ያንብቡት – ስለተኮሱት ወጣቶች እከራከራለሁ! /ጌታቸው ሺፈራው/

ያንብቡት – ስለተኮሱት ወጣቶች እከራከራለሁ! /ጌታቸው ሺፈራው/

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቢቢሲ ላይ ቀርቦ “አንድም ጥይት አልተኮስንም” በማለቱ የሚፃፉ አስተያየቶችን ተመለከትኩ። “ብለናችሁ ነበር” የሚል ይበዛል። አንዳርጋቸው ፅጌ የአርበኞች ግንቦት 7 ፀኃፊ ነው። “ብለናችሁ ነበር፣ ግንቦት 7 አንድ ጥይት አልተኮሰም” ብለው የሚከራከሩትም የአርበኞች ግንቦት 7 ደጋፊ፣ አባል ወይም ቅርበት የነበራቸው ናቸው። እኔ ደግሞ ከድርጀቱ ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም። “አባል ነህ” ተብዬ በሀሰት ከመከሰሴ ውጭ! ግን ስለተኮሱት ወጣቶች መስዋዕትነት እመሰክራለሁ!

አንዳርጋቸው “አልተኮስንም” ሲል ለፖለቲካ ፈልጎት ይሆናል፣ አባልና ደጋፊዎቹ ከግንቦት 7 የጠበቁትን ስላላገኙ ድክመት ያሉትን ለማስረገጥ ይሆናል። እኔ ከአንዳርጋቸውም ከደጋፊና አባላቱም ለግንቦት 7 አልቀርብም። ከእነሱ አያገባኝም!

ግን ነገ አንዳርጋቸው ብቻ ሳይሆን ድርጅቱ በመግለጫ “አልተኮስኩም” ቢል የልዩነት ሀሳቤን አቀርባለሁ። በድርጅቱ ስም የወደቁ ወንድሞቼ ደመ ከልብ እንዲሆኑ ስለማልፈልግ ነው። ስለተኮሱት ጥቂት ወጣቶች ድርጅቱንም ቢሆን እሞግተዋለሁ!

ሰኔ 27/2008 ዓም አንድ የግንቦት 7 ወታደር በአንድ ዝግጅታቸው እንደግኝ ይጠራኛል። 7 ሰዓት ላይ ቂሊንጦ እስር ቤት ዞን 1 ስምንተኛ ቤት ተገኘሁ። በርካታ በሽብር የተከሰሱ እስረኞች የእዝን ቆሎ ይቆረጥማሉ። የጋበዘኝን የአርበኞች ግንቦት ወታደር ስጠይው ሰኔ 27/2007 ዓም ወልቃይት ላይ ከትግራይ ልዩ ኃይል፣ ከትግራይ ሚሊሻ እና መከላከያ ሰራዊት ጋር ገጥመው የተሰዉትን ጓዶቻቸውን ለማስታወስ እንደሆነ ነገረኝ። እነዚህ እስረኞች ጠያቂ ቤተሰብ የላቸውም። ከጎናቸው የወደቁትን ጓዶቻቸውን ለማስታወስ ያደረጉት ዝግጅት ላይ የቀረበልልን ቆሎ እንኳ እስር ቤት ውስጥ ካወቋቸው እስረኞች ለምነው ነው። በዛ ዝግጅት በጦርነቱ ጉልበቱ ላይ ቆስሎ ባለመታከሙ ቅዝቃዜ በመጣ ቁጥር የሚሳቀቅ ክብረትም ነበር።

በዛ ጦርነት ወቅት አርበኞች ግንቦት 7 የላካቸው የአርማጭሆ ወጣቶች መተኮስ ብቻ አይደለም። ተኩሰው የገደሉት የመጀመርያው ሰው የልዩ ኃይል ኃላፊ የሆነ ኮማንደር ነው። በርካቶችን ገድለዋል። በርካቶችን አቁስለዋል። አርበኞች ግንቦት ሰባት 360 ጥይት አስይዞ የላካቸው ሶስት ወታደሮችም ህይወታቸውን ሰጥተዋል።

በዚህን ወቅት ብርሃን የተባለ የአርበኞች ወጣት ይቆስላል። የ23 አመቱ ብርሃን መተኮስ ብቻ አይደለም። ተተኩሶበትም ተመትቷል። እጁን ለመንግስት ጦር ላለመስጠት ራሱን ጨርሷል። ይህ እንደ አጤ ቴዎድሮስ “እጄን ጠላት አይዘውም” ብሎ ራሱን የጨረሰን ወጣት ለፖለቲካ ድርድር ወይንም፣ በየቦታው ሌላ የተኮሰውም እኔ ነኝ ይላል እየተባለ የሚወቀሰውን ድርጅት ለማብሸቅ ሲባል እንዲረሳ መፍቀድ ተገቢ አይመስለኝም።
አንዳርጋቸው ለምንም ይፈልገው ለምን አልተኮስንም ሲል የእነዚህ ወጣቶች መስዋዕትነትን ከንቱ እንደሆነ ይሰማኛል። በግንቦት 7 የተናደዱ ወገኖች የአንዳርጋቸውን ቃል ይዘው “አልተኮሱም” ብለው ሲከራከሩም የእነ ብርሃን ግለጥ መስዋዕትነት ከንቱ ይሆንብኛል።

አለማየሁ መለስ የታወቀ አርበኛ ነው። ይህ ጀግና የተገደለው በዚህ ወቅት ነው። አብርሃ ጅራ ክሊኒክ የነበረው ብርሃኑ የሚባል ዶክተር ነበር። ይህ ሰው ጥሩ ኑሮ ነበረው። የህዝብን መበደል አይቶ ኤርትራ ተሻገረ። በ2009 መጀመርያ አመት ወደ ኢትዮጵያ ገባ። ዶክተር ብርሃኑ በጦርነቱ እጁን ላለመስጠት ራሱን ሰውቷል። በርካቶች በዚህ መንገድ መሰዋዕት ሆነዋል።

ትዕዛዝ ዋልድባ ጫካ ውስጥ የትግራይ ልዩ ኃይል ጋር ሶስት ቀን ተዋግቷል። የላከው አርበኞች ግንቦት 7 ነው። 10 አመት ተፈርዶበት ዝዋይ የሚገኘው ትዕዛዙ ቁስሉን አልታከመም። ሰውነቱን በስቶ የገባው የፈንጅ ፍንጣሪ አሁንም ከሰውነቱ አልወጣም። አንዳርጋቸው “አልተኮስንም” ሲል፣ ሌሎቹም “አልተኮሱም” ሲሉ የእነ ትዕዛዙን መስዋዕትነት ከንቱ ማድረግ ነው። እኔ ደግሞ ለእነዚህ ጀግኖች እከራከራለሁ! ተኩሰዋል! ቢያንስ እንደግለሰብ እከራከርላቸዋለሁ! ቁስላቸው ይሰማኛል! በጨለማ ተጉዘው፣ አፍና አፍንጫቸው በባሩድ ተዘግቶ፣ ውሃ ጠምቷቸው፣ የቻሉትን ያህል ያደረጉት ድካማቸው መካድ እንደሌለበት አምናለሁ!

አቶ አንዳርጋቸው በእርግጠኝነት የአርባምንጩን እንግዳ አበበን ያውቀዋል። አሁን “እንግዳ እንዴት ነው?” ቢል “ተሰውቷል” ይሉታል። እንግዳ የሞተው በእንቅፋት አይደለም። እንግዳ አበበ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎችን መርቶ አርባምንጭ ጫካ የገባ ወጣት ነው። ተታኩሶ ጥይት ጨርሶ በሳንጃ እስከመግጠም የደረሰ ጀግና ነው። በኢቲቪ ዶክመንተሪ “እንግዳ አበበን ገደልነው” እያሉ ሸልለዋል። ስለሚያውቁት ነው። ቤተሰቦቹ የድርጅቱ ኃላፉ”አልተኮስንም” ሲል፣ የድርጅቱ ደጋፊ የነበሩት በቅንነት ወይ ድርጅቱን ለመሞገት “አልተኮሱም” ሲሉ በእስር ፍዳቸውን ሲያዩ የኖሩት የእንግዳ ቤተሰቦች ያ ወጣት ለማን ሲል ተሰዋ ሊሉ ነው?

ሰኔ 26 እና 27/2007 ዓም ግንቦት 7 ልኳቸው የተሰውት ወጣቶችን ወታደራዊ ዲስፕሊን የሚባል ያልፈጠረበት የገዥው ጦር አስከሬናቸውን ሜዳ ላይ ጥሎ እንዳይቀበሩ ከልክሏል። ከቀናት በኋላ ግን የወልቃይት እረኞች የአቅማቸውን ያህል መሬቱን ጭረው አፈር አልብሰዋቸዋል። ቂሊንጦና ቃሊቲ የሚገኙት የሟቾቹ ጓደኞች ሁሌም ከጎናቸው ስለወደቁት ወንድሞቻቸው ያስባሉ። አስታዋሽ ሲያጡ፣ ተራ ፖሊስ መሳርያ ስለያዘ ብቻ ከፍ ዝቅ ሲያደርጋቸው ተኩሶ ገድሎ የወደቀውን አለማየሁ መለስን ያስታውሳሉ። “አይ አለማየሁ አንተኮ እድለኛ ነህ” ይላሉ። ዛሬ በድርጅታቸው ሰው፣ በደጋፊዎቻቸው፣ ወይንም በወንድሞቻቸው መስዋዕትነታቸው መና እንደቀረ፣ አልተኮሱም እንደተባሉ ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን?

አንደኛው እንደተፈታ የመጀመርያ ስራው የወንድሞቹን አፅም ቤተሰቦቻቸው ጋር አምጥቶ መቅበር እንደሆነ አጫውቶኛል።

በእርግጥ አርበኞች ግንቦት 7 ብዙ መስራት ነበረበት የሚሉ በርክተዋል። ከፕሮፖጋንዳው አንፃር ልክ ይመስሉኛል። በእርግጥ “በሰሜን እዝ” ዜና ያልሆኑም የሆኑም ነገሮች ይነገራሉ ይባላል። በዚህኛው አልተኮስንም ቢሉ ችግር ላይኖረው ይችላል። ወይም በዚህኛው አልተኮሱም ተብለው ሊተቹ ይችላሉ።

ጥቂትም ቢሆኑ ግን የተኮሱ ካሉ ሊካዱ አይገባም። ስለተኮሱ ብቻ አይደለም። ህይወታቸውን ሰጥተዋል። አንድም ቢሆን ነፍስ ነፍስ ነው፣ አንድም ቢሆን መስዋዕትነት መስዋዕትነት ነው! በዚህ ጉዳይ ለድርጅቱ አልከራከርም። ለድርጅቱ አንዳርጋቸው አለ። በዚህ ጉዳይ ድርጅቱ ወቃሽ ሞልቶታል። በሁለቱ ፍትጊያ ግን ስኳርን ስንቃቸው አድርገው፣ ጉሮሯቸው ደርቆ መስዋዕት የሆኑትን አንድም፣ ሁለትም……ይሁኑ መረሳት የለባቸውም። እነሱ ተኩሰዋል! ተሰውተዋል!

ምን አልባት አካሄዱ ትክልል ነው ወይስ አይደለም፣ ትግሉ በቂ ነው አይደለም፣ መስዋዕትነቱ ተገቢ ነበር አልነበረም የሚለው ሊያከራክር ይችል ይሆናል! እሱን ለድርጅቱና ተችዎቹ እተወዋለሁ! ለፖለቲካ ሲባል ግን፣ ለመበሻሸቅ ሲባል ግን የወደቁትን ወጣቶች መስዋዕትነት ከንቱ ማስቀረት ተገቢ አይደለም! ስለድርጅቱ አያገባኝም! ስልቱን ባልደግፈው እንኳ፣ የላካቸው ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ ባልሆን እንኳ ጭቆና አንገብግቧቸው ሲሰዉ ገዥዎች እንደረሷቸው ሁሉ ድርጅታቸውም ሲረሳቸው ዝም አልልም!
ተኩሰው፣ ተተኩሶባቸው፣ እጅ አንሰጥም ብለው ራሳቸውን ስለሰውት ጥቂቶች እመሰክራለሁ! መስዋዕትነታቸው ከንቱ እንዳይሆን!

ለእኔ የአንድ ወንድሜ መስዋዕትነትም እንዲረሳ አልፈልግም! እናም ተኩሷል ብየ እከራከራለሁ! ስለ ብርሃን፣ ስለ አለማየሁ፣ ስለ እንግዳ፣ ስለ አብርሃጅራው ዶክተር ብርሃኑ! ከአንድ በላይ ጥይት ተኩሰዋልና! ከአንድ በላይ ጥይት ተተኩሶባቸዋልና! እጃቸውን ለጠላት ላለመስጠት ራሳቸው ላይም ከአንድ በላይ ጥይት ተኩሰው የአጤ ቴዎድሮስን የጀግንነት መርህ ተከትለዋልና!

ተኩሰዋል! ክቡር ህይወታቸውን ሰጥተዋል!

LEAVE A REPLY