የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን /ethiopian tv/...

የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን /ethiopian tv/ መግለጫ ሰጡ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ዶክተር ታደሰ ብሩ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን(ኢቲቪ) በስልክ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ድርጅታቸው አርበኞች ግንቦት 7 ለዶክተር አብይና ቡድናቸው ድጋፍ እንዳለው ገልጸዋል።

ዶክተር ታደሰ ብሩ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና ቡድናቸው የሚያደርጉትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉና ድርጅታቸው አርበኞች ግንቦት ሰባትም ከጎናቸው እንደሚቆም በቃለ-ምልልሳቸው አረጋግጠዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሰኞ በፓርላማ ተገኝተው ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ጨምሮ ከዚያ ቀደምም ያደረጓቸውን ንግግሮች በቀናነት እንደሚያዩት ጨምረው ተናግረዋል።በዶክተር አብይና በእሳቸው ድርጅት(አርበኞች ግንቦት 7) ተመሳሳይ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳለም ጠቁመዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ትናንት ባወጣው መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረበውን የሰላም ጥሪ እንደሚቀበልና ለተግባራዊነቱም የበኩሉን እንደሚወጣ መግለፁ የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል “በሽብርተኝነት” ለተከሰሱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምህረት እንዲደረግላቸው የሚፈቅድ አዋጅ ሊወጣ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዕረፍት ከመበተኑ በፊትም  የምህረት አዋጁን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለኢቲቪ ዛሬ እንደገለጹት በሚንስትሮች ምክርቤት ተመክሮበት ወደ ፓርላማው የተላከው ረቂቅ አዋጅ በቀጣዮቹ  ቀናት በፓርላማ ይፀድቃል ብለው እንደሚጠብቁና  እሱን ተከትሎ ተቋማቸው አዲስ አዋጅ እንደሚያዘጋጅ ገልፀዋል።

አዲስ የሚዘጋጀው ይህ አዋጅ ተጠርጥረው በምርመራ ሂደት ያሉ ክስ የተመሰረተባቸው እንዲሁም የቅጣት ውሳኔ ለተላለፈባቸው ምህረት ማድረግንም ይመለከታል ብለዋል፡፡እንዲህ አይነት ህግ መዘጋጀቱ በሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጐት እያሳዩ ያሉና በፓርለማው በሽብርተኝነት  የተፈረጁ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰለማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ሲሉ ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ለኢቲቪ ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደ አርበኞች ግንቦት 7፣ኦነግና ኦብነግ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በአሸባሪነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY