ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከአዲስ አበባ፣ ጋዜጠኛ ጺዮን ግርማ ከVOA እና የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ ከኢሳት #Getachew Shiferaw; #Tsion Girma Tadesse, #Wendmagegne Gashu
እነዚህ ሦስት ጋዜጠኞች ላለፉት ጥቂት አመታት በአገዛዝ ሥርዓቱ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተለይም በእስር ቤቶች ስቃይ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ዜጎችን እያነጋገሩ እና የተፈጸመባቸውን ግፍ በግሩም ዘገባዎቻቸው እያቀረቡ የግፉአኑ ድምጽ እንዲሰማ ትልቅ ጥረት አድርገዋል፤ ዛሬም እያደረጉ ይገኛሉ።
በተለይም ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት እየተዘዋወረ በግፍ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን የችሎት ውሎ በሚገርም ሪፖርት አቀራረብ ብቃቱ እየከተበ ለታሪክ ተመዝግቦ እንዲቆይ ከማድረጉም በላይ ብዙ ሰዎች የታሳሪዎቹን የክስ ሂደት እንዲከታተሉ እና የአገሪቱም የፍትህ ሥርዓት ምን ያህል የዘቀጠ መሆኑን እንዲገነዘቡ በማስረጃዎች እያስደገፈ ለማሳየት ጥረት አድርጓል። ጌታቸው በዚህም ሳያበቃ በየእስር ቤቱ እየተዘዋወረ እስረኞችን በማነጋገር እና የሚገኙበትን የእስር ሁኔታም በመዘገብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን አለም እንዲያውቀውም አድርጓል። ይህ ትንታግ የሆነ ጋዜጠኛ ዛሬ በመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀር የምንሰማቸውን የሰቆቃ አይነቶች እሱ ቀድሞ በመዘገብ የሥርዓቱን ገበና ገልጦ አሳይቷል። በግፍ ሲሰቃዩ ለቆዩትም እስረኞች ድምጽ ሆኗል። ከፍ ያለ ዋጋም ከፍሎበታል።
ጺዮን ግርማ እጅግ ተወዳጅ ጋዜጠኛ እንድትሆን ካደረጓት ሥራዎቿ በዋናነት የሚጠቀሰው ባላፊቱ ሦስት አመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ እና ሌሎች ክልሎች የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት ሰጥታ በመከታተል ያቀረበቻቸው ድንቅ ዘገባዎቿ በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው። የጺዮንን ሪፖርት እጅግ ሚዛናዊ የሚያደርገው ዘገባዎቿ በሥፍራ፣ በሰዎች ማንነት ወይም በክስተቶቹ አይነት የተገደበ አለመሆኑ ነው። የመብት ጥሰቱ የትም ይፈጸም፣ በማንም ላይ ይፈጸም፣ ማንም ይፈጽመው ጺዮን ትዘግበዋለች። በዘገባዋም የግራ ቀኙን ሃሳብ ታስደምጣለች። በእያንዳንዱ ጉዳይ ዙሪያ ተበዳዮችን፣ የአይን እማኞችን፣ የመንግስት ባለሥልጣናትን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የተለያዩ ባለሙያዎችን ታሳትፋለች። ከሰሩ አይቀር እንዲህ ነው።
ወንድማገኝ ጋሹ እረዘም ላሉ አመታት በሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ በመሆን በኢሰመጉ ውስጥ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ስላካበተ በኢሳት ውስጥ ለሚያቀርበው ዝግጅት ትልቅ እገዛ አድርጎለታል። ብዙዎቻችን ዛሬ ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ስናተኩር እና የለት የለቱን ስናይ ወንድማገኝ ግን ወደ ኋላ እየተመለሰ ሥርዓቱ ባለፉት 27 አመታት የፈጸማቸውን የመብት ጥሰቶች እንድናስታውስ እና ፍትህ ላላገኙትም ወገኖች ፍትህ እንዲያገኙ ይጮሃል።
ዛሬ እነዚህን ሰዎች ለማመስግን የወደድኩት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ብሶት እና በተለይም ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጆሮ ዳባ ልበስ ባሉበት፣ የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሕግና በነፍጥ አፋቸው እንዲለጎም ተደርጎ የመጮህ አቅም አጥተው እነሱም ብሶተኞች በሆኑበት ወቅት፣ ነጻ ሚዲያዎች እንዲጠፉ በተደረገበት ወቅት መብታቸው ለተጣሰባቸው ሰዎች ድምጽ ሆነው ስለቆዩ ነው። ዛሬማ ችግሩ ባይቀረፍም የግፉአንን ድምጽ በማሰማት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ያዝልቅላቸው እንጂ የሚያክለን የለም በማለት ግንባር ቀደም ሆነዋል። የእነሱን ጅማሮ ይበል እያልን እዚህ ያደረሱንንም እናመስግን ብዮ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ስማቸውን ያልጠቀስኩት የመብት ተሟጋችና የሕዝብ ድምጽ የሆኑ በርካታ ጋዜጠኞችም ምስጋና ይገባችዋል።