ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ

ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በአገሪቱ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ለኢቢሲ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሰኔ 16/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ እውቅና ለመስጠት፣አገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለመደገፍ በወጣው ህዝብ ላይ ቦምብ ተወርውሯል፣ ሂደቱ እንዲስተጓጎልም ተደርጓል፡፡

 ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ቦምብ ከመወርወር ጀምሮ ሂደቱ እንዲስተጓጎል በወቅቱ መብራትና የቴሌኮም ኔትወርክ ማጥፋት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር በተደራጀ አኳኋን በመስራት የኑሮ ውድነትን እንዲባባስ እና የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ተቋማት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉንም ጽ/ቤቱ አመልክቷል፡፡

እነዚህን ህገወጥ ተግባራት አጣርቶ ለህግ የሚያቀርብ ከተለያዩ አካላት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ፅ/ቤቱ ገልጿል፡፡

ለተልዕኮው ስኬታማነትም መላው ሰላም ወዳድ ህዝብ ከኮሚቴው ጎን በመቆም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግና አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እንዲተባበር ተጠይቋል ሲል ኢቲቪ ዘግቧል።

ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ጽ/ቤቱ አመልክቷል፡፡

LEAVE A REPLY