/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በደቡብ ክልል የበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። በሀዋሳ ከተማ ባለፉት አራት ቀናት በተፈጠፈው ግጭት ምክንኒያት የአስር ሰዎች ህይወት ሲጠፋ፤ ዘጠኝ ሰዎች ከባድ ጉዳት እንዲሁም በ85 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ማምሻውን አስታውቋል።
የኮሙኒኬሽን ቢሮው እንዳስታወቀው ከ2500 ሰዎች በላይ እንደተፈናቀሉና ግምቱ ያልታወቀ የመኖሪያ ቤቶችና ንግድ ድርጅቶች በእሳት መውደማቸውን ጨምሮ ገልጿል።
በሀዋሳና ወልቂጤ በአንጻራዊነት ከተሞቹ ፀጥታ የሰፈናባቸው ቢሆንም ወላይታ ሶዶ ከፍተኛ ተቃውሞን ስታስተናግድ መዋሏን የተለያዩ መረጃዎች ጠቁመዋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ በተቃውሞ ስትናጥ የዋለች ሲሆን የተለያዩ መፈክሮችን ህዝቡ ሲያሰማ እንደዋለ ታውቋል። “ዴኢህዴን የህወሓት ተላላኪ ነው።ዴኢህዴን እኛን አይወክልም።”የሚሉና ሌሎች በርካታ ድምፆች መሰማታቸውን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።በሶዶ ከተማ የትራንስፖርት፣ንግድና ሌሎች የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መቆሙም ታውቋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ከሰዓት በሗላ ወደ ተለያዩ ወረዳዎች መዛመቱ ተገልጿል።ህዝባዊ ተቃውሞውም “የወላይታ ተወላጆች መብት እስኪከበር ድረስ ይቀጥላል” ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ማምሻውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን(ኢቲቪ)በሰጡት መግለጫ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሀዋሳ አቅንተው ህብረተሰቡን እንደሚያወያዩ አስታውቀዋል።