በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 165 መድረሱ ታወቀ

በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 165 መድረሱ ታወቀ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ለመደገፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የቦንብ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ስድስት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን  ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

አዲሱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ዘይኑ ጀማል እንደገለፁት እስካሁን የሞተ ሰው አንድ ሲሆን 165 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል። ከእነዚህ ውሰጥም 15 የሚሆኑት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል። የዛሬውን የቦንብ ጥቃት ተከትሎም የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉን መረጃዎች ወጥተዋል።

የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶክተር አሚር አማን፣ በዛሬው ፍንዳታ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሆስፒታሎች እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ፍንዳታው ከተፈፀመ ጥቂት ደቂቃ በሗላ በቤተ-መንግስት በሰጡት መግለጫ፤ ሰልፉ የተቋረጠዉ ሰላምን በሚያደፈርሱ ሰላም ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከፋፈል በተጠና እና ሞያን ታግዘዉ የሰዉ ህይወት ሊቀጥፉ፤ ደም ለማፍሰስ ባቀዱ ሀይሎች  የተፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል። ለጠፋዉ  የሰው ህይወት ማዘናቸውን ገልፀው ለተጎዱ ወገኖችም በቶሎ ማገገምን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጲያ ህዝብ የጀመረዉን ልበ ሰፊነት በትናንሽ ነገሮች ሊያጣ እንደማይገባም ጠቅላይ ሚኒስተሩ አሳስበዋል፡፡ ጉዳዩ እንዴትና በማን እንደተፈፀመ በፖሊስ እየተጣራ በመሆኑ የምርመራውን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚያረጉም በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጀመሯቸውን የለውጥ ተግባራት ለመደገፍ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በደሴ፣ጎንደር ፣ደ/ማርቆስና ሌሎች ከተሞችም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። ነገም በድሬዳዋ ከተማ እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

LEAVE A REPLY