/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት ተዘርፎ የተቋቋመው ኤፈርት የተሰኘው የህወሓት ንብረት አክሲዮኖችን ለህዝብ መሸጥ ሊጀምር መሆኑ ዶክተር ደብረፂዮን አስታወቁ። በህግ የበላይነት፣ በሰብአዊ መብቶችና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙርያ ያተኮረ የትግራይ ፖለቲከኞችና ሙሁራን የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ በሀርመኒ ሆቴል መካሄዱን ኢትዮጵያ ላይቭ አፕዴት የተሰኘ ድህረ-ገፅ ዘግቧል።
በውይይቱ ላይም ለረጅም ዓመታት በተለያዩ ቅራኔዎች ምክንያት በአንድ መድረክ ላይ አበረው ያልታዩ ግለሰቦች መሳተፋቸውም ታውቋል።በውይይቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳድር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል “ኤፈርት” አክሲዮኖችን ለህዝብ መሸጥ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።ኤፈርትን ወደ ግል ይዞታ እንዲዞር በህወሓት ባለስልጣናት መወሰኑን እንዲሁም ከፖለቲካ ሰዎች ወጥቶ በባለሙያዎች መመራት እንደሚጀምርም ጨምረው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሀላፊ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኜው “ውራይና” ለተባለች ትግርኛ መፅሔት በሰጡት ቃለ-ምልልስ “እየተካሄደ ያለው ለውጥ ሀገርንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በልቶታል” ማለታቸው ታውቋል። ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች በተደረገው ሪፖርት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኜው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ሀላፊ በነበሩበት ወቅት ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ማባከናቸው ተገልጿል።ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን ተከትሎ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበው ተቀባይነት በማግኘታቸው በዘረፉት የሀገር ሀብት ሳይጠየቁ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።