ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግብፅ ታስረው የነበሩ 32 ሰዎችን ይዘው ተመልሰዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግብፅ ታስረው የነበሩ 32 ሰዎችን ይዘው ተመልሰዋል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግብፅ ታስረው የነበሩት 32 ሰዎችን ይዘው መመለሳቸው ተገለጸ።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግብፅ ካይሮ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ፤በተለያየ ምክንያት የግብፅ መንግስት አስሯቸው የነበሩ 32 ኢትዮጵያዊያንን በእራሳቸው አውሮፕላን አሳፍረው ይዘው መመለሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።

ከተመለሱት 32 ኢትዮጵያዊያን መካከልም የቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) የጦር መሪ የነበሩትና ከዓመታት በፊት ከ100 በላይ ወታደሮችን በመያዝ  ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ገብተው የነበሩት  ኮለኔል አበበ ገረሱ እንዲሁም የኦህዴድ መስራችና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩ አቶ ዮናታን ዱቢሳ እንደሚገኙበት ተገልጿል። ሁለቱም ኤርትራ ውስጥ የነበራቸውን የጦር ሰፈር በመተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር አዲስ አበባ የገቡ መሆናቸውን የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ጨምሮ ገልጿል።

እ.ኤ.አ በ2015 በሊቢያ በስደት እያሉ በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን አጽም ከተቀበረበት በማውጣት ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሶ የመጨረሻ እረፍት እንዲያገኝ ለማድረግ ከግብፅ መንግስት ጋርም ስምምነት ማድረጋቸው ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ጋር በጋራ በመሆን በአማርኛ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አባይ ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የተሰጠ በረከት ስለሆነ የእኛ ስራ የእኛን ድርሻ መጠቀምና የእናንተን ድርሻ ወደ እናንተ መላክ ብቻ ሳይሆን መድረሱንም ማረጋገጥ ጭምር እንደሆነ አውቃችሁ በእኛ በኩል ስጋት እንዳይገባችሁ።”በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫውን በአማርኛ ቋንቋ መስጠታቸው “በራስ ማንነት መኩራት ነው” በማለት የብዙዎችን ቀልብ የሳበና ከፍተኛ አድናቆትም እንዲቸራቸው ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በቀድሞው ሊግ ኦፍ ኔሽንና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአማርኛ ቋንቋ ንግግሮች ያቀርቡ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

LEAVE A REPLY