቸው የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም እንደሄዱ፣ ይህም ሆኖ ከነሱ መካከል 15 አባወራዎች ተመልሰዉ 10 አባወራዎች ንብረታቸዉን ሽጠዉ ሲመለሱ አምስት አባወራዎች ደግሞ ዉክልና ሰጥተዉ መሄዳቸዉ ታዉቋል፡፡

  የአከባቢዉን ህዝብም ሆነ አመራሩን የማይወክሉ አንዳንድ ግለሰቦች ያልተለመደ ባህርይ አሳይቷቸዉ የነበረ ቢሆን እንኳን በህግ አግባብ ማስተካከል እየተቻለ እና ሌሎች ወገኖቻችን በአምስት ቀበሌዎች ዉስጥ እንዲሁም በዞኑ ልዩ ልዩ ወረዳዎች በሰላም እየኖሩ ባለበት ወቅት እነዚህ በቁጥር ጥቂት የሚሆኑ ወገኖቻችን መሄድ አልነበረባቸዉም፡፡

አሁንም ከወረዳዉ አመራርና ከአካባቢዉ ነዋሪዎች በተገኘው መረጃ መሰረት ንብረታቸዉ እንዳይጠፋ፤ መሬታቸዉንም ማንም ሰዉ እንዳያርስባቸዉ ህዝቡና አመራሩ ጠብቀው በማቆየት ላይ ናቸው። ሲመለሱም ተረክበው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ በመጠባበቅ ላይ ናቸዉ፡፡

  ከአማራ ከልላዊ መንግሥት ለማጣራት በተደረገው ጥረት እነዚህ ከሰዲ ጫንቃ እጉ ኮፈሌ ቀበሌ በራሳቸዉ ፍላጎት የሄዱት ሰዎች የተወሰኑት ራያና ቆቦ አከባቢ እንዳሉ ብነገርም በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ዉስጥ እንዳልሆኑ ተገምቷል። የትም ቢሆኑ ግን እንደማንኛውም ዜጋ ያለምንም ስጋት ወደ ቄዬአቸዉ መመለስና መኖር እንደሚችሉ፣ ለዚህ ደግሞ የወረዳዉ አመራር አስፈላገዉን ድጋፍ እንደሚያደርገላቸዉ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

 በቡኖ በደሌ ዞን ዴጋ፤ጮራና ድዴሳ ወረዳዎች ከወራት በፊት ተፈጥሮ በነበረዉና ወድያዉኑ አንዲስተካከል በተደረገዉ አለመግባባት ምክንያት መስተጓገል የደረሰባቸዉን እንዲሁም የአካባቢዉ ህዝብና አመራር እንዳይሄዱ እየለመናቸው ህብረተሰቡን የማይወክሉ የጥቂት ግለሰቦች ትነኮሳን ሰምተዉ በራሳቸዉ ፍላጎት ወደ አማራ ክልል የሄዱትን ሰዎች በተመለከተ ግን የሁለቱም ክልል አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሰዎቹ ተወካዮች የተሳተፉበት ዉይይት አንደተደረገና መፍትሄ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

በአጠቃላይ መሬት ላይ ያለዉ እዉነታ ከላይ የቀረበውን ይመስላል። ይህን ዕውነታ ወደ ጎን በመተዉ በተለይም በዚህ ሳምንት ነገሮችን እያጋነኑ በማቅረብ በህዝቦቻችን መካከል የኖረውንና በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጠናከረ የመጣዉን መልካም ግንኙነት ለማደናቀፍ በሚደረግ ሙከራ ህዝባችን እንዳይደናገር እናስገነዝባለን፡፡”

LEAVE A REPLY