/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ባለፉት ሦስት ቀናት በተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ዘገበ። ግጭቱን ያነሳሱ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል።
ግጭቱን ያስነሱትም በገንዘብ የተገዙ መሆናቸውን ኢቲቪ ጨምሮ ዘግቧል።
ከአይን እማኞች ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በአሶሳ ከተማ ትናንትና ከትናንት በፊት የነበረውን ግጭት ያስነሱት በመከላከያ ኦራል መኪና ከገጠር ተጭነው የመጡ በርካታ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።ግጭቱም “በርታ” የሚባለው ማህበረሰብ የኦሮሞና አማራ ተወላጆችን ከክልላችን ውጡ በሚል መሆኑ ታውቋል።የበርታ ማህበረሰብ ወጣቶች ዱላና ገጀራ በመያዝ ያገኙትን ሰው ሁሉ ጭካኔ ተሞላበት መልኩ እንደጨፈጨፉና ቤት ለቤት በመዞር የግለሰቦችን ንብረት መዝረፋቸውን ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
ኢቲቪ የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ ነው ይበል እንጂ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቂመው፤ እስከ 15 ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተከታተሉ ነው ብለዋል።
አሶሳ በአንፃራዊ መልኩ ዛሬ ጸጥታ እንደሰፈነባትም ታውቋል።