/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በሀዋሳ ከተማ ከትናንት በስትያ የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬም ተባብሶ መቀጠሉን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። ከተማዋ በተኩስ ድምፅ ስትናጥ የዋለች ሲሆን በድንጋይና በተለያዩ ቁሳቁሶች ተመተው በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል።
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በጉራጌና በቀቤና ብሔረሰቦች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ቀጥሎ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉም ታውቋል። ከ35 በላይ ቤቶች ሲቃጠሉ፣ ስምንት ተሽከርካሪዎችም በእሳት ወድመዋል። “ዘርማ” በመባል የሚታወቁት የጉራጌ ወጣቶች ቅዳሜ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራታቸው ታውቋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን አስመልክቶም ስርዓቱ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል። መግለጫውም የተቀሰቀሰው ግጭት በምንም መስፈርት ህብረተሰቡን የማይወክልና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ባልተዋጠላቸው አካላት ጠንሳሽነት የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል።
“መንግስት” በግጭቱ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ ብሏል። በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት መርምሮ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስድም በመግለጫው ተጠቅሷል።