/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የትግራይ ክልል መስተዳድር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ላይ የቅሬታ ደብዳቤ ፃፈ። የክልሉ መንግስት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወይም ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ዛሬ በፃፈው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያው “የትግራይ ህዝብን አንድነት የሚጎዱና ማንነቱን የሚያጎድፉ ዘገባዎች እየሰራ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ሲል ጠይቋል።
በደብዳቤው ላይ ሦስት ዘገባዎች ለአብነት የተጠቀሱ ሲሆን፦
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ የተባሉ ግለሰብ “በፌዴራሊዝም ስም” ተጠርተው ሀሳብ እንዲሰጥ የተደረገበት ውይይት የትግራይን ህዝብ አደጋ ውስጥ በሚከት የተዘጋጀ መሆኑ”
- የውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ቡድን ያጠፋው ጥፋትና ኢብኮ የሰጠው ሽፋን የማይመጣጠን መሆኑና
- ኢብኮ በባድመ ከተማ ሰኔ 5/2010ዓ.ም ተገኝቶ ያቀረበው ዘገባ በከፍተኛ ሁኔታ የህዝብን ቁጣ መቀስቀሱን ያትታል።
ኢብኮ ወይም ኢቲቪ ባድመን አስመልክቶ የሰራው ዘገባ “ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም በመጨረሻ አካባቢ በትግራት ህዝብ ላይ ካስተላለፉት በጥላቻ የተመረዘ ንግግር የሚመሳሰልና በአካባቢው ህዝብ ላይ ተገቢ ያልሆ ስሜት የሚቀሰቅስ ነው” ብሎታል።
ኢብኮ ከጥፋቱ የማይታረም ከሆነ ግን ጉዳዩን ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ እንደሚወስደውም ጨምሮ ገልጿል።
ከ18 ዓመታት በፊት አልጀርስ ላይ አቶ መለስ ዜናዊና ስዩም መስፍን ፈርመው የተቀበሉትን “የአልጀርሱን ውል” የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መቀበሉን ከገለፀ ወዲህ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ሲሆን ይህም ሆን ተብሎ በዶክተር አብይ አመራርን ላይ እንቅፋት ለመፍጠር የተቃውሞ ሰልፎቹን ህወሓት በድብቅ እየመራቸው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።