በ2008 ዓም ባህርዳር ላይ በተደረገው ሰልፍ መጀመርያ የጠራው ሰማያዊ ፓርቲ ነበር። ከመሸም ቢሆን ሰማያዊ ፓርቲ “ትቸዋለሁ” ሲል ብአዴን ኃላፊነቱን ለሰማያዊ ፓርቲ ሰጠ። ብአዴን ሰማያዊ “የለሁበትም” ብሎም ሀላፊነቱን የሰጠበት ዋነኛው ምክንያት የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ አቅም ስለሌለው ነው። ብአዴን መቀመጫው በሆነው ባህርዳር እንኳን የማዘዝ አቅም የለውም። ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ፍላጎትም የለውም።
በመሰረቱ አንድ ሰልፍ እውቅና ከማግኘቱ በፊት የሰልፈኛውን ደህንነት የመጠበቅ አቅምና ሁኔታ ይመዘናል። መንግስት የሰልፈኛውን ደህንነት የመጠበቅ አቅም ወይም ሁኔታ ከሌላው እውቅና አይሰጥም። እውቅና ከሰጠ ደግሞ የሰልፈኛውን ደህንነት ለመጠበቅ የፖሊስና የደህንነት ሀይል የመመደብ ግዴታ አለበት። ምክንያቱም መንግስት ሌሎች አካላት ባስተባበሩት ሰልፍም የዜጎቹን መብት የማስጠበቅ ቀዳሚው ግዴታ አለበት። የሰልፍ አስተባባሪዎች ሰልፉ ላይ የሚነሱትን ጉዳዮች ከመወሰን እና ለፖሊስ ድጋፍ ከማድረግ ውጭ በሰልፈኛው ላይ የሚደርስን ወይንም ሰልፈኛው ሊወስደው የሚችለውን ከአቅም በላይ የሆነ ነገርም መንግስት ሰልፈኛውን ወይንም ሌላውን ህዝብ ከሰልፈኛ ሊከላከል የሚችለውን ያህል የመከላከል አቅም የለውም። ይህ ሀላፊነት የመንግስት ነው።
አቅመ ቢሱ ብአዴን ግን ባለፈው ባህርዳር ላይ የተፈፀመውን ለሰማያዊ ፓርቲ አሳልፎ ሰጠ። ዜጎችን ከአደጋ የመከላከል ግዴታን ይህን ግዴታ መወጣት ለማይችል የሰልፍ አስተባባሪ ሰጠ ማለት ምንም ይከሰት ምን አያገባኝም ማለቱ ነው።
ብአዴን ሰኔ 24 የሚደረገውን ሰልፍም አስተባባሪ ኮሚቴው ኃላፊነቱን እንዲወስድ በግልፅ የእውቅና ደብዳቤው ላይ አስፍሯል። ይህ የአስተዳደሩ ደብዳቤ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ምንም ይከሰት ምን “አያገባንም” እንደማለት ነው።
ሰልፉ ብአዴን እደፍፈዋለሁ የሚለውን አብይ ለመደገፍም ጭምር ነው። የሚደረገው ዋና ከተማው ባህርዳር ላይ ነው። የዜጎችን ደህንነት የማስከበር መብት አለበት። በመሆኑም ግዴታውን በሙሉ ለአስተባባሪው ሊሰጥ አይገባም። ብአዴን ይህ የሚያደርገው ከየትኛውም ተጠያቂነት ለማምለጥ ብቻ አይደለም። ባህርዳርንም መቆጣጠር አቅም፣ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን ለመወጣት ፍላጎት የሌለው ግድ የለሽ ስለሆነ ነው። እንዲያውም አስተዳደሩ ግዴታውን ለአስተባባሪዎች ብቻ ማሸከሙን ስናይ በሰልፈኛው ላይ ምን አይነት ሴራ ቢወጠን ነው ብለን እንድንጠረጥር ያደርገናል።
በመሆኑም ይህ ሰልፍ መካሄድ ካለበት ብአዴን ሁሉን ግዴታ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ አቅም ለሌለው አስተባባሪ መስጠቱን አቁሞ የሚጠበቅበትን ሰልፈኛውንና ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታ መውሰድ ይኖርበታል። ይህ ደብዳቤው ላይም መስተካከል ይኖርበታል! ስለ ባህርዳሩ ሰልፍ ስናስብ ከባለፈው የአዲስ አበባ ሰልፍ ብቻ ሳይሆን ከሁለት አመት በፊት ብአዴን ግዴታውን ለሰልፉ አስተባባሪ በሰጠበትና ባህዳር ካዘነችበት ሰልፍም መማር ይኖርብናል! አስተባባሪ ኮሚቴው ሰልፈኛውንም ሆነ የከተማውን ሕዝብ መጠበቅ የሚያስችልበት ደህንነትና ፖሊስ የለውም! የተፈለገው የሕዝብ ደህንነትን ለመጠበቅ ግዴታን ላለመውሰድ ነው!