መደመር ‘ ‘ ደ ‘ ን ጠበቅ /ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ/

መደመር ‘ ‘ ደ ‘ ን ጠበቅ /ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ/

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብዙ ንግግራቸው ላይ በአፅንኦት መደመር ‘ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ :: ባጠቃላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸው ሁሉ የሚያሰባስብ: የሚያፋቅር : አንድነትን የሚያስተጋባ: ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያን እየለወጡዋት ነው:: ከንንግግራቸው ጋር በተግባር የሚያሳዩት ሁሉ ከጨለማና ሕዝብን ከለያየ: ከከፋፈለ: በጥቂቶች ተገዝቶ: ተዋርዶ ከኖረበት ዘመን ወደ ብርሀንና የተስፋ ዘመን እያሸጋገሩት ነው:: አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሆ ‘መደመር ‘ ነው’::

ኢትዮጵያን ታላቅ አድርጓት እስከዛሬ በማንም በምንም ሳትደፈር እዚህ ያደረሳት መደመር ነው:: ኢትዮጵያውያን በባህል: በቋንቋ: በሀይማኖት ያሸበረቀ የድልና የትግል ታሪክ ተጎናጽፈው የደፈራቸውን ሁሉ ያሸነፉት በመደመራቸው ነው:: እንደሰው በውስጣቸው ልዩነት ኖሮ አልፎ አልፎ ቢጋጩም: እንደ አንድ ሕዝብ: አንድ አገር: ተደምረው: አሸንፈው ኢትዮጵያ የምትባል አገር አቆዩን :: በመደመር ያላመኑትና ይህንን እድል ያላገኙት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ቅኝ ገዢዎች በሰጧቸው ድንበር ውስጥ ተከፋፍለው ለአገራቸውም ስም ሰጥተው በዚያ ስም ብሔራዊ ስሜት ለመገንባት የሞከሩት ባለፉት ሰባ ዓመታት ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያ ተብላ የኖረችው ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ነው:: እንደዘመኑ ኢትዮጵያዊነት የተለየ ትርጉም: የተለየ አስተዳደር ይኑረው እንጂ : ኢትዮጵያዊነት የኖረ: የነበረ: ስሜትና ዜግነት ነው ::ይህም የሆነው በመደመራችን ነው :: ዛሬ አዲሱ ትውልድ በተለያዩ ርዕዮተ አለሞች ተደናግሮ; ጥቂቶች ባራመዱት የግራ አስተሳሰብ:አገርና ብሔርን ለያይቶ በመመልከት ሕዝብን ለመከፋፈል ሲሞከር በመደመር ፋንታ ተቀነስን ::

በእኔ የውትድርና ዘመን የምናውቀው መደመር ብቻ ነበር :: ቁዋንቃ ባህል ሀይማኖት ሳይከፋፍለን እንደ እንደ ሰው ባህርይ ጉድለቶች ብናሳይም በአገር ጉዳይ ላይ ግን ሁል ጊዜ እንደተደመርን ነበር ::

የኤርትራ መገንጠልእንቅስቃሴ ሲወለድ መቀነስ ጀመርን :: በመቀነሳችን ምክንያት ብዙ ሕዝብ አለቀ: ሰላም አጣን: ኢትዮጵያ አካሏ ጎደለ:: መደመርን አውግዘው መቀነስን ለመረጡ ለነሱም አልበጀም:; የመደመርን አስተሳሰብ በጥሞናና በሰላም ያላራመደ ህዝብ ወደጦርነት ይሄዳል:: የሚደመረው በሀይል ሳይሆን በፍቅር , በውይይት በመቻቻል መሆኑን መረዳት የተሳነው የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትቀነስ ሁኔታውን አመቻቸ:: በመደመር የማያምነው እንደውም መቀነስን ዓላማው አድርጎ የመጣው የወያኔ መንግስት አገርን ከማስገንጠል አልፎ ሌላው ኢትዮጵያ ከድምር በታች ሆኖ ተከፋፍሎ እንዲኖር የአገዛዙ ፖሊሲ አደረገ :: ኢትዮጵያ በደቡባዊ እፍሪካ ሀገሮች የቅኝ አገዛዝ አስተዳር ያወጀው (Bantustanization) ባንቱስታናይዜሽን በውኃላም በደቡብ አፍሪካ የተገበረው የአፓርታይድ ፖሊሲ ዓይነት ኢትዮጵያ ታወጀባት:: ሕዝብ ተከለለ::

ወያኔ እራሱን ከሌላው ኢትዮጵያ ቀነሰ:: መደመር ለአገዛዙ አደገኛ ስለሆነ ጥቂቶች እንዲገዙ ሌሎች ደግሞ ተከፋፍለው ተገዥ እንዲሆኑ 27 ዓመት የመቀነስ ፖሊሲ ሲያራምድ ኖረ:: ለመግዛት እንዲያመች የአገራችን ታሪክ ጎደፈ: ተጣመመ: አዲስ ታሪክ ተፈጠረ ብዙ ሕዝብ ተሰቃየ: ታሠረ: ተገደለ: ተለያየ: አገሩን ለቆ በምድረ ሰሀራ , በሜዲቴራኔያን ባህር: በቀይ ባህር : በየመን: በአረብ አገሮች ምድረ በዳ: በሲናይ በረሀ አለቀ: ታረደ: ሰውነቱ እየተቀደደ ኩላሊት መነገጃ ሆነ ::

መደመር ሲዋረድ መቀነስ ሲነግስ ማንንም አልጠቀመም : ጥቂቶች የተጠቀሙ መስሏቸው ነበር:: መደመር ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊነት አሸነፈ:: በጠ/ሚ አብይ አማካኝነት የመደመር ታሪካችን እየታደሰ ነው:: ስንደመር የአድዋ ነብር: የመቅደላ አምበሳ ሆነን ዳር ድንበራችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እንኖራለን:: ስንደመር እንፋቀራል: ስንደመር ያለንን እንካፈላለን: ስንደመር እንከባበራለን: ስንደመር የቋንቋ: የሀይማኖት: የባህል ልዩነቶች የጥንካሬና የአንድነት ምንጮች እንጂ አይቀንሱንም:: ስለዚህ የጠ/ሚ አብይን መልዕክት በተግባር ለማዋል: ለአመራሩም ድጋፍ ለመስጠት መነጋገር መወያየት እንጀምር:: መደመር ሀይል ነው:: ሰሞኑን የሚወጣው ሕዝባዊ ሰልፍ የመደመር ተሀድሶ: የአንድነት ሀይል አሸናፊመሆኑን የሚያበስር ታላቅ ሰልፍና መልህክት ይሁን:: ስንደመር በማንም በምንም አንሸንፍም:: ሊቀንሱን, ሊያደክሙን: ሊበታትኑን: ሊያፋጁን የሚሞክሩ ሁሉ የታሪክ አተላዎች ሆነው ይቀራሉ:: መደመር ያሸንፋል::

LEAVE A REPLY