እስር ቤቶችና የስቃይ ሰቆቃዎች /ማህሌት ፋንታሁን-ከአዲስ አበባ/

እስር ቤቶችና የስቃይ ሰቆቃዎች /ማህሌት ፋንታሁን-ከአዲስ አበባ/

የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ እና ማረፊያ ቤት ሃላፊ ገ/እየሱስ ገ/ርን ዛሬ ኢቲቪ በ7 ሰአት ዜና ስለ እስረኞች አያያዝ ጠይቀዋቸው በእስረኞች ላይ ምንም አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደማይደርስባቸው ሲገልፁ ሰማሁ። በአንፃሩ እስረኞቹ ግን በማረሚያ ቤት ሆነው ስለሚደርስባቸውን የተለያዩ በደሎች (ድብደባ፣ ጨለማ ክፍል መግባት፣ ህክምና መከልከል፣ ከቤተሰብ እንዳይገናኙ መከልከል፣ ንፅህናው ያልተጠበቀ ክፍል እንዲኖሩ ማድረግ…) ለኢቲቪ ተናግረዋል። እስረኞቹ በማረሚያ ቤቱ የሚደርስባቸውን ኢ ሰብአዊ የሆነ ድርጊት ከተናገሩ በኋላ “ለናንተ በመናገራችን ራሱ ሚጠብቀን ምን እንደሆነ አናውቅም። ይደበድቡናል። ከዚህ የበለጠ ምንም አይመጣም። ብንሞትም እንሙት” ብለው ወስነው የተናገሩ መሆኑን ገልፀዋል። ሃላፊው ግን ይሄን ሁሉ ክደዋል። የማረሚያ ቤት ሃለፊዎች የሃሰት ምላሽ በመስጠት ተክነውበታል።

ሰኔ 14/2010 በእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ ክሳቸው ያልተቋረጡ ተከሳሾች የአቃቤህግ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘ ቀጠሮ ነበረ። በመዝገቡ 2ኛ ተከሳሽ የሆነው ዘመነ ጌጤ ከማረሚያ ቤት አልቀረበም። ከማረሚያ ቤቱ የችሎቱን ጉዳይ የምታስፈፅመው ሰርጀንት ዘመነ ጌጤን ክፍሉ ሄዳ አይታው እንደነበረ እና በህመም ምክንያት ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳልቻለ በቃል ተናግራለች። አቃቤ ህግም ጉዳይ አስፈፃሚዋ በቃል የተናገረችው ነገር ተቀባይነት እንደማይኖረው እና ተከሳሹ ታሟል ከተባለ የህክምና ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል ሲል ያቀረበውን ሃሳብ ዳኞች ተቀብለውት ተከሳሹ ዛሬ ፍርድ ቤት ያልቀረበበትን ምክንያት ማረሚያ ቤቱ ህጋዊ ማስረጃ በአዳሪ ይዞ እንዲቀርብ፤ ተከሳሹንም እንዲቀርብ አዘዙ። በነጋታውም ዘመነ ጌጤ ከማረሚያ ቤት አልቀረበም ነበር። በችሎቱ ቀርቦ የነበረው ሌላ ጉዳይ አስፈፃሚ ሲሆን በዋና ሱፐር ኢንተንደንት ገብረ እ/ር ገ/ሃዋርያት የተፃፈ ደብዳቤ ለዳኞች ያቀረበ ሲሆን፤ ዘመነ ጌጤ ሆዱን በመታመሙ ምክንያት ችሎት መምጣት እንደማይችል እና እንደተሻለው ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡት ደብዳቤው ይገልፃል። የዘመነ ጌጤ ጠበቃ የሆነው አዲሱ ጌታነህ (Addisu Getaneh) ከዘመነ ጌጤ ጋር አንድ ክፍል የሚኖር ሌላ እስረኛ በችሎቱ ስለሚገኝ እሱ የሚያቀውን እንዲያስረዳ ጠይቆ በዳኞች ፈቃድ እስረኛው የሚከተለውን ተናግሯል። “እናንተ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ማእከላዊ ተደብድቤአለው ሲል ምንም ሳትሉት ቀራችሁ። አሁን ልጁ ማእከላዊ በደረሰበት ድብደባ መንጋጋውን ኦፕራሲዮን ሆኗል። ምግብ እንኳን የሚበላው ፈሳሽ ብቻ ነው። ዛሬም ያልመጣው ሆስፒታል ሄዶ ነው።

የካቲት 12 ሆስፒታል ሄዷል።” ጉዳይ አስፈፃሚውም ዘመነ ጌጤ የካቲት 12 ሆስፒታል መሄዱ እውነት መሆኑን መስክሯል። አቃቤ ህግ ተከሳሹ በትላንትናው እለት ለምን እንዳልቀረበ እንጂ ዛሬ ለምን እንዳልቀረበ የሚገልፅ ህጋዊ ማስረጃ ባለመቅረቡ የሚመለከተውን አካል ቆንጠጥ በሚያደርግ መልኩ ትእዛዝ እንዲሰጥለት ዳኞችን ጠይቋል። ዳኞችም ጉዳይ አስፈፃሚውን/ዎችን በቀጥታ የሚያዙትን/የሚያሰማሩ እና የሚከታተሉትን ሃላፊዎች ስም ተቀብለው ትእዛዝ ለመስጠት እየተነጋገሩ እያለ በመሃል ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው የእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ ለህዝብ እና መንግስት ጥቅም ሲባል መቋረጡን ጠቅላይ አቃቤ ህግ የገለፀበት መሆኑን ነገሩን። ክሱ በመቋረጡ ተከሳሾች ከእስር እንዲፈቱ አዘው ብቻ ችሎቱ አበቃ። የማረሚያ ቤት ሃለፊዎቹም ጉዳይ ምንም ሳይባል ታለፈ።

የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ጭካኔ በቃላት ተገልፆ የሚያልቅ አይደለም። የሚፈሩትም ሆነ የሚታዘዙት አካል የለም። በአብዛኛው ፍርድ ቤትን ትእዛዝ አያከብሩም። እንዲያውም “ዳኛ ምንም አያመጣም” ይሉናል እያሉ ተከሳሾች ለዳኞች ሲናገሩ ብዙ ጊዜ ሰምቼ አውቃለው። ተከሳሾች ለሚያቀርቡት አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጡ ሲታዘዙ ከእውነታው የራቀ ምላሽ ነው ሚሰጡት። ዳኞችም ከማስጠንቀቂያ እና ምክር ባለፈ ሲቀጧቸው አጋጥሞኝ አያውቅም። በእነ ጉርሜሳ አያኖ ስር ያሉ ተከሳሾች ለከሰአት ሲቀጠሩ ዳኞች ከቤተሰቦቻቸው የሚቀርብላቸውን ምሳ እንዲበሉ ትእዛዝ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ግን በራሳቸው ስልጣን የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሽረው ምሳ ሳያበሏቸው ለከሰአት ችሎት ማቅረባቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በሌሎችም መዝገቦች ተመሳሳይ የፍርድ ቤት ትእዛዝ አለማክበር እና የውሸት ምላሾች ትንሽ የሚባሉ አይደለም።

ኢቲቪ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች እየሄደ እስረኞችን እየጠየቀ እስረኞች የሚደርስባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በዜና መልክ ማቅረቡ መልካም ሆኖ ሳለ ፕሮግራም ይዘው ሰፋ ያለ ሰአት ወስደው ዘርዘር ባለ መልኩ ቢያቀርቡት ደግሞ ይበልጥ ችግሩን አጉልቶ ማሳየት ይቻላል ብዬ አስባለው።

LEAVE A REPLY