/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (National Movement of Amhara – NAMA) የመስራች ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። ጉባኤው እስከ ነገ እንደሚዘልቅም ታውቋል። አዲስ የሚመሰረተው ንቅናቄ የአማራ ህዝብ መብትና ጥቅምን ለማስከበር የሚቀሳቀስ መሆኑንም ከመስራቾቹ መካከል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን የፊርማ ማሰባሰብና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልቶ የዛሬውን ጉባኤ እንደጀመረ ተገልጿል። የፓርቲው ዋና ማዕከልም አዲስ አበባ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን ለማሳተፍ እንደሚሰራ የተገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ በጎሳ መደራጀትን በህግ ከተቀበለች ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ “በብሔር” የተደራጁ በርካታ ፓርቲዎች ቢኖሩም ለአማራው ግን ይህ ሁለተኛው (በሀገር ውስጥ) የሚወክለው ፓርቲ መሆኑ እንደሚሆን ተገምቷል። የመጀመሪያው የአማራ ብሔር ፓርቲ በ1984ዓ.ም የተመሰረተው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መሆኑ ይታወቃል።