ላለፉት ስድስት ወራት ያክል በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ልዩነቱ ሰፍቶ ወደ መፈረካከስ እየደረሱ መሆኑን እኔን ጨምሮ ጥቂቶች ምክንያታዊ ምልከታችንን ስናካፍል ቆይተናል። ብዙዎች ግን ከበቂ በላይ አመንክዮ በማቅረብ ጥርጣሬያቸው የጎላ ነበር። የተንደረደርኩበት እይታ ይበልጥ እውን እየሆነ የመጣው የዶር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆንና በአፋጣኝ እየወሰዷቸው ያሉ የህወሃትን የበላይነት የሚንዱ እርምጃዎች ሲታዩ ነው። በኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ ሃይሎች በህዝቡ ትግል መወለዳቸውን ተቃዋሚውም እየተረዳውና እየተቀበለው መጥቷል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ቅርቃር ውስጥ የገባችው ህወሃት ናት። ሽብልቁ ይበልጥ እየተቀበቀበና ጥልቀት እያገኘ ሲመጣ ትህነግ ልብሷን አውልቃ ስንጥቅጥቋ ወጥቶ እብደቷን ገሃድ አውጥታለች። ከሰኔ 3 እስከ 5 2010 ያካሄዱትን ግም-ገማ ተከትሎ ያወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ መቀበል እንደተሳናቸውና እየተዋጋን እንሞታለን ያሉበት እራስ የማጥፋት/ሱዊሳይዳል ድንፋታ ነው!
1) በዶ/ር አብይ የሚመራውን ስራ አስፈፃሚ በሚከተሉት ነጥቦች ይከስና የኢህአዴግ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ይጠራልን ብለዋል። ዶ/ር አብይን በስም ባይጥቅሱም የአልጀርስን ስምምነት በመርህ ብንቀበልም ህዝባችንን ቀድመን እንድናባብል እድል አልሰጠህንም፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት ሊወስንበት ሲገባ በስራ አስፈፃሚ ጨርሰህ አግለህናል የሚል ክስ አለበት።
ሌላኛው ክስ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ዶ/ር አብይ መርህን ያልተከተለ ሹመትና ሽረት እየፈፀመ ነው ይላል። ሶስተኛው እሮሮ የህወሃት ነባር ባለስልጣናትና ሚሊሺያ ስለተገፋን እውቅናና ካሳ ይከፈለን የሚል ድርቅናም አለበት።
2) ሌላኛው በአንክሮ መታየት ያለበት የመግለጫው ክፍል እራሳቸው አቡክተው የጋገሩት ህገ መንግስት(ህገ ወያኔ) መልሶታል ያሉት የድንበርና የማንነት ጥያቄ አከርካሪውን መትተነዋል ባሉት ሃይል(አማራው) አገርሽቶ መነሳቱ ነው። ይህን የባለቤትነትና የማንነት ጥያቄ ትህነግ ድርጅቴንና የትግራይ ህዝብን “ሊመታ” የመጣ ስለሆነ ክተት ሰራዊት መልሰን ጫካ እንግባ እያሉ ጦር ሰብቀዋል።
3) ህወሃት ደጋግማ ያነሳችው አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መርህ መጣስ ነው። ይህ ነጥብ ህወሃትን ከለውጥ አራማጁ የዶ/ር አብይ ሃይል እና ይሁንታን እየሰጠ ካለው ለውጥ ፈላጊ ህዝባዊ ሃይል ፍንትው ባለ ርእዮተ አለም ተቃርኖ ውስጥ ከቷቸዋል። ይህ ወደ ቁሳዊ ግጭት/ፍልሚያ ማምራቱ እድሉ የሰፋ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ነው።
4) ህወሃት ብቻዋን ቀርታለች! የአልጀርስ ስምምነት መቀበል በትግራይ ውስጥ ህዝባዊ ቁጣ በመቀስቀሱ ቀጥታ የሚያላትመው ህወሃትን ነው። በኢህአዴግ ውስጥም የህወሃት የበላይነት በመናዱ (የደህንነትና የመከላከያው ቁንጮዎች መቀየራቸው እንደ አንድ ማሳያ ወስደን ዶ/ር አብይ የሾማቸውን የመሻር እድሉን እያጤንን) ተፅእኖ ፈጣሪ መሆናቸው እጅጉን አሽቆልቁሏል። ለጊዜውም ቢሆን እየተልፈሰፈሰ ባለው ሽፈራው ሽጉጤ እና ወደ ኢህአዴግ እህት ፓርቲ ለማስገባት ህወሃት እያባበለች (ሲላትም እያስፈራራችበት) ባለው ጠብደሉ አብዲ ኢሌ ላይ ያረጁ ክንዳቸውን ተንተርሰዋል።
ከላይ የጠቃቀስናቸውን የህወሃት የቀቢፀ ተስፋ መፍጨርጨር በአግባቡ ፈጣን የመልስ እርምጃ ካልተወሰደ እየገሰገሰ ያለውን የለውጥ ባቡር ማስቀረት ባይችሉም ሊያደናቅፉትና ሊያዘገዩት ይችላሉ። የሚከተሉት እርምጃዎች በፍጥነት ሊወሰዱ ይገባል፦
1) ዶ/ር አብይ ከህወሃት ፍፁም የፀዳ የሴኩሪቲና የፕሮቶኮል መዋቅር መዘርጋት አለበት።
2) በመከላከያውና በደህንነቱ ውስጥ አዲስ የአመራርና የሃይል አወቃቀር/አሰላለፍ ያስፈልጋል። ከላይ የተቀየሩት ሁለቱ ሹመኞች በጊዚያዊነት ብቻ እንዲቆዩ ተደርጎ በስራቸው ያሉ የጦርና የደህንነት ከፍተኛና መካከለኛ መኮንኖች መፐወዝ አለባቸው። ዶ/ር አብይ በውስጡ ያለፈ ነውና አይጠፋውም ግን ደጋፊው የለውጥ ሃይሉ ይህን ግንዛቤ ይዞ የመፍትሄው አካል ለመሆን እራሱን ማሰለፍ አለበት።
3) ዶ/ር አብይና ከኢህአዴግ ውስጥ አፈትልከው የወጡት የለውጥ ሃይሎች ለዚህ የበቁት ብቸኛ ምክንያቱ የህዝባችን ትግል ነውና ህዝቡን ከጎናቸው የሚያሰልፍ እየወሰዱት ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች ይግፉበት።
4) ህወሃት የኢህአዴግ ጉባኤ በማስጠራት የሶማሌውን ጨምሮ አጋር የሚባሉ ወያኔ የጠፈጠፋቸውን ምስለኔ ድርጅቶች አካተን ውህድ ሃገር አቀፍ ፓርቲ እንፍጠር ሊሉ ይችላሉ። ይህንን ለውጥ አራማጆቹ ቀድመው ሊዘጋጁበት ይገባል። አንድም አጀንዳውን ውድቅ ማድረግ። ውህድነቱ ገፍቶ የሚመጣ ከሆነም አጋር ድርጅት የተባሉት እንዳይካተቱ ማድረግ። ኢህአዴግ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ከማንም በላይ ፍላጎት ያላት ህወሃት ናትና ይህችን አሜኪላ ድርጅት ከማገድ እስከ ማባረር የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ስልት በመንደፍ ሳይቀደሙ መቅደም ነው።
5) የዶ/ር አብይ መንግስት ሁሉ አቀፍ የሆነ እሳቸው እንደሚሉት ከተፎካካሪው ሃይል ጋር አፋጣኝ ድርድና ውይይት ማድረግ አሁን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። የህወሃት አጉራ ዘለል ድንፋታ እስከናካቴው መቅበር የሚቻለው ይህ ሲከናወን ነው።
6) የዶ/ር አብይ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማስፈን አፋኝ የሆኑ ህጎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ እና አፈፃፀሞችን በምን ያህል ጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚያነሳ በግልፅ ያስቀምጥ። ለሁሉ እኩል የሚያሳትፍ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ፣ ግልፅ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዴት፦መቼ፦እና በምን መልኩ እንደሚፈፀም ለኢትዮጵያ ህዝብ በአስቸኳይ መልስ ይሰጠው።
ከላይ የተጠቀሱት የመፍትሄ እርምጃዎች ወያኔ ልትሰነዝር ከምትዝተው የለውጥ ማደናቀፊያ ፍልሚያ ሊገታት ይችላል። ለውጥ ከሚመጣ ሞቴን እመርጣለሁ ካለችም ፍልሚያው ከዶ/ር አብይ ጋር ብቻ ሳይሆን ከለውጥ ፈላጊው ጋር ሁሉ ይሆናል። ጊዜ አያሳየን የለ!
ህዝብ ሁሌም አሸናፊ ነው!
ሐሙስ ሰኔ 7 2010 ዓ.ም.
*******
Political Science and International Relations
(Addis Ababa University)
Diplomacy/International Conflict Management
(Norwich University, USA)