የአማራና ኦሮሞ ማህበረሰብን የሚያጋጭ የህትመት ውጤቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑ ተገለጸ

የአማራና ኦሮሞ ማህበረሰብን የሚያጋጭ የህትመት ውጤቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑ ተገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመደገፍ ቅዳሜና እሁድ ሰልፍ ለማድረግ በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ባህር ዳር፣ ወልዲያ፣ ደብረብርሃን፣ ደብረታቦርና በሌሎች በርካታ ከተሞችም የድርጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከወዲሁ የተለያዩ መልዕክቶችን የያዙ ባነሮችና ፋፍሌቶች እየተዘጋጁ ነው። ነገር ግን የታሰበውን የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ዓላማውን ለማሳት አንዳንድ ወገኖች ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና የኦሮሚያ ክልል የገጠር ፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት የአማራና ኦሮሞ ማህበረሰብን ሊያጋጩ ይችላሉ የተባሉ የህትመት ውጤቶች አዲስ አበባ ታትመው ወደ አማራ ክልል እየገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ የህትመት ውጤቶች የትኛውንም ህዝብ እንደማይወክሉና የድርጊቱ ፈፃሚዎችንም በቁጥጥር ስር ለማዋል የኦሮሚያ ፖሊስ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በፌስ ቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

ሁለቱ ባለስስልጣናት በፌስ ቡክ ገፃቸው ያስተላለፉት መልዕክት የሚከተለው ነው፦

_______

አቶ ንጉሱ ጥላሁ

“ሰሞኑን በክልላችን በሚካሄዱት የድጋፍ ሰለፎች ላይ ጥላቻ የሚዘሩ እና ለብጥብጥ የሚያነሳሱ የህትመት ውጤቶች ታትመው በመጓጓዝ ላይ እንደሆኑ ተጨባጭ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡ የህትመት ውጤቶቹ በተለይም የአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት ያለሙ እንደሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ተግባራት ቢታዩ የአማራን ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸውን እንገልፃለን ፡፡”

__________

አቶ አዲሱ አረጋ

“ሰሞኑን በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች የሚካሄዱ የመደመር፣የፍቅርና የምስጋና የድጋፍ ሰልፎች ላይ ጥላቻ ለመዝራት እና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚያነሳሱ የህትመት ውጤቶች ፊንፊኔ ከተማ ላይ ታትመው ወደ አማራ ክልል በመጓጓዝ ላይ እንደሆኑ ተጨባጭ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡ የነዚህ የህትመት ውጤቶች ዓላማ የኦሮሞ እና አማራ ወንድማማች ህዝቦችን ማጋጨት ነዉ። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ፀያፍ መልዕክቶች ሰሞኑን በሚካሄዱ ሰልፎች ላይ ቢታዩ የትኛዉንም ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸውን ማስገንዝብ እንወዳለን፡፡የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላትም እነዚህን አፍራሽ መልዕክቶችን ተከታትለዉ ቁጥጥር ስር ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

ቶኩማ ያፈራዉ በፍቅር ተተክሎ

አረም ቢዘራበት እንዲመክ ቶሎ

ቅጠሉ ቢረግፍ ግንድላዉ ተንጋዶ

ስሩ እምቢ አለ የኖረው ተገምዶ!”

 

LEAVE A REPLY