ቆይታ ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ ከአቶ ንጉሱ ጥላሁን ጋር

ቆይታ ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ ከአቶ ንጉሱ ጥላሁን ጋር

ትናንት በባህ ዳር ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ በማስመልከት ቢቢሲ አማርኛ ከአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ ከአቶ ንጉሱ ጥላሁን ጋር ቆይታ አድርጓል።

————

 “የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የህዝቡን ውይይት መጠየቁ አይቀሬ ነው” የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሀላፊ ንጉሡ ጥላሁን

ዕለተ እሁድ ሰኔ 24/2010፤ የባህርዳር እና አከባቢዋ እንዲሁም ከሌሎች ሥፍራዎች የመጡ ኢትዮጰያዊያን “ለውጥን እንደግፍ፤ ዲሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል ከተማዋን አድምቀዋት ውለዋል።

ወደ መቶ ሺህ እንደሚጠጉ የተነገራለቸው እኚህ የሰልፉ ተሳታፊዎች በዋነኛነት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለማሻሻያ እርምጃዎቻቸው ያላቸውን ድጋፍ ለመግለፅ ነው አደባባይ የወጡት።

ይህንን ተከትሎም አማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሥ ጥላሁን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ- የትናትንትናውን ሰልፍ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ምን ያህል ሰዎች ተገኙ? ሰልፉስ እንዴት አለፈ?

አቶ ንጉሱ፦ ከሰኔ 16 ጀምሮ እስከ ትናትናውን ዕለት ድረስ በክልላችን ከ43 በላይ ከተሞች ነው የድጋፍ ሰልፍ የተደረገው። ሰሞኑን የሚያደርጉም አሉ። በሁሉም ከተሞች ባለቤት ሆኖ፣ አቅዶ የፈፀመው የየከተሞቹ ህብረተሰብ ነው። ወጣቶቹ ራሳቸው አስተባባሪ ኮሚቴ መስርተው፣ መንግስት ፀጥታ እንዲያስከብርላቸው ጥያቄ አቅርበው ነው የሄዱት። እናም በአስካሁኑ በሁሉም ሥፈራዎች የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች በሰላም ተጠናቅቋል። የባህር ዳሩ ክልላዊ ነው፤ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተገኘበትም ነው። በባህር ዳር ስቴዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄን ያህል ሰው፣ በሜዳውም በመቀመጫውም ሞልቶ የተገኘበት ነበር። ሜዳውን የሚያስተዳድሩ ባለሞያዎች እንደሚያስረዱት ሕዝቡ ከመቶ ሺህ በላይ ይገመታል። እንግዲህ በሰልፉ ላይ ህብረተሰቡ መልዕክት አስተላልፏል። ከዚያ ባሻገር እጅግ ሰላማዊ እና በተፈለገው መልኩ የተጠናቀቀ ሰልፍ ነው።

 ቢቢሲ- በሰልፉ ላይ በተለየ ሁኔታ ጎልተው ከተስተዋሉት ጉዳዮች አንዱ ከሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ጋር የተያያዘው ነው። አርማ የሌለበት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በስፋት ታይቷል። ይህ ምን ዓይነት መልዕክት ወይንም አንድምታ ይዟል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ንጉሱ፦ [ይህ ባንዲራ] በእኛ ክልል፤ በተለያዩ ጊዜያት፤ በተለይም በኃይማኖት በዓላት፣ በጥምቀት፣ በደመራና በመሳሰሉት በዓላት ላይ ህብረተሰቡ በአገልግሎት ላይ ይውላል። በሃዘንም፣ በደስታም፣ በለቅሶ ላይ ሁሉ ተይዞ ይወጣል። በተለይ በአማራ ክልል፣ በተለይም ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት፣ ህብረተሰቡ በሰፊው ጥቅም ላይ ያውለዋል። ህገ መንግስታዊው፤ አርማ ያለው ሰንደቅ ዓላማ በመንግስት መድረኮች እና መንግስታዊ በሆኑ ተቋማት የሚውለበለብ እና አገልግሎት ላይ የሚውል ነው። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይሄ ሰንደቅ ዓላማ አንዳንድ ጊዜ በርከት ብሎ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አነስ ብሎ በአደባባዮች ጭምር የሚታይ ነው። በኃይማኖት ተቋማት የሚታይ ነው።

ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ ለማንም ይሄን ላየ ሕብረተሰቡ ይሄንን ሰንደቅ ዓላማ ፈልጎ ይዞ መውጣቱና ህገ መንግስታዊውን ሰንደቅ ዓላማ በተመለከተ ከክልላችን ህዝብ ጋር ብዙም ያልተግባባን መሆኑን ያስረዳን ነው። ምናልባትም በመመሪያዎች በደንቦች ያስቀመጥናትቸው ህግጋት ስላሉ፤ ለህግ ተገዥነቱን ለማሳየት፤ ግን ደግሞ ልዩነቱን በእንደዚህ ዓይነት መልኩ በስፋት እንዲገልፅ ዕድል በተፈጠረበት ጊዜ መግለፅ መቻሉን ነው ያስረዳን።

ለምንድን ነው እስካሁን እንደዚህ በስፋት አጥለቅልቆ ይዞ ያልወጣው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ እኛ ህብረተሰቡ ማንኛውንም ነገር እንዲያደርግ አልፈቀድንለትም፤ ተፅዕኖ አሳድረንበታል ነው። ስለዚህ ህገ መንግስታዊ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ላይ አልተግባባንም፣ አልተቀበለንም ማለት ነው። ስለዚህ ቀጣይ፤ ለበለጠ መግባባት ህብረተሰቡን በዚህ ጉዳይ ላይ ማወያየት፤ ውሳኔውን አይቶ እንዲወስን፤ ያመነበትን እንዲያደርግ ስራ እንዳለብን ነው ያስተማረን።

ቢቢሲ – በዚህ ረገድ በእናንተ በኩልየክልሉን ህዝብ ውሳኔ እና ምርጫ ተግባራዊ ለማድረግ የመስራት ተነሳሽነት አለ?

አቶ ንጉሱ፦ ህገ መንግስቱ የአማራ ክልል ሕዝብ ብቻ አይደለም። ህገ መንግስታችን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች፥፣ ብሄር እና ብሄረሰቦች ህገ መንግስት ነው። ሰንደቅ ዓላማውም ህገ መንግስታዊ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ስለዚህ የአማራ ክልል ለብቻው ከህገ መንግስቱ ያፈነገጠ ውሳኔ አይወስንም። በመንግስትም በሕዝብም። ነገር ግን ህብረተሰቡ ኃሳቡን ገልጿል፤ ምልክት አሳይቷል። ስለሆነም ምን እናድርግ ብለን ከሕዝባችን ጋር ነው የምንመካከረው። የአማራ ህዝብ ከሌሎች ብሄሮች እና ብሄረሰቦች ጋር በእኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ እንኑር ነው ያለው።

ዴሞክራሲያዊ ማለት በሁሉም ጉዳዮች ላይ መክሮ ዘክሮ አብዛኛው ይሁን ያለውን መቀበል ነው። ስለዚህም በተናጠል አንድ ክልል የሚወስነው ሳይሆን፤ ሁሉም ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የሚወስኑት ነው ማለት ነው። ነገር ግን በአማራ ህዝቦች ዘንድ ያለው መልዕክቱ ህገ መንግስታዊው ሰንደቅ ዓላማን በተናጠልም ይሁን በጋራ ይዞ መውጣት አልፈለገም ማለት ነው። ለምን ብለን መመርመር አለብን።

ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ይሄንን እንዲቀበለው፤ በልቡ ላይ እንዲፃፍ አልሰራንም፤ መመሪያ እና ደንብ በአዋጅ አውጥተናል። እነዚህ መመሪያ እና ደንቦች በልቡ እንዲቀበላቸው አላደረግንም። ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች በደንብ አግባብተን እና ተግባበተን፤ መነሻውን እና መድረሻውን፤ አንድምታውን ለይተን በደንብ መነጋገር እና መግባባት የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ወይንም ሌሎች ጉዳዮች ካሉ የሚታይ ነው የሚሆነው። ዞሮ ዞሮ የህዝብ ውይይት፤ የህዝብ ኃሳብ የሚፈልግ አጅንዳ እንደሆነ አይተናል። ችግሩ የሚመስለኝ የህዝቦችን ነፃነት፣ አብሮነት እና ህገ መንግስቱን በሰንደቅ ዓላማ አጀንዳ ማሳነስ፤ የሰንደቅ ዓላማ ንትርክ ውስጥ መግባት ነው። የክልላችንም ህዝብ ይሄንን ይገነዘባል። እኔ ያልኩት ካልሆነም አይልም። ነገር ግን የህዝቡን ውይይት መጠየቁ አይቀሬ ነው።

ቢቢሲ- በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ በተከናወኑ ሰልፎች ላይም የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁ በብዛት አልታየም። ይሄስ ምንን ያመለካታል ይላሉ?

አቶ ንጉሱ፦ በዚህ ጉዳይ ላይ የግል አስተያየቴን ነው የምሰጠው። እንደክልል መንግስት ለውይይት የቀረበ እና አቋም የተወሰደበት ጉዳይ አይደለም። ለምን የአማራ ክልል ሰንደቅ ዓላማ አልታየም ብለን ብንወስድ ይሄ የራሱ ምክንያት ይኖረዋል። አሁን እየተነጋገርን ያለነው፤ ህብረሰተቡ ይሄንን ሰንደቅ ዓላማ ይዟል፤ በህገ መንግስት የተደነገገውን ሰንደቅ ዓላማ አልያዘም፤ በክልሉ ህገ መንግስትም የተደነገገውን ሰንደቅ ዓላማ አልያዘም የሚል ነው።

ይሄ ኅብረ ብሄራዊ ክልል ነው። በርካታ ብሄር ብሄርሰቦች በጊዜያዊነትም፤ በቋሚነትም የሚኖሩበት ክልል ነው። ስለዚህ ይህ ጉዳይ የአማራ ህዝብ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ህገ መንግስት ላይ በተቀመጡት ጉዳዮች በተለይም ሰንደቅ ዓላማን በሚመለከቱት ላይ መነጋገር እና እንደገና በደንብ መወያየት እና የጋራ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይጠይቃል። በአዲስ አበባው ሰልፍ እንዳየነው በርካታ ሰንደቅ ዓላማዎች ነው የታዩት፤ በባህር ዳር ደግሞ አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህም እነዚህን ፍላጎቶች እንዴት ነው ማጣጣም የሚቻለው? የሚለው መመለስ ያለበት በህዝብ ስምምነት እና ከህዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት ነው። ስለዚህ የክልሉ እና የፌዴራሉ ሳንል በአጠቃላይ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የቤት ስራ አለብን ብለን ነው መደምደም የምንችለው።

LEAVE A REPLY