የቀደሙትን ፓርቲዎች ያደናቀፉ እንቅፋቶች! /ጌታቸው ሺፈራው/

የቀደሙትን ፓርቲዎች ያደናቀፉ እንቅፋቶች! /ጌታቸው ሺፈራው/

የትህነግ/ኢህአዴግ ዘመን ፖለቲካው ግራ የሚያጋባ ነው። ሕጋዊ ስርዓቱ የተስተካከለ ስላልሆነ ብቻ አይደለም። ያለው ሕግም ማስመሰያ ነው። በመሆኑም የታቀደ የፖለቲካ ትግል እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል። በዚህም ይመስላል አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ትግላቸው “ልማዳዊ” ነው! የሚገመት፣ የተለመደ! አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የወደቁባቸው ከእነዚህ ልማዳዊ ስልቶች ባለመውጣታቸው ይመስለኛል። እንደኔ እምነት ዛሬ የተመሰረተው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች ከወደቁባቸው አዙሪት መውጣት አለበት! እንደ አንድ ተመልካች ምሳሌዎችን ልጥቀስ:_

 ~የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደትልቅ ነገር ይታያል። በእርግጥ አንገትም ስለሚያስቆርጥ ነው፣ በእርግጥ ከስራ ስለሚያስባርር ነው፣ በእርግጥ ትዳር ስለሚያስፈታ ነው! የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ብቻ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ይህ ለፓርቲ አባልነት የሚሰጠው ክብር፣ ወደፓርቲ ቢሮ የአባልነት ቅፅ ለመሙላት የሚመጣውን ሁሉ እንዲታመን አድርጓል። ከሰልፍና ከስብሰባ መልስ ወደ ቢሮ ብቅ ብሎ አባልነት የሚሞላው ብዙ ነው። ይህ ሰው መበደሉን ከተናገረ፣ “ወያኔ ይውደም!” ካለ ይታመናል። ይህን የሆነው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን የከበደ ዋጋ ስለሚያስከፍል ነው። ለዚህም አባል ሊሆን የመጣው አብዛኛው ሰው አባል ይሆናል። ፓርቲዎች አባል ልሁን ብሎ የመጣን ሰው አጣርተው የሚመልሱበት አጋጣሚ ብዙ አይደለም። ከምንም በላይ ከሰልፍና ስብሰባ መልስ የመጣውን ከመቀበል ባለፈ አጥንተው የሚመለምሉት ብዙ አይደለም። ትህነግ/ኢህአዴግ ደግሞ ከሰልፍና ስብሰባ በኋላ በርካቶችን ይልካል። ለህዝብ በነፃ የሚሰሩት ጋር፣ በኢህአዴግ ትዕዛዝ ፓርቲ ለማፍረስ የሚሰሩት ገንዘብ ይከፈላቸዋል።

 ~ትህነግ/ኢህአዴግ አብዛኛውን የደህንነት መዋቅር የሚያውለው ስልጣኑን ለማስጠበቅ ነው። በተለይ ተቀናቃኞቹን ለማጥፋት በርካታ ሀይሉን ይጠቀማል። ለዚህ ተግባሩ ከተቃዋሚው የሚገጥመው ፈተና ምንም የሚባል ነው። በእርግጥ ተቃዋሚዎች ገዥዎቹን የሚሰልሉበት እድል ጠባብ ነው። መረጃ መንሳትና ማወናበድ ግን ከአቅማቸው በላይ አይደለም። ፖለቲከኞቹ ስልካቸው እንደሚጠለፍ እያወቁ ከሌላ ሰው ጋር ሲያወሩ የሚያስቀሩት ነገር የለም። ተገናኝተው ማውራት እየቻሉ በስልክ ጨርሰውት እንደገና በአካል ይገናኛሉ። ለቢሮ ፀሀፊነት የሚመጡት፣ ለፅዳት የሚቀጠሩትን ተጠንተው አይደለም።

አብዛኛው ተቃዋሚ የራሱን ትግል ከቀጠለ ሌላው ትርፍ ነው። ጥቃቅን ነገር ይመስለዋል። የፓርቲው ሰነዶች፣ ደብዳቤዎች አብዛኛው ወይንም ማንኛውም አባል ነኝ የሚል የሚያያቸው ናቸው። አመራር ብቻ የሚያውቀው፣ ለአባል የማይፈቀድ……ተብሎ ሚስጥር የለም፣ ሚስጥር አባላትን አለማመን የሚመስላቸው አሉ፣ ሚስጥር መያዝ የማይችለው ብዙ ነው፣ ሚስጥረኝነት ከሌብራሊዝም ያፈነገጠ የሚመስለው አይጠፋም! የመረጃ ቀላል የለውም! አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ደግሞ ትግላቸው ግልፅ እንደሆነ ያስባሉ፣ ከአባልም ከገዥዎችም የሚደብቁት ሚስጥር የላቸውም።

 ~ከትህነግ/ኢህአዴግ መጠንቀቅ አንዱ ድክመት እንደሆነ ሁሉ አባላት ላይ ክትትል አይደረግም። የመጣው ሁሉ ታምኖ ወረቀት ይበትናል። ሌላም ስራ እንዲሰራ ተሰጥቶት ጥሩ ከመሰለ የተሻለ ስራ ይሰጠዋል። በአንድ ወቅት ነው። አንድ ፓርቲ ቢሮ ውስጥ የውይይት ፕሮግራም ነበር። በዚህ ፕሮግራም ላይ በፈቃደኝነት ቡና የሚያፈሉ ሰዎች ነበሩ። አንድ የፓርቲ አባል ታስሮ ቡና ሲያፈሉ ከነበሩት መካከል አንዷን እስር ቤት አግኝቷታል። ስራዋ ፖሊስ ነበር። ቡና እያፈላች ወሬ መቃረሟ ነው።

~ዲስፕሊን ትልቁ የፓርቲዎች ፈንጅ ነው። በደንብ ከተያዘ ጥሩ ፓርቲ ይፈጥራል። እንደነገሩ ለሆነ ይበትነዋል። ሲበትንም አይተናል። የፓርቲ መሪ ወይንም አባል ሆነ የፓርቲውን ጉዳይ ፌስቡክ ላይ ይዘረጋዋል። አማራር ሆኖ “በግሌ ነው” ብሎ ይፅፈል። የፓርቲ አመራር ከሆነ በኋላ ሕዝብ የሚያውቀው በፓርቲ አባልነቱ ነው። ስልጣን ያለው አካል በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ከመግለፁ በፊት አባልም አመራሩም በየፊናው ይፅፋል። ጥንካሬውን እንደ ፓርቲ አባልና አመራርነቱ የወሰደለት ሕዝብ ድክመቱንም “የግሌ ነው” ቢል የሚሰማው አይደለም። በዚህ መልክ ብዙዎቹ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ተበትነዋል!

 ~ፓርቲዎች ፕሮግራም ይኖራቸዋል። ሆኖም ከዋናዎቹ ውጭ አብዛኛው አባል የፓርቲውን፣ የገዥዎቹንና የተቀናቃኞቹን ድክመትና ጥንካሬ፣ ፖሊሲ፣ ወደየት እንደሚሄዱ በጥቅል ካልሆነ በዝርዝር አያውቁትም። አብዛኛውን ጊዜ የኢህአዴግ አምባገነንነት ካንገሸገሸው በቂ ይመስላል። “ኢንዶክትሪኔሽን” የሚባል ነገር አይታወቅም። ቢበዛ በሳምንት አንድ ቀን የሚደረግ ውይይት ነው። የጥናት ቡድንና መሰል ጉዳይ ያረጀ ያፈጀ የ60ዎቹ ፖለቲካ የሚመስለው ብዙ ነው። ይህን የመሰለ አባል ነገ ችግር ቢመጣ አይመክትም!

~አብዛኛው የፓርቲ ፖለቲካ መስዋዕት የመሆን ፖለቲካ ነው። ወረቀት መበተን፣ ሰልፍ መውጣት፣ ስብሰባ… ክርክር ነው። ከሀገር ውጭ አይወጣም። ሌሎች ተቋማትን ማሳመን ላይ አይሰራም። ወደ ውጭ ከተባለ የሚፈለገው ዳያስፖራው ካልሆነ የተለያዩ መሰል አጋር ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን አፈላልጎ ገዥዎች ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ልምድ ማግኘት ብዙም አይሰራበትም። እንዲያውም የሌሎቹን ተቋማት ቤት ማንኳኳት ክብርን የመጣል ያህል ይታያል።

 ~ፓርቲዎች አብዛኛው ግባቸው ፓርቲነት የሚሆንበት ጊዜ ይበዛል። እነሱን የሚያግዙ ሌሎች ተቋማትን አይፈጥሩም። ቀጫጭን ገመድ የሚያያይዛቸውን ማህበራዊ ተቋማት አይጠቀሙም። ሁሉ አባላቸው ቢሆን ነፍሳቸው ነው። ለሚታገሉለት ሕዝብ ሌላ አደረጃጀት አይታያቸውም። አይፈጥሩም ወይንም አያበረታቱም። መግነን የሚፈልጉት ብቻቸውን ነው። ሲወድቁ ግን ከፊትም ከኋላም ደጋፊ የላቸውም። የሚያሳብቡበት፣ የሚጠለሉበት፣ አባል የሚመለምሉበት ሌላ ቅርብ ተቋም የላቸውም።

~የፓርቲ አባላት ካድሬዎች ይሆናሉ። የራሳቸውን ድርጅት ማሞካሸት እንጅ ድክመታቸውን የሚነግራቸው አይወዱም። ገዥዎቹ አንዱን ፓርቲ ከሌላው የሚያናቁር አጀንዳ ሲዘረግፍ ከሌላው ፓርቲ ጋር አይንህን ለአፈር መባባልን ስራ ያደርጉታል። ልክ ከሌላው ፓርቲ አባል ጋር መተናነቅም አጀንዳ ሆኖ እንደሚዘራው ሁሉ በአንድ ፓርቲ ውስጥም በአመራሩ ላይ የሚያስወሩ፣ በጠንካራ አባላት ላይ አሉባልታ የሚያስነዙ የገዥው ሰዎች ይለቀቃሉ። አሉባልታና የሀሰት ወሬ ደግሞ ፓርቲዎች፣ የፓርቲ አባላትና መሪዎች ጥል ውስጥ ከገቡባቸው ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ከፈረሱበት መካከልም እንዲሁ!

~በተለይ በተለይ እንደ ብሔርተኛ ፓርቲ ጠላቶች በርካቶች ናቸው። የሕዝብ ችግር የተከመረ ነው። በዚህ መካከል ገዥዎቹ በመናቆር ጊዜን እንዲጨርስ አጀንዳ መዘርገፋቸው የተለመደ ነው። የዘመኑ ፌስቡክ ደግሞ መናቆሪያ ሆኗል። ይህን የጎንዮሽ መናቆር በድርጅቶች መካከል የልምድ ያህል ሆኗል። በተለይ ብዙዎች ጠጠር የሚወረውሩበት ሕዝብ ወኪል የሆነ/ነኝ ያለ አካል የጠላቶቹን ቁጥር ለመቀነስ መጣር ያለበት ይመስላል። ለዚህ ትግስት አስፈላጊ ነው። የሕዝብን ትግል ሰብአዊና ማንም ሊቆምለት የሚገባ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ ይመስላል!

LEAVE A REPLY