የደራሲ ይስማዕከ ወርቁ እና የባለቤቱ ወ/ሮ ጸጋ አንዳርጌ ጉዳይ እያነጋገረ ነው

የደራሲ ይስማዕከ ወርቁ እና የባለቤቱ ወ/ሮ ጸጋ አንዳርጌ ጉዳይ እያነጋገረ ነው

ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ከዘጠኝ ወራት በፊት የመኪና አደጋ ደርሶበት ማውራት አይችልም። ባለቤቱን ጨምሮ አንዳንድ ሰዎች ይህንን አይቀበሉም። ማውራት (መናገር) እንደሚችል ይሞግታሉ። ይስማዕከ ስለተፈጠረው እና ከዚህ በፊት የልጆቹ እናት ለአዲስ አድማስ ለሰጠችው ቃል በጽሁፍ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

የሁለቱንም ምልልስ እንደሚከተለው ይከታተሉ…

__________

ይስማዕከ ባለቤት ፡ –

የደራሲ ይስማዕከ ሚስት፣ ”ስቃይና ብሶቴን ስሙኝ” ትላለች
· “ሁለት ልጆቼን የማበላቸው አጥቼ ተቸግሬአለሁ”
· “ህይወቴ በአደጋና በስጋት የተሞላ ነው”
የ27 ዓመቷ ወ/ሮ ፀጋ አንዳርጌ ምህረት፣ የዕውቁ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ባለቤት ናት፡፡

በ1998 ዓ.ም መተዋወቃቸውን የምትናገረው ወ/ሮ ጸጋ፤ ለ12 ዓመታት በትዳር መኖራቸውንና አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ማፍራታቸውን ትገልጻለች፡፡ ሆኖም የደራሲነት ዝናው እየጨመረ ሲመጣ ውጭ ውጭ ማለት እንደጀመረ የምታስረዳው የደራሲው የትዳር አጋር፤ አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ተለያይተው እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ጥንዶቹ ዳግም የተገናኙት ይስማዕከ የመኪና አደጋ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ወ/ሮ ጸጋ ተናግራለች፡፡

ሁለተኛ የአብራካቸው ክፋይ የተወለደችውም በዚህ ጊዜ ነው ትላለች፡፡
ይሁን እንጂ ባላሰብኩት ሰዓት እኔንና ሁለት ህጻናት ልጆቻችንን ባዶ ሜዳ ላይ ጥሎን በመሰወሩ፤ በአሁን ሰዓት ለልጆቼ ቀለብ መግዣ አጥቼ የከፋ ችግር ላይ እገኛለሁ ብላለች – አዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ድረስ መጥታ ብሶቷን የነገረችን ወ/ሮ ፀጋ አንዳርጌ፡፡ ደርሶብኛል የምትለው በደል ግን ይሄ ብቻ አይደለም፤ እስከ ዛሬ መልካም ስሙንና ዝናውን እንዳላጎድፍበት ብዬ ሲያደርስብኝ የቆየውን ግፍ ደብቄ ቆይቻለሁ የምትለው የደራሲው ባለቤት፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ከዚህ በኋላ የመጣው ይምጣ ብላ የደረሰባትን ሁሉ አፍረጥርጣ ተናግራለች፡፡ እነሆ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
ጉዳዩን ለማጣራት ለደራሲ ይስማዕከ ወርቁ በሞባይል ስልኩ የፅሑፍ መልዕክት (ቴክስት ሜሴጅ) ልከን “የኮሚቴው ኃላፊ ሽመልስ አበራ ጆሮ ስለሆነ በእነሱ ፊት አነጋግሪኝ” በማለት ምላሽ ቢሰጥም በኮሚቴው በኩል ልናገኘው ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ከይስማዕከ ወርቁ ጋር እንዴትና መቼ ተዋወቃችሁ?
ከይስማዕከ ጋር የተዋወቅነው በ1998 ዓ.ም እኔ የአንደኛ ደረጃ፣ እሱ የሀይስኩል ተማሪ እያለን ነው። የተዋወቅነውም ቤት ተከራይቶ፣ እኛ ጎረቤቶች ቤት ከገባ በኋላ ነው፡፡ ለአንድ አመት ብቻ በጓደኝነት ከቆየን በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ አብረን መኖር ጀመርን።

D3D67F39-38BC-4180-A8DC-418B0697D3A6

በጥሩ ፍቅር ስንኖር ቆይተን፣ በድርሰቱ እውቅናና ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር፣ በሰው ሲታጀብ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት መስከር፣ እኔንም መደብደብና ማሰቃየት ጀመረ፡፡ ይባስ ብሎ ባመሸበት ማደር፣ ለትዳሩ ታማኝ አለመሆን ጀመረ፡፡ ብዙ ስቃይና ጭቆና ውስጥ ነው የኖርኩት፡፡ ስልክ ማናገር፣ ከጓደኛና ከቤተሰብ ጋር መገናኘት አልችልም ነበር፡፡
ግን እኮ ይስማዕከ በስራው እውቅናና ዝናን ካገኘ ቆይቷል፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ጭቆናና በደል ሲያደርስብሽ እንዴት ዝም ብለሽ ተቀመጥሽ?
እኔ ያገባሁት ለዝና ብዬ አይደለም፤ ገና ተማሪ እያለ ሳይታወቅ ነው፤ ይወደኝ እውደው ነበር፡፡ ማሰቃየትና መበደል ሲጀምር፣ ብዙ ጊዜ ከቤት እየወጣሁ ቤተሰቤ ዘንድ እሄድ ነበር፡፡ ከዚያ ሽማግሌ እየላከ ይቅርታ እየጠየቀ፣ መልሶ ይወስደኛል፡፡ ቤተሰቤም፤ “እስኪ ታገሺው፣ ይሻሻል ይሆናል” ብለው ይልኩኛል፡፡

B2F54D0C-8DAF-466F-82E4-2D6D909F1625

በዚህ መልኩ አብረን ቆየን፡፡ ሀብትና ንብረትም አፈራን፡፡ ወንዱን ልጃችንን ወለድን፡፡ እኔም ብዙ ውክልናዎችን በመውሰድ፣ በመፅሐፎቹ ሥራ፣ በማተሚያ ቤቱ አብሬው እሰራ ነበር፡፡ በመሀል ብዙ ስቃዮችን፣ ድብደባዎችን ሲያደርስብኝ፣ በቃ ይሄ ነገር ለህይወቴ ያሰጋኛል በሚል ፍቺ ጠየቅሁኝ፡፡ ጉዳዩ ገና በፍርድ ቤት እያለ፣ ሀዋሳ ላይ ጠጥቶ ከሌላ ሴት ጋር አምሽቶ ሲያሽከረክር፣ ያው አገር የሚያውቀው፣ የመኪና አደጋ ደረሰበት፡፡
እኔም ይህን ያህል ጊዜ አብሬው ኖሬያለሁ፤ የልጄ አባት ነው ብዬ፣ ሁሉን ትቼ፣ እሱን ማስታመም ጀመርኩ፡፡ ይህንንም ወዳጅ ዘመድ ያውቃል፡፡ ሌሊት ቀን ሳልል አስታመምኩት፣ ዳነ፡፡ ተሻለውና ያንን ረስቼ፣ አብሬው መኖር ጀመርኩ፡፡ እንደገና ሁለተኛዋ ህፃን ተወለደች፡፡ አሁን ዘጠኝ ወሯ ነው፡፡ ታሞ ከተሻለው በኋላ፣ እኔ ህፃኗን እርጉዝ ሆኜ፣ መልሶ መደብደብ ማሰቃየት ጀመረ፡፡ እርጉዝ ሆኜ ሆዴን ረግጦኝ፣ ብዙ እንገላቶኝ፣ ከሞት ተርፌያለሁ፤ የህፃኗ መትረፍ ራሱ ተዓምር ነው፡፡

ከተወለደች በኋላ ያው ስቃዩን ችዬ መኖሬን ቀጠልኩ፡፡ ለልጆቹ ሥል ነበር ስቃይ የማየው። ከዚያ የፋሲካ በዓል መጋቢት 30 ሊሆን፣ መጋቢት 28 ቀን ፋሲካን ሀዋሳ እናሳልፍ ብሎ ከእነ ልጆቼ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይታይሽ ለልጆቹም ለእኔም ለበዓል የሚሆን ልብስ ብቻ ነው የያዝኩት፡፡ እዛ እንደሄድን እኔም ቤተሰቤ ጋ፣ እሱም እህቱ ጋ ገባ፡፡ የበዓል ቀን ልጆቼን አለባብሼ፣ እሱ ቤተሰብ ጋ ስሄድ፣ ሊያናግረኝም ሆነ ልጆቹን ሊያይ ሁሉ አልፈለገም፡፡
ለምን? ምን ተፈጠረ?
ምን አውቃለሁ?! ፊት ሲነሳን፣ ልጆቼን ይዤ፣ ወደ ቤተሰቤ ተመለስኩ፡፡ እኔ እጠብቅ የነበረው፣ ኩርፊያው አልፎለት፣ ወደ አዲስ አበባ እንመለስ እስኪለኝ ነበር፡፡ ዝምታ ሲበዛና ስጠይቅ፣ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ተረዳሁ፡፡

እኔም ልጆቼን ይዤ ተመለስኩ፤ ግን የተከራየነውን ቤት ለቅቆ፣ የት እንደገባ ማወቅ አልቻልኩም፡፡
የት ነበር የምትኖሩት?
አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ነበር፡፡ ከእነቤት እቃው፣ የኔንም የልጆቼንም ልብስ፣ የልጆች መኝታና መጫወቻ ሁሉ ሳይቀር የለም፡፡ ከዚያም እኔም የምሰራበት፣ የምንተዳደርበት ማተሚያ ቤት ስሄድ፣ ማሽኖቹን የት እንዳደረሳቸው አላውቅም፡፡ የማተሚያ ማሽኖቹ 13 እና 14 ሚ. ብር እንደሚያወጡ ባለሙያዎች ነግረውኛል፡፡ እንዲህ ከሆነ አሁን ሦስት ወር ሊሆነን ነው፣ ለልጆቹ ቀለብ የለ፣ አይጠይቃቸው፣ የት እንዳለ አይታወቅ፤ ራሱን ሰውሯል፡፡ ነገር ግን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ በሰይፉ ሾው ቀርቦ፣ መናገር አልችልም ሲል ስሰማ፣ ማመን ነው ያቃተኝ፡፡
ለምን ማመን አቃተሽ?
አንደኛ፤ ጥቁር አንበሳ ለመጨረሻ ጊዜ ለቼክአፕ ሲሄድ አብሬው ነበርኩ፡፡ ዶክተሮቹ፤ “በደንብ ማስታወስ ትችላለህ፣ የረሳኸው ነገር የለም፤ ስፒች ቴራፒው አሪፍ ሆኖልሃል፣ መናገር ችለሃል፤ ወደ ውጭ የሚያስኬድ ነገር የለም” ሲሉት አብሬው ሆኜ ሰምቻለሁ፡፡
ከዳነ በኋላ አብሬው ኖሬያለሁ፤ በደንብ ያወራል፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ ይጥለዋል፤ ይህም የሚሆነው መጠጥ ከጠጣና ከተበሳጨ ብቻ ነው።

4F56F30C-A44B-4E53-AC80-AD84778CA6EC

እንደሚናገርና በጣም ሰላም እንደሆነ፣ አብረውት ያሉ፣ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ነን የሚሉት ታዋቂ አርቲስቶችና ጓደኞቹ በደንብ ያውቃሉ፡፡ ይሄን ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው እንዴ ከኔና ከልጆቹ የተሰወረው? እያልኩ፣ ይሄው ከእነ ልጆቼ በችግር ላይ ወድቄያለሁ፡፡
ለሶስት ወር ያህል አብራችሁ እንዳልኖራችሁ ነግረሽኛል፡፡ ምናልባት በዚህ መሃል እንደገና ታምሞ መናገር ተስኖት ቢሆንስ?
በደንብ እንደሚናገር አውቃለሁ፡፡ ከኮሚቴው ከሌሎች ሰዎች ጋር በውጭ ህክምና ዙሪያ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሴራ የተጠነሰሰው በስልክ ነው፡፡ ይሄንን በቀኑና በወቅቱ፣ ከቴሌ ድምፁን ማስወጣት ይቻላል፡፡

ከእህቱ ጋር ሆነው፣ እኔንም በስልክ አስፈራርተውኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከጎኔ ሆኖ የሚረዳኝ በማጣቴ፣ ልጆቹንም ለማንም ሰጥቼ መንቀሳቀስ ስላቃተኝ እንጂ ስለመናገሩ በደንብ ማስረጃ አለ፡፡ ህሊናቸውን ካልካዱ በስተቀር አሁን ከጎኑ ሆነው ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚሯሯጡትና ሰይፉ ሾው ላይ ቀርቦ፣ የእሱ አፍ የሆነው፣ ፈሪያት የሚባለው ጓደኛውም፣ በደንብ ያውቃል፡፡
አሁን አንቺ የት ነው የምትኖሪው?
ሐዋሳ ቤት ነበረን፤ አብረን ያፈራነው ቤት ነው። እርግጥ ለመኖሪያ ቤት ሳይሆን ለሆቴልነት ነበር አሰራሩ፡፡ አሁን እዛ ቤት ነኝ፡፡ ፊት ለፊቱ መስታወት ነው፤ እኔም ልጆቹን ይዤ እዛ ሜዳ ላይ ነው ያለሁት፡፡ እዛም የገባሁት በእህቱ በኩል ቤቱን ሊሸጥ ሲያስማማ፣ ቁልፍ ስለነበረኝ፣ ከፍቼ ገብቼ እንዳይሸጥ አሳገድኩት፡፡ አሁን አንዳንዴ አባቴ፣ አንዳንዴ ወንድሞቼ እየጠበቁኝ ነው የማድረው፤ በጣም ስጋት ላይ ነኝ፡፡ እህቱ አገሬ እሸት ትባላለች፡፡ ከቤቱ ጎትተው እንዲያስወጡኝ ለፖሊሶች ነግራቸው ነበር፡፡ ህጋዊ ሚስቱ መሆኔን ሲያውቁ፣ አርፈሽ ተቀመጪ አሏት፡፡
እስከ ዛሬ የበደለኝን፣ ያደረሰብኝን ጭቆናና ስቃይ የቻልኩት፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የገነባው መልካም ስምና ዝና እንዳይበላሽ ብዬ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አንድ ነገር ያደርገኛል፣ ገና በወጣትነቴ ቢገድለኝ፣ ለቤተሰቤም ለልጆቼም አጎድላለሁ ብዬ ነው፡፡

አሁን ግን ችግሩ ባሰብኝ፤ ልጆቼን የማበላው አጣሁ፡፡ ሜዳ ላይ ወደቅኩኝ፡፡ ከዚህ በኋላ የፈለገው ይምጣ ብዬ ነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዱን እንዲሰማ ወደ እናንተ የመጣሁት፡፡ ቅድም መናገር ባይችልስ? ብለሽኛል። መናገር መቻል አለመቻሉ፣ ትዳሩን ለመበተንና ልጆቹን ያለ ቀለብ ሜዳ ላይ ለመጣል ምክንያት አይሆንም፡፡ ከኔ ተደብቆ መጥቶ፣ ከሌላ ሴት ጋር ነበር የሚኖረው፡፡ ከሌላ ሴት ጋር ህይወት መስርቶ፣ ለእኔ ግን በምወዳቸውና በማከብራቸው ሰዎች በኩል፣ የፍቺ ወረቀት ላከልኝ፡፡ ለመሆኑ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ የአገራችን ህግ ይፈቅዳል?
ህጋዊ የጋብቻ ፊርማ አላችሁ?
አዎ! ወንዱን ልጄን እስካረግዝ ድረስ አብረን እንኖር ነበር እንጂ አልተፈራረምንም ነበር፡፡ ወንዱን ልጄን እርጉዝ ስሆን ተፈራረምን፡፡ ህጋዊ ጋብቻ አለን፡፡ የሚገርምሽ ሃዋሳ የመኪና አደጋ ሲደርስበት፣ ከሌላ ሴት ጋር ነበር፡፡ መቼም በዚያ ሌሊት ከእህቱ ጋር አልነበረም፡፡ ከዚያም በፊት ለትዳሩ ታማኝ አልነበረም፡፡

ይሄን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አውቆት፣ ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝም፡፡ የኢትዮጵያም ህዝብ መጭበርበር የለበትም፡፡ የሚገርምሽ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው አካውንት ውስጥ 400 ሺህ ብር መግባቱን አረጋግጫለሁ፡፡ ህዝቡ እየተጭበረበረ ነው፡፡ እኔም ከዚህ አካውንት ገንዘብ እንዳይወጣ አሳግጄዋለሁ፡፡ እርግጥ ነው እሱ እኔን ለማጥፋት ከመሞክር ወደ ኋላ አይልም፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለመንግስትም ለኢትዮጵያ ህዝብም ህይወቴ በአደጋና በስጋት የተሞላ መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እህቱ በየቀኑ ሀዋሳ የተለያዩ ሰው እየላከች፣ እንዲያስፈራሩኝ እያደረገች ነው፡፡ እኔ እንኳን ብሞት፣ ልጆቼን መንግስትና ህዝብ እንዲጠብቅልኝ አደራ እላለሁ፡፡
የፍቺ መጥሪያ ከደረሰሽ በኋላ ፍ/ቤት ቀረብሽ?
ቀጠሮው ለግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፤ እኔ ቀረብኩ፣ እሱ የለም፡፡ በመሃል ለሁለተኛ ጊዜ ቀረብኩ፤ አሁንም የለም፡፡ እኔ በመሃል ይግባኝ ብዬ ነበር፡፡ እሱ ስላልቀረበ ፒያሳ የሚገኘው፣ አራዳ ምድብ ችሎት፣ ለሰኔ 26 ፍ/ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቶኝ፣ እየተጠባበቅሁ ነው። የይሰማዕከን በደልና ግፍ በተመለከተ፣ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሄደሽ ብትጠይቂ፣ ይነግሩሻል፡፡ የሴቶች ጉዳይ አመልክቼ፣ እንረዳሻለን ካሉኝ በኋላ፣ እሱ መሆኑን ሲያውቁ፣ ጉዳዩን ችላ አሉት፡፡

አሁን በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በኩል፣ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እየጣርኩ ነው፡፡
ለመሆኑ አሁን ምን እየሰራሽ ነው የምትኖሪው?
ምንም እየሰራሁ አይደለም፡፡ እንደምታይው፣ እዚህ አንቺን ለማግኘት ስመጣ እንኳን፣ እነዚህን ህፃናት ይዤ ነው፡፡ ወንዱ 2 አመት ከሰባት ወር፣ ሴቷ 9 ወሯ ነው። ለማን ጥያቸው እመጣለሁ? ለማንስ ሰጥቻቸው ስራ እፈልጋለሁ? የምሰራውና የምንተዳደረው በማተሚያ ቤቱ ነበር፡፡ የማተሚያ ቤቱን እቃዎች ወዴት እንዳሸሻቸው አላውቅም፡፡ አንቺ ልጆች ይዘሽ ዳቦ ሲሉሽ ማቅረብ ካልቻልሽ፣ በቃ በህይወት እንደሌለሽ ቁጠሪው፡፡ አሁን ላይ ይህን ጉድ የሰሙ ሰዎች፤ መቶም ሁለት መቶም፣ አስርም ብር እየሠጡኝ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሦስት ወር ሊሞላኝ ነው፡፡ የሚገርምሽ በፊትም ባሻ ወልዴ ችሎት እያለን፣ የተሟላ የቤት እቃ ያለበት ቤት ውስጥ ነበር የምንኖረው፡፡ ግን ለቤቱና ለልጆቹ አስቤዛ እንኳን አይገዛም፤ ስሙን ለማጥፋት አይደለም፤ በረሃብ ሲቀጣን ነው የኖረው፡፡

አሁን የሚደርስብኝን ለመቀበል ለመሞትም ጭምር ዝግጁ ነኝ፡፡ ሁሉም ግን በግልፅ መውጣት አለበት፡፡ ዝና ወዲህ ተግባር ወዲያ ነው፣ የእሱ ጉዳይ፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ ይቁም፡፡
የህግና የፍትህ አካላት ድጋፍ እሻለሁ፡፡ በእህቱ በኩል የሚልክብኝን ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ፖሊስ እንዲያስቆምልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ፣ የዕለት የሚሆን የልጆች ቀለብና ተያያዥ ወጪዎች ያስፈልጉኛል፡፡ ይህን በማጋለጤ ህይወቴ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አውቃለሁ፡፡ ለሚደርስብኝ ሁሉ ሀላፊነት የሚወስደው እሱና በሱ ዙሪያ ያሉ፣ ጋሻ ጃግሬዎቹ እንደሆኑ፣ አበክሬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ፍትህ እሻለሁ፡፡

——————————-

በጤናውና በቤተሰቡ ዙሪያ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ የሰጠው ምላሽ

  • “ርካሽ ዝና ከኔ ትወስዳለች እንጂ ልጆቼን አታሳየኝም”
  • “የልጆቼ እናት ለማኝ ሆና እንቅልፍ የሚወስደው አዕምሮ የለኝም”
  • “እህቴ ለእርሷ እንጂ ለኔ አድልታ አታውቅም”

 ከአዘጋጁ

ለውድ አንባቢያን፡- ባለፈው ሳምንት የታዋቂው ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ባለቤት ፀጋ አንዳርጌ ምህረት ዝግጅት ክፍላችን ድረስ መጥታ “ህዝብ ብሶቴን ይስማ” በማለት፣ ደረሰብኝ ያለችውን በደል መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ወደ ማተምያ ቤት ከመሄዳችን በፊት ግን ደራሲ ይስማዕከ ወርቁን አግኝተን ምላሽ ወይም ማብራሪያ እንዲሰጠን ጥረን ነበር፡፡ ያደረግነው ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ይስማዕከ ፈቃደኛ ሆኖ፣ ለጥያቄዎቻችን በፅሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በኢ-ሜይል የላከልንን ከሞላ ጎደል እንዳለ አቅርነበዋል፡፡ ጥንዶቹ ችግሮቻቸውን በመነጋገር ይፈቱታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ስለ ባለቤትህና ስላንተ ግንኙነት ባጭሩ ብትነግረኝ?

እኔም በትምህርትና በመፃፍ ነው ሕይወቴን ያሳለፍኩት። ሕይወቴ ከታመምኩ በኋላ ምስቅልቅሉ መውጣቱም ይህን ያሳያል፡፡ ጋብቻችንን የፈፀምነው ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው ብትልም በጣም ጥሩ ነው፡፡ በ02/02/2008ዓ.ም-በተራ ቁጥር 031883፣ በክብር መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ነው፡፡ የሚገኘው ጋብቻችን፡፡ ከዛም በኋላ አንድ ወንድ ልጅ፣ አንዲት ደግሞ ሴት ልጅ ወለድን፡፡ የጠቀሰችው ዓመተ ምህረት ግን ትክክል አይደለም፡፡ የሚገርመው ለዚህ ጋዜጣ የሰጠችውና ለፍርድ ቤት ያቀረበችው ተመሳሳይ አይደለም፡፡ በተለይም መላ ቤተሰብዋን ምስክር አድርጋ ካቀረበቻቸው ላይ ሁለቱ በጠቀሰችው አመተ ምህረት ይወለዳሉ ወይ ነው ጥያቄው፡፡ የልጆቼ እናት ናትና ምን እላለሁ፡፡

ባለቤትህ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ላይ ያቀረበችውን ቅሬታ እንዴት ታየዋለህ?

ባለፈው ሳምንት ጋዜጣ ላይ አሜሪካ ለኮሪያ ወይም ለራሺያ የማትሰጠው አቲካራ ሆኖ ባገኘውም የሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ ምንም ብንለያይም፣ የልጆቼ እናት ናት፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ልጆቼን የሚጎዳ ነገር እዚህ ላይ መናገር አልፈልግም፡፡ ልጆቼ በእኔ እንዲያፍሩ አላደርግም። ሁሉም ያልፋል፡፡ እኛም ራሱ እናልፋለን፡፡ ግን መጥፎ ታሪክ ሰርተን፣ ወይም የማይጠፋ ቃል ተናግረን ካለፍን፣ የእኛ ሸክም ልጆቻችን ላይ ይከመራል፡፡ እነሱ በማያውቁት ነገር ሲጎዱ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ አቀራረቡ ቢያሳዝነኝም አልፈዋለሁ፡፡ ሌላው …የተካሰስነው እኔ እና እርሷ ነን፡፡ በእኔ ዙሪያ ማንንም እንድታይ ፈቃደኛ አይደለችም፡፡ ግን የመጨረሻ የማሳስባት ነገር ቢኖር፣ ከኮሚቴው ራስ ላይ ትውረድ፡፡ አንዱ ወይም መላ ኮሚቴው በስም አጥፊ ቢከሳት የለሁበትም፡፡ ሽመልስ አበራ ጆሮ ነው ሚያጭበረብር? ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ ነው እሚያጭበረብር? መንገሻ ተሰማ ነው እሚያጭበረብር? ፍርያት አትክልት ነው እሚያጭበረብር? መሳይ ወንድሜነህ ነው እሚያጭበረብር?  እስከ ዛሬ ከሰማኋቸው ዜናዎች “አዬ ጉድ” የሚያስብል ወሬ ነው… እራሷ ገንዘብም ቆጥሬ አላውቅም፡፡ አዲስ አበባ ያሉትን ጓደኞቼን … እስክድን እንኳ አቅቶሽ፣ ያለ ስሜ ስም ሰጥተሽ፣ ለጉዋደኞቼ ተናግረሽ ሲርቁኝ ጥሎኝ ያልሄደውን ፍርያትን “የእርሱ አፈ ጉባኤ” በማለትሽ ፀፀቱ ለራስሽ ነው፡፡  ሰይፉ ፋንታሁንም እስከ ዛሬ ተገናኝተን፤ “ህዝቡን እንዴት መዝረፍ አለብን” በሚለው ላይ ተገናኝተን አውርተን አናውቅም:: በኮሚቴው ላይ ያነሳሽው አሰስ ገሰስ ወሬ ጊዜውን ጠብቆ ትከፍይበታለሽ። ኮሚቴዎቸን በተመለከተ የራሳቸው ዝና ያላቸው ናቸው፡፡ እንኳን እርሷ ልታጎድፋቸው፣ እኔም ብሆን ቀና ብዬ ለማየት የማፍር፣ ከእነርሱ ጋር ብጣላ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደምጣላ አውቀዋለሁ፡፡ እነሱ ሲጠይቁኝ ነው መኖሬ የሚሰማኝ፡፡

ኮሚቴው ራሱ “እኛ ገንዘቡ ቢገባ እንተማማለን፣ በአንተ ስም በተከፈተ አካውንት ይግባ” ተብዬ ነው በእኔ ስም የተከፈተው፡፡ ከሰይፉ ሾው በሁዋላም አንዲት ሳንቲም ነክቼ አላውቅም፡፡ ሂዱና በብርሃንና ሰላም ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ ተመልከቱ፡፡ የባህር ዳር ልጆች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ገንዘቡን በባንክ አስገቡ ሲልዋቸው፡፡ እኔ ጋ ቼኩ አልደረሰም። ቢጠፋበት አንድ ሰው ብለው፤ ተመንዝሮ ነው የተላከው፡፡ እኔም ለጤናዬ እንጂ ገንዘቡ የሚውለው፣ በፍፁም የኢትዮጵያ ህዝብን አላጭበረብርም፡፡ አንቺ እኮ እኔን ስታጭበረብሪ ነበር፡፡ ሁሉንም ባንቺ ሂሳብ አትለኪ። ፍርድ ቤቱ ባግባቡ ይፍረድና፣ እኔ ጤናዬን እንጂ ሁሉም ነገር ለልጆቼ ይውላል፡፡ እርሱንም በእኔ በአባታቸው ስም ከተጠሩ ብቻ ነው፡፡

ከባለቤትህ ጋር ለፍቺና ለፍርድ ቤት ያበቃችሁ ነገር ምንድን ነው?

ከዛ በፊት ታስሬ ነበር፡፡  ምክንያት በሌለው ምክንያት። በእርስዋ ምክንያት፡፡ ወይ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ወይም ሰኔ መጨረሻ ላይ፡፡ ሐምሌ ላይ ታሰርሽ ማለት ደግሞ ጉዳይሽ ጥቅምት መጨረሻ ላይ ነው የሚታይልሽ፡፡ መንግሥት በምን  ልሰረው እያለ፣ ወስዳ ከተተችኝ ሚስቴ፡፡ ብታሰር አሪፍ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና አላይም ነበር፡፡ ከባድ የመኪና አደጋ ያስተናገድኩትም ከዛ በኋላ ነው፡፡ ያው በእርሷ ምክንያት ማለት ይቻላል፡፡ ለምን? ሀዋሳ ውስጥ ነኝ ብላ ለእህቴ ተናገረች፡፡ እኔ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ነበርኩ ማተሚያ ቤት፡፡ ባንክ ቤት ሄድኩና “ወይ ሸጣችሁ ክፈሉ ወይም እኛ ጨረታ ልናወጣው ነው ቤቱን” ተባልኩ። ለባንኮቹ እንኩዋን ቤቱን ራሴንም ቢሸጡኝ ክብር አለኝ፡፡ አከብራቸዋለሁ፡፡ ረቡዕ ነበር፡፡ ወደ ሀዋሳ በዛው ነዳሁት፡፡ እህቴ ቤት አደርኩ፡፡ ሐሙስ በጥዋት ገዢ ፍለጋ ተነሳሁ፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ገዢ አገኘሁ፡፡ ከዛ ወደ ሻሸመኔ ሄድን፡፡ ወደ እህቴ ደወልኩና “በዓይኔ እየሄደብኝ ነው፣ ልጄን አሳይኝ፡፡” እላለሁ እኔ፡፡ “ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ናት ሰው ታሞባት” ትለኛለች እርሷ፡፡ “ትጨርስና አምጥቼ ልጅህን አሳይሃለሁ።” ከዛ ከጆሮዬ ጥልቅ አለ አንድ ነገር፡፡ ሀዋሳ ውስጥ የለችም፡፡ አብረን ለገዢው ብንሸጥለትስ? አዲስ አበባ ናት፡፡ እንዲያውም ለሃያ ሁለት ቀናት አዲስ አበባ ናት፡፡ ከዛ ወደ ይርጋለም እየነዳሁት ነበር፡፡ ያደፈጠ መኪና መጥቶ እስኪጋልበኝ ድረስ፡፡ ከዛ በኋላ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነቃሁ፡፡ መናገር አልችል፣ መጻፍም አልችልም ነበር፡፡ ቀስ ቀስ እያልኩ ነው የተለማመድኩት፡፡ እንዲያውም… መቆም አይችልም ብለው ነበር አሉ ሀኪሞች፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና ከሰማይ ከምድር ያህል የሚከብደኝ ቂጤ ነበር፡፡ ሽንት ቤት አንድ ቀን ገባሁና ተቀመጥኩ፡፡ መነሳትም አልችልም፡፡ አልናገርም፡፡ እንዴት እህቴን ልጥራት፣ ብልጎመጎም፣ ብልጎመጎም፡፡ ከብዙ ሰዓት በኋላ እህቴ መጣች፡፡ ከዚሁ ጋር… ወንድሟ ሰው ገጨ ተብሎ ብትሰማ፣ እንባዋ ማባሪያ ጠፋው፡፡ ወንድሟ ታልቅስ፡፡… እንዲያውም በእኔ ጊዜ፣ አዲስ አበባ ሰምታ፣ “ኢየሱስን አመስግኑ” በማለት … አሁን ወደ ኋላ ታሪኬን ሳጠና፣ መላ የሀዋሳ ህዝብ አዝኖ፣ እነሱ ግን አልመጡም … ፀሎት ላይ ነበሩ፡፡ የልጃቸው አባት ነበርኩ፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር ለ22 ቀናት ነበረች፡፡ እኔና እሱ በቀን በቀን እየተገናኘን ነበር፡፡ ለ22 ቀናት ባለቤቴን እንዳስቀመጠ ግን አልነገረኝም፡፡ አሁን የሚለው ግን “ልጅህ ታሞ” ብላ ደውላልኝ መጣች፣ እርሱ በችግሩ ጊዜ ከእኔ እንደማይወስድ፣ ልጅህን ላሳክምልህ ነው” የሚለኝ፡፡ ሆኖም እንደ እኔ ባጋጣሚ ሳይሆን፣ የሚፈልገውን ላሟላለት ነው ልጄን የወለድኩት፡፡ ደሜ የፈሰሰውም ለእርሱ ነው፡፡ የአራት ሰው ደም ነው የወሰድኩት፡፡ በዛ ላይ ቆንጆ ልጅ ነው፡፡ እንደምወደው እያወቀ፣ ሌሊት ሌሊት በህልሜ ከእርሱ ጋር እንደማድር እያወቀ፣ ባለቤቴን ከቤቱ እንዳስቀመጠ ሳላውቅ…፡፡ እሷ እሱ ቤት ሆና እንድትከሰኝ አመቻችቷል፡፡ እኔ ሳላዉቅ፡፡ እኔ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወጥቼ እያገገምኩ፣ ጠበቃ የሆነ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ “አራዳ ፍርድ ቤት ባለቤትህ ስትመላለስ ነበር” አለኝ፡፡ ቅርብ ስለሆነ ሄድኩ፡፡ ቦርዱ ላይ ሳየዉ ከሳኛለች፡፡ ወደ ላይ ስወጣ፣ “ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ እና ጉዳቱ የጭንቅላት ነው ይህን መስጠት የለብሽም፤” … ከብዙ ድራማ በሁዋላ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፡ “ለምን እኔ አልጠይቃትም” ብዬ ትዳር እኮ ማቆየት እንጂ አደጋው፣ ለማፍረስ ምንም እኮ ችግር የለውም፡፡ ትዳሩ ደበረኝ ብሎ እኮ ማፍረስም ይቻላል። እንኳን ይህ ሁሉ ምክንያት እያለኝ” እኔም በዛው ቀን የፍታህ ብሄር ክስ ይዤላት መጣሁ፡፡ እኔም ስለማልስራ አንቺም ስለማትሰሪ ፍርድ ቤቱ “ይህ ያንቺ፣ ይህ የእኔ” እስኪለን ድረስ አብረን እንኑር፤ ተባብለን አብረን መኖር ጀመርን፡፡ ማድረግ ያልነበረብኝ ነገር ነው … እስከ መጋቢት 29/2010 ድረስ፡፡ ወይ አንሰለጥን፣ ወይም ደግሞ…፡፡

ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዳችሁ በፊት ችግራችሁን በሽምግልና ለመፍታት አልሞከራችሁም?

እኔ ከአስራ አምስት  ጊዜ በላይ ሽምግልና ሞክሬአለሁ። እነ ዶክተር እዝራ፣ እነ አየለ እምሩ፣ እነ ብርሃኔ ዘርው፣ እነ ሽመልስ አበራ ጆሮ…፡፡ እኔ እርሷን አልከሰስኳትም፡፡ ክስዋን የሰጠችው ለፖሊስ ነው፡፡ እኔ ታምሜ ምንም አላይም፡፡ ከዛ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፡ ደግሞ እኮ ይነገራል፡፡ እኔ ሄጄ ባየው ጊዜ በጣም ነው የተናደድኩት፡፡ ደግሞ ወዲያውኑ ነው የወሰንኩት፡፡ ሰው ከጠላቱ ጋር አይኖርም፡፡ እሷም ያሰበችው ይኖራል፡፡ እንዲህ በቀላሉ ትዳር የሚያስፈታ ነገር ምን አለ? እኔን ጨካኝ አድርገው የሳሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ምንም የማላውቀው ነገር  ስላለ ነው፡፡ ድርጅት ነበረን፣ እኔ ስተኛ አብሮ ተኛ፡፡ ሠራተኞች ነበሩ፤ እየነቃሁ ስመጣ ግን በሙሉ ተበትነዋል፡፡ ምን አለ አሁን ተቀምጦ ሂሳብ ከመስራት፤ እንደ ባለትዳር የማታስተዳድረው ድርጅቱን?… በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ሽምግልናው ሰልችቶኛል፡፡  ቃል ተጠብቆ፣ ይህን ያሉኝን አላደርግም ብሎ አይሆንም፡፡ ቂም አንድ ቀን እስኪያስተምራት መጠበቅ ነው፡፡

ፍቺ ከጠየቅህ በኋላ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ያልቀረብክበት ምክንያት ምንድን ነው?

ይህን ህጻን ልጅም ይመልሰዋል፡፡ በውክልና፣ እራሴን ሆኖ ሚከራከር ጠበቃ ጉዳዩን ሰጥቻለሁ፡፡ እኔ አልናገርም። ዳኛዋን እንደ እርሷዋ በእንባ ለመብላት ነው እንዴ? ሳልናገር ተቀምጬ፣ ዳኛዋን ትክክለኛ ፍትህ እንዳትሰጥ አላደርጋትም። ለፍትህ መዛባት ሲሉ፣ የማይደረግ ነገር የለም።  ናፈቅኳት እንዴ?… ይህ የምትለውን ስታጣ ግራ ገብቷት ነው፡፡

ሰኔ 26 ለተያዘው ቀጠሮስ ትቀርባለህ?

እንዳልኩሽ ነው፡፡ ግን ጠበቃዬ በህመም ወይም በሌላ ነገር ከቀረ፣ እኔ ሄጄ በፅሁፍ የምጠየቀውን ልመልስ እችላለሁ፡፡ የከበደኝን “ጠበቃዬን ላማክርና እርሱ ይመልስላችኋል” ልል እችላለሁ፡፡ እኔ በፅሁፍ ይመለስ ወይም አይመለስ አላነበብኩም፡፡

LEAVE A REPLY