ይህ ምስሉን የምትመለከቱት ወጣት ማንደፍሮ አካልነው ይባላል። ከአጠገቡ የሚታየው ደግሞ ከሰባት ዓመታት በፊት በማዕከላዊ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ወደቃሊቲ እስር ቤት ከተላከ በሁዋላ ቀለሙን የቀየረው አካሉ እየተቀረፈ ይንጠባጠብ ስለነበር በወቅቱ “ታሪክና ሕዝብ ይፍረድ” ብለን በድብቅ ያስወጣነው የትግል አሻራው ነው።
ወጣት ማንደፍሮ በላስታ ላሊበላ የመኢአድ አባልና በ2002 ዓ.ም የክልል ም/ቤት ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን በአከባቢው የሥርዓቱ ካድሬዎች ብዙ እንግልቶች ካደረሱበት በሁዋላ እርሱን ጨምሮ ወጣት መሰለ ድንቁ ከአይና ቡግና፣ ወጣት ቴዎድሮስ አያሌው ከወልዲያ፣ አቶ ሲሳይ ብርሌ ከኡርጌሳ እና ሌሎችም ለዴሞክራሲ የሞገቱ የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ወደማዕከላዊ ምርመራ መጥተዋል።
በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የማይገመት የግፍ መአትም ወርዶባቸዋል።
በወቅቱ እኔ በሌሊት ወደ ግፈኛው ምርመራ ክፍል ስወሰድ እነዚህ ወጣቶች ፊታቸው በደም ተሸፍኖና ሰውነታቸው ቆሳስሎ በሸክም ሲመለሱ አይ ነበር። ሲናገሩት ይቀላል፤ ሲኖሩት ይከብዳል!
ከማንደፍሮ ጋር ዛሬ የተገናኘነው በወቅቱ በደረሰበት ድብደባ በተደጋጋሚ ራሱን እየሳተ፣ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎቹን መቆጣጠር ባለመቻሉና በመሳሰሉት የህክምና እርዳታ ፈልጎ ወደመዲናችን በመምጣቱ ነበር።
ይሁንና ለህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ከጠበቀው በላይ ሆኖ በመገኘቱ ከነህመሙ ወደትውልድ አከባቢው እያዘነ ለመመለስ ተገዷል። እሱና ሌሎች ወንድም እህቶቻችን የከፈሉት ዋጋ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ቢሆንም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ አጋርነታችንን ማሳየቱም የህሊና እርካታ ይሰጣልና ከዚህ ወንድሜ ጎን እንድትቆሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ። የስልክ ቁጥሩ:- (0922- 629000) ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!