/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተገኝተው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የጀመረቻቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ 7.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከሀገር ውስጥ ብቻ ከ400 ቢሊየን ብር በላይ ተበድረዋል ብለዋል፡፡ከዚህም መብራት ሀይል 240 ቢሊየን ብር የሀገር ውስ ብድር እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩ አስታውቀዋል።ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ሀብት ፈሶበት አንዳችም ውጤት ያላስመዘገበው የስኳር ፕሮጀክቶች በሚቀጥለው ዓመት የስራ ተቋራጮች መስራት የማይችሉትን ለሌሎች እንዲያስተላልፉ፤ የሚችሉትን ደግሞ በፍጥነት እንዲፈፅሙ ይደረጋል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሚቀጥለው 2011ዓ.ም የመንግስት በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር ሆኖ ፀድቋል።ከዚህም 55 በመቶ ካፒታል እንዲሁም 45 በመቶ ደግሞ መደበኛ በጀት በመሆን ተደልድሏል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ_ኢትዮጵያዊያን ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚልከውን ገንዘብ በባንክ በኩል በመላክ የመንግስትን የለውጥ እንቅስቃሴ ደግፉ፤ ዲያስፖራው ማኪያቶ ከሚጠጡበት አንድ ዶላር በመለገስ በገጠር አካባቢ ያለውን ህዝብ ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ድጋፍ እንዲያደርግል።” ሲሉ ጠይቀዋል። ይህን የሚያንቀሳቅስ ቦርድ ሽራፊ ሳንቲም ሳትባክን ለታሰበለት አላማ እንደሚያውልም ቃል ገብተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነገም ልዩ ስብሰባ እንደሚኖረው አፈጉባኤ ሙፈሪያት ካሚል ተናግረዋል።አጀንዳው በግልፅ አልታወቀም።አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከም/ቤቱ አባላት መካከል ያለመከሰስ መብታቸዉ የሚነሳ እንዳለ ጠቁመዋል።