ሰበር ዜና፡ አርበኞች ግንቦት 7 የትጥቅ ትግሉን ማቆሙን አስታወቀ

ሰበር ዜና፡ አርበኞች ግንቦት 7 የትጥቅ ትግሉን ማቆሙን አስታወቀ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛዉም አካባቢ የሚገኙ ታጋዮቻቸው  ከማናቸውም የአመፅ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ድርጅቱ ትዕዛዝም አስተላልፏል።

የድርጅቱ ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ተያይዟል።

———-

በሃገራችን የዲሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት ተገደን የገባንበትን ማንኛውንም ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ገተናል። ልዩ መግለጫ

 የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት በርካታ አመታት ከአፈና አገዛዝ ለመላቀቅና ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለመሸጋገር እልህ አስጨራሽ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝባችን ትግል የወለደውና በኢህአዴግ ውስጥ ታፍኖ ይኖር የነበረው የለውጥ ሃይል ይህንን ትግል ተቀላቅሎ በዋነኛነት ትግሉን የመምራት ሃላፊነት እየተወጣ ነው። ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ከትናንት በስቲያ ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓም ባወጣው መግለጫ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብና ይህን ለውጥ ከሚመራው ወገን ጎን እንደሚቆም በማያሻማ ቃላት ግልጽ አድርጓል።

መግለጫችን ደጋግሞ ለማስረዳት እንደሞከረው አርበኞች ግንቦት 7 ከማናቸውም አመጾች ነፃ የሆነ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ትግል ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሊወስደን የሚችል አስተማማኝ የትግል ስልት መሆኑን አስገንዝቧል። በሃገራችን የአመጽ ትግል አስፈላጊነት የመነጨው ራስን ከአሸባሪው የወያኔ አገዛዝ ለመከላከል ሲባል ብቻ የተወሰደ አማራጭ ያልነበረው መፍትሄ በመሆኑ ነበር ።

ኢህአዴግ ውስጥ የተነሳውና በጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል እየወሰደ ባለው እጅግ አበረታች እንቅስቃሴ የሃገራችንን ፖለቲካ ከአመጽ ነጻ በሆነ ሰላማዊ እና ስልጡን ፖለቲካ ከግብ ማድረስ እንደሚቻል ተስፋ ስለፈነጠቀ፤ እየታየ ያለውን አበረታች እንቅስቃሴ ለማገዝ ሰኔ 8 እና 9 ልዩ ስብሰባውን ያካሄደው የንቅናቄያችን ሥራ አስፈጻሚ ወቅታዊውን ሁኔታ ከገመገመ ቦኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፎአል።

ከዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ አርበኞች ግንቦት 7 በማናቸውም መልኩ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ምንም አይነት አመጽ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ ታቅቧል። በዚህ ውሳኔ መሠረት ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛዉም አካባቢ የሚገኙ የነጻነት ታጋዮቻችን ከማናቸውም የአመጽ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ድርጅታዊ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል። ይህ እርምጃ በኢህአደግ ውስጥ ያሉ ቀልባሽ ሀይሎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የሚያደርጉትን የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎች ለማምከን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ጥንቃቄ ግምት ውስጥ ያስገባና ፤ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ገጽታውን ይዞ እንዲሄድ ለማበረታታት የታለመ በራስ ተነሳሽነት የተወሰደ ውሳኔ ነው።

አንድነት ኃይል ነው!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ

ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓም

LEAVE A REPLY