የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ከሀላፊነታቸው ሊነሱ ነው ተባለ
/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆነው እየሰሩ ያሉት አቶ ደሴ ዳልጌ ከሀላፊነታቸው ሊነሱ መሆኑ ተገለጸ። በምትካቸውም ትናንት ማክሰኞ የደኢህዴን(ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ም/ሊ/መንበር በመሆን የተሾሙት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንደሚሾሙ ሪፖርተር ዘግቧል።
ደኢህዴን በአሁኑ ወቅት ከወረዳ እስከ ላይ የደረሰ የአመራር ለውጥ እያካሄደ ሲሆን በወንጀል የተጨማለቁትን እነ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሲራጅ ፈጌሳና ሌሎች በርካታ ሀላፊዎችን እያባረረ ይገኛል። አቶ ደሴ ዳልጌም ሰሞኑን በክልሉ ከተነሳው የርስ በርስ ግጭት ጋር ተያይዞ ስሙ ተደጋግሞ እየተነሳ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወላይታ፣ ሲዳማና ጉራጌ ዞን አመራሮችን በራሳቸው ፈቃድ የሀላፊነት ቦታቸውን እንዲለቁ በጠየቁት መሰረት የወላይታና ጉራጌ ዞን አመራሮች ለመልቀቅ መስማማታቸውን ባለፈው ሳምንት በደብዳቤ አሳውቀዋል። ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ይጠበቃል።
በአዲስ አበባ የሚገኘውን የደኢህዴን ጽ/ቤት ወደ ሀዋሳ ከተማ እንዲዛወር መወሰኑም ታውቋል። ባለፈው ሰኞ የደኢህዴን ሊ/መንበር የነበሩት አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ተነስተው በወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል (የፓርላማ አፈ-ጉባኤ) መተካታቸው የሚታወስ ሲሆን የደኢህዴን ጽ/ቤት ወደ ሀዋሳ ከተማ ከተዘዋወረ ከአፈ_ጉባኤ ሀላፊነታቸው እንደሚለቁም ተጠቁሟል።