መጀመሪያ እንኳን እግዚአብሔር አተረፈን ልበል።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጀግንነት ከማድነቅ አልፈን በምንደሰትበት ጊዜ አንዳንድ ሰዎች “አትቸኩሉ” እያሉ ይመክሩናል። ደስታ ለነገ አይከተትም። ግዴታችን የዛሬውን ደስታ የሰጠንን አምላክ ነገም እንዲያስደስተን መለመን ነው። የዚህን ሰሞን የኳስ ጨዋታ እንደኔ የምትከታተሉ እንደምታውቁት፥ አንድ ቡድን ኳስ ባገባ ቁጥር የደጋፊዎቹ የደስታ ድምፅና ጭፈራ ጫወታው እስኪያልቅና ድሉ እስኪገኝ አይታመቁም፤ ጎል በገባ ቍጥር የደስታው ጫጫታ ጆሮ ያደነቍራል። አዝማሚያው ግልጽ እየሆነ፥ ድሉም እየታየ ሲሄድማ፥ ደስታው የሚገለጸው ዕብድ በሚያስብል ሁኔታ ነው። ዶክተር ዐቢይ የተነፈግናቸውን መብቶች በለውጥ ስም አንድ ባንድ ሲመልስልን፥ በየአንዳንዱ እንደሰታለን።
የሚያመጣው ለውጥ ትልቅ እንደሚሆንም ምልክት እያየን ነው፤ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ሲያስለቅሱን የነበሩ ሰዎች ያለቅሳሉ። እንዲደግፋቸው በግርፊያ ያስገድዱት የነበረውን የትግራይ ሕዝብ (“ፋሺዝም እትግራይ ውስጥ” ተብሎ ነበር እኮ) ዛሬ በፈቃዱ ኢትዮጵያን ከድቶ እነሱን እንዲደግፋቸው መማፀን ጀምረዋል። እስከ ዛሬ መኖሩን እንኳ የማያውቁትን አምላክም ሲለምኑ እናያለን። ይህ ሁሉ ሲደርስ በማየታችን ደስታ ይገባናል፤ ግን የምንደሰተው በጠላት መሸነፍ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ድል በመገኘቱ ነው። የኢትዮጵያ ድል የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድል ነው።
የኢትዮጵያ ድል የትግራይ ሕዝብም ድል ነው። ዶክተር ዐቢይ ጥፋቱ ሁሉ የሕወሐት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ከደሙ ንጹሕ ነው ሲል፥ የትግራይን ሕዝብ ሳይወቅስ፥ ወያኔዎች ኢትዮጵያን ሳያጠፏት የለማ መገርሳ ቡድን እንደደረሰባቸው አረጋገጠልን። ኢትዮጵያን ለማዳን አምላክ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኦሮሞዎችና በአማሮች (አልፋና ኦሜጋን) ሲያስተባብር ዛሬ የመጀመሪያው አይደለም። በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ከአፄ ሠርፀ ድንግል ጋር ቱርክን ከዛሬዋ ኤርትራ ሲያባርሩ፥ በቅርብ ጊዜ ደግሞ፥ ከምኒልክ ጋር ሆነው የተበታተነች ኢትዮጵያን ሲሰበስቡ በታሪክ አብረናቸው ነበርን።
አሁን እንኳን የተነሣሁት፥ ዶክተር ዐቢይ፥ “ብዙዎች ከርስታቸው የተፈናቀሉት በጥላቻ ነው” ሲል ስለሰማሁት፥ ጥላቻ የበሽታው ምልክት እንጂ በሽታው ሌላ መሆኑንና እንደ ዶክተርነቱ ለበሽታው መድኃኒት እንዲፈልግለት ለማሳሰብ ነው።
ከሥሩ እንጀምርና፥ በዓሥራ አራት የአስተዳደር ጠቅላይ ግዛት የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያን ኢሕአዴግ (ሕወሐት ማለት ይሻል ይሆናል) ከዓሥራ አራቱ አንዱን ቆርጦ በእንጥልጥል ጥሎ፥ የቀረውን አገር በዘጠኝ ክልል መከለሉን በሕገ መንግሥቱ ዐወጀ። እንደማየው አከፋፈሉና የክፍሎቹ ስያሜ አሻሚዎች ናቸው። ማለት፥ እነዚህ ክልሎች የተከለሉትና የተሰየሙት ለምን እንደሆነ ሕዝቡ የገባውና መንግሥት የሚለው የተለያየ ነው። ሕገ መንግሥቱ ክልሎችን ራስ-ገዝ የአስተዳደር ክፍሎች ያደርጋቸዋል። እንግሊዝኛው States ይላቸዋል።ሐሳቡ Federally United States of Ethiopia ለማለት የተፀነሰ ይመስላል። ሕዝቡ ግን በክልሎቹ ውስጥ የሚኖረው የትልቁ ነገድ የግል ንብረት አድርጎ ወስዶታል። እንዲያውም የጋምቤላን ክልል ሲተረጐም ክልላቸውን የጋምቤሎች የግል ንብረታቸው እንደሚያደርግ ከኔ በፊት ሁለት ጸሐፊዎች አሳይተዋል።
ክልሎች የተፈጠሩት፥ ስማቸው እንደሚያመለክተው፥ የትልቁ ነገድ የግል ንብረት ከሆኑ፥ ሌሎቹን “ውጡልን፥ድምበራችን ተገፋ” ቢሉ አይፈረድባቸውም። ትልቁ ደኻ ትንሹን ደኻ የሚያሳድደው “ለኔ የተሰጠውን ክልል ልቀቅልን” እያለ ነው። እንደ ሲዳማ፥ እንደ ጉራጌ ያሉ ነገዶችም የየራሳችን ቦታ ተከልሎ ይሰጠን የሚሉት፥ “እናታችን ስትዘረፍ እኛ ለምን አንዘርፍም? ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት አይደለችም ወይ?” ብለው ነው። የሚሰጣቸው መልስ፥ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳለው፥ “አዎን፥ እውነታችሁን ነው፤ ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች” መሆን አለበት።
ግን አማሮች ሲባረሩ የሆነውን እንመልከት፤ ለአማሮች ብቻ የተሰጠ የግል ክልል ያለ ይመስል፥ በስማቸው ባልተጠራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ አማሮችን፥ “ወደ ክልላችሁ ሂዱ” አሏቸው። ሕገ መንግሥቱን አርቃቂዎችን የምጠይቀው፥ “የቱ ነው ለአማሮች በግል የተሰጠው ክልል?” እርግጥ፥ ጥንት “አምሐራ” የሚባል ክፍለ ሀገር ነበረ። ግን ክፍለ ሀገሩ የተመሠረተው በቤተሰብ እንጂ፥ በቋንቋ ላይ አልነበረም። የተመሠረተው በቋንቋ ላይ ቢሆን ኖሮ፥ የጥንቱ አምሐራ ክፍለ ሀገር አማርኛ የተንሰራፈፈባቸውን ጎንደርንና ጎጃምን ይጨምር ነበር፤ አልጨመረም። ጎንደር፥ ጎጃም፥ አምሐራ ከጥንት ጀምሮ ራሳቸውን የቻሉ ሦስት ክፍለ ሀገሮች ነበሩ።
“አማራ የሚባል ነገድ አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ ተነሥቶ የነበረው፥ ሕዝባችንን በቋንቋ መከፋፈል ስለተጀመረና አማርኛ የሚናገረውን ሁሉ (ጎጃምን፥ ጎንደርን፥ ሰሜን ሸዋን ሳይቀር) አማራ/አምሐራ ማለት ያመጣ ብን ጣጣ ነው እንጂ፥ የዛሬውም ሆነ የጥንቱ አማራ ጎሳው ኢትዮጵያዊነት ነው፤ ክልሉም ኢትዮጵያ ነች። ሌሎቹን ጎሳ-ተከል ኢትዮጵያውያንን እንደ አማራ እንዲያስቡ (ጎሳችን ኢትዮጵያዊነት ነው፤ ክልላችንም ኢትዮጵያ ነች እንዲሉ) በመጥራት ፈንታ፥ አማሮቹን እንደ ጎሳዎች እንዲያስቡ (ጎሳችን አማራነት ነው፤ ክልላችንም ተከልሎ የተሰጠን ቦታ ነው) እንዲሉ አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጠረባቸው። እገሌ ከእገሌ ሳይል፥ በሥልጣኔ ከጎሰኝነት አስተሳሰብ ነፃ የወጣውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወደ ኋላ-ቀሮቹ የሚስብ ኀይል መጣበት።
ክልሎች ለጎሳዎች ኢትዮጵያ እንደቅርጫ ተከፋፍላ የተሰጠች ከሆነ ግን፥ ክልል ሌልው ስሙ “ክልክል” ነው። ክልል የሌላቸው ጎሳዎች በገዛ አገራቸው አገር- አልባ ሆኑ። የታሰበው ይህ ከሆነ፥ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ፥ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው” የሚለው አንቀጽ፥ “ለባይተዋር የሚሰጥ መስተንግዶ አይነፈጋችሁም፤ በፍቅር ትስተናገዳላችሁ” ከማለት ያለፈ ዋጋ የለውም።
ከዶክተር ዐቢይና ከቅዱስ ዳዊት ጋራ “ጽድቅ ወሰላም ተሳዐማ” (እውነትና ሰላም ተቃቅፈው ተሳስመው)፥ ጥላቻ የሚወገደው ሕገ መንግሥቱን በማያሻማ ቋንቋ በመጻፍ እና ለአስተዳደር ክፍሎች የማያሻማ ስም በመስጠት ብቻ ነው። ጎሳዎችን ለማስደሰት የተጫረውን እሳት ክልል በሚባል ቤንዚን ማጥፋት አባባሰው እንጂ፥ አላጠፋውም። ደጋግሜ እንደጻፍኩት፥ የተሻለው ወደ ጥንቱ ታሪካዊ አውራጃዎች መመለስ ነው። ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት መሆኗን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አረጋግጦልናል። አገር ከፍሎ ለመያዝ የሚያስችል የጎሳ ወይም የቡድን መብት የሚባል ነገር በየትም አገር የለም። እንደዱሮው አብረን በአንድ ሌማት እንብላ፤ በሳህን ማካፈሉ ባህላችን አይደለም።
ጉዳዩ በአካባቢው ነዋሪዎችና ሽማግሌዎች እንደሚጠና ሰምተናል። መልካም ዜና ነው። ግን፥ ጉዳዩ የሽምግልና ብቻ አይደለም፤ በሕግ ላይ የተመሠረተ ለውጥ ያስፈልገዋል። ዶክተር ዐቢይ ብቻውን ይኸን ማድረግ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ማንሣትና ሐሳቡን ለፓርላማ ማቅረብ ግን ይችላል። ፓርላማው ሕገ መንግሥቱን ማረም ይችላል። ሐሳቡን ምፅ ብልጫ ውድቅ ካደረገው፥ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ማቸነፊያ ይሆናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን፤ በቅርቡ አሜሪካ እንደምትመጣ በሰፊው ይወራል። ሕዝብህ የሚወደውን የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለብን፥ “ሐዊሳ በምጽአትከ” (በደኅና አምጥቶ በደኅና ይመልስህ) እንላለን። ባንዲራችንን ስትመርቅልን ለመስማትና ለማየትም በመጓጓት ላይ ነን። እስካሁን የጠበቀህ የኢትዮጵያ አምላክ ሁል ጊዜም ይጠብቅህ። አንተም እርዳው።