ይህን ፁሁፍ እንዳሰናዳ ገፊ-ምክንያቴ ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስተር ቦታውን ከያዘ ጀምሮ በርካታ “ጥበበኞች” ነን ባይ ነጋዴዎች የቤተ-መንግስቱን አጠር የሙጥኝ ብለው መዋል ማደር መጀመራቸው ሳያሳፍራችው፣ እራሳቸውን የሀገሪቱ ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች “ተወካይ” አድርገው በማቅረብ፣ ዛሬም እንደትላንቱ በአቋራጭ ትርፍ የሚያጋብሱበትን ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የሚያደርጉት መሽቀዳደም ያገጠጠ ሀቅ ሆኖ መታዘቤ ነው።
በኢትዮጵያችን ተፈጥረው ከነበሩ ደራሲያን፣ ገጣሚያን፣ መዚቀኞች፣ ተዋንያኖች… በዚህ ሞያ ውስጥ ኖረው ያለፉና አሁንም በአገልግሎት ላይ ያሉ ልባቸውን ከቤተ-መንግስት ይልቅ ከህዝብ ጋር አድርገው ሀገር የማዳን እና ትውልድ የመቅረፅ ስራ ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው።
ከነዚህ ጎን ለጎንም በየዘመኑ በአፋቸው “የጥበብ ባለቤትነን” እያሉ፣ በተግባር ግን የቤተ-ቤተመንግስት ፍርፋሪን አንደ ዶሮ አጎንብሰው ሲለቅሙ የከረሙ ነበሩ። ዛሬም አሉ። ሞያውን ትውልድን በዕውቀት፣ በሞራል፣ በአርበኝነት… ከሚቀርጽበት ምስጢራዊ-ኃይል ወደ ለየለት አሸርጋጅነት፣ ተላላኪነት፣ ተርታ-ካድሬነት…ለውጠው በአፋሽ አጎንባሽነታቸው እየታዘብን እዚህ ደርሰናል። ሙያውን ቢያረክሱም፣ ስብእናቸውን ቢያዘቅጡም ሀብት ማጋበሳቸውን ግን ልብ ይሏል።
ባለፉት 27 የአሳማዎች-ዓመታት ወዶ ገብ “አርቲስቶች” የወያኔ የጥበብ ክንፍ በመሆናቸው ብቻ ቲያትርና ሲኒማ ቤቶችን ለኦናነት መዳረጋቸው ሳያንስ፣ የዶክተር አብይን መመረጥ ተከትሎ በ’ሜታምርፎሲስ’ ቆዳቸውን ግልበጠው ለባለሟልነት ሲራወጡ እያየናቸው ነው። ትላንት ደደቢት በረሃ ድረስ ሄደው “እመበር ተጋዳላይ…”፣ “አጇይ፣አጇይ…” እንዳላሉ፤ የጫካውን ፕሮፓጋንዳ እንደ-ወረድ ወደ ፊልም ገልብጠው “ቀይ ስህተት…” እያሉ ጭቆናን እንዳላራዘሙ፤ ኢትዮጵያዊነትን እንዳልረጋገጡ… ዛሬ ደግሞ የለውጥ “ሀዋርያ” ከእኛ በላይ ላሳር ፊሽካን እየነፉ ነው።
ባህልና ቱሪዝም ሚኔስትር መ/ቤት ሰኔ 18/2010 ዓም ለተለያዩ የጥበብ ባለሙያዎች እየደወለ ሰኔ 20/ 2010 ዓም ‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥበብ ሞያተኞች ስልጠና ስለሚሰጡ የጥሪ ካርድ ውሰዱ’ እያለ ነበር። አስገራሚው ጉዳይ ይህ ጥሪ ከመደረጉ ከ15 ቀን በፊት ‘ማን ይጠራ ?’ ‘ማን አይጠራ?’ የሚለውን ሲያቦኩና ሲጋግሩ የሰነበቱት እነዚሁ የወያኔ የጥበብ ክንፍ ተጋዳላዮች መሆናቸው ነው። እነዚህ ሰዎች የባህል ቢሮ ሰራተኛ አይደሉም፤ በህግ የሚታወቅ የወከላቸውም አካል መኖሩንም አላውቅም። ይህ ብቻም አይደለም ለምን የሚያውቁትና የሚቀርቡትን ሰው ብቻ እየመረጡ “ተዘጋጁ” ብሎ በድብቅ መንገር እንደፈለጉም አላውቅም።
/በነገራችን ላይ ከ15 ቀን በፊት እነዚሁ ሰዎች ወደ “አላቲኖስ የፊልም ስራዎች ማህበር” ደውለው በፕሮግራሙ ላይ የምትወክሉትን 5 ሰዎች ላኩ ባሉት መሰረት፣ ማህበሩ ከሰጣቸው የወኪሎቹ ስም ዝርዝር መካከል “የሱን ተውት” በማለት የእኔ ስም ሰርዘው ማስቀረታቸው ቅር ባያሰኘኝም፣ አስገርሞኛል፤ ምክንያቱም የአብይን “የእንደመር” ጥሪ አዛብተው መረዳታቸው ገብቶኛልና ነው/
በተጨማሪ ትላንት የተበተነው ይፋዊ ደብዳቤ በባሀልና ቱሪዝም ሚኔስትር ስም ሲሆን፣ የመረጣ ጥሬው ሲከናውን የነበረው ግን ከቴውድሮስ ተሾመ ሴባስቶቦል ቢሮ ነበር። …እንዴት ነው ነገሩ አብይንም በሰፈር-ልጅነት ለመጥለፍ ታስቦ ነው? ወይስ ያልሰማነው ሹመት አለ? መቼም መለስ ዜናዊ እስከ አንገቱ የተዘፈቀበትን መንደርተኝነት ዳግም እንዲያንሰራራ ሲያሴሩበት እያየን ዝም አንልም። አብይም ቢሆን የስራ ጫና በዝቶበት ካልሆነ በቀር በእንዲህ አይነት የአዳህሪዎች ገመድ ተጠልፎ ላለመውደቅ ይጠነቀቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
የሆነው ሆኖ ጥበብ ከላይ የሚሰጥ ምስጢራዊ መክሊትእንጂ፣ ሆድን ለመሙላት ከየፓርቲው ጽህፍት ቤት የሚታደል የአባልነት-ካርድ እንዳልሆነ ባግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።
እኛም ‘መንግስት ጥበብን ይደግፍ’ ስንል ጣልቃ አይግባ ማለታችን ነው። የኪነት-ቆሌ፣ የኪነት-መንግስት በፓርቲ በኩል የሚመጣ አይደልም፤ ኪነት ገንዘብ ያለው ሁሉ ገብቶ የሚደንስበት ውቤ-በረሃ አይደለም። ባለሙያውም እንደ ሴተኛ-አዳሪ ለከፈለው ሁሉ የሚንጋለል አይደለም።
አዲሱን ወይን ጠጅ በአዲሱ አቁማዳ!
(የተቀረውን ጉዳይ የውይይቱንም መንፈስ አካትቼ እመለስበታለሁ)
ሰኔ 19/2010 ዓም