/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት በአዲስ አበባ የተጠራው ሰላማዊ ሰለፍ እውቅና ማግኘቱ ተገለጸ። በግለሰቦች ተነሳሽነት የፊታችን ቅዳሜ የተጠራው የድጋፍ ሰልፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እውቅና መስጠቱ ታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩም የድጋፍ ሰልፉ “መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማድረስ እያደረገ ያለውን ስራ ለመደገፍና ከጎኑ ለመቆም” በመሆኑ በመጭው ቅዳሜ ከጠዋቱ 4፡00 እስከ 7፡00 በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ እንዲካሄድ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ዛሬ በደብዳቤ አሳውቋል።የሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እስካሁን የወሰዷቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች እንዲገፉበት በመደገፍ እንዲሁም ከዚህ በስተጀርባ ሆነው በጠ/ሚኒስትሩ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለማደናቀፍ ያሰፈሰፉ ወገኖችን ለመቃወም በሚል ሰልፉ መጠራቱን አስተባባሪዎቹ ትናንት በኢሊሊ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል።
ይሁንና ለጠ/ሚንስትሩ የተጠራውን የደግፍ ሰልፉ የተቃወሙ ግለሰቦች መኖራቸውንም በማህበራዊ ሚዲያ ተመልክተናል።