የጠ/ሚኒስር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝት እጅግ ስኬታማ ነበር ተባለ

የጠ/ሚኒስር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝት እጅግ ስኬታማ ነበር ተባለ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሁለት ቀናት የአስመራ ጉብኝት እጅግ ስኬታማና ታሪካዊ እንደነበረ ተገልጿል። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ዛሬ ጠዋት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጦርነት በይፋ መቆሙን የሚያበስር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል እንደገለጹት ሁለቱ መሪዎች ከደረሱባቸው ስምምነቶች መካከል፡_

 1) የጦርነት በይፋ መቆሙን፣

2) ሁለቱም ሀገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ትስስር መፍጠር፣

3) የትራንስፖርት፣ ንግድና ቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነትን መጀመርና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማደስ፣

4) በአልጀርስ ስምምነት መሰረት የድንበር ውሳኔውን መተግበርና

5) የአካባቢውን ሰላም፣ ልማትና ጸጥታ ለማስከበር ሀገራቱ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ነው ብለዋል።

 የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል ጨምረው እንደገለጹት፤ስምምነቱን እንዲሁም ተግባራዊነቱን የሚከታተል ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተመስርቷል።ብሔራዊ ኮሚቴውም በስሩ አምስት ንዑሳን ኮሚቴዎች አዋቅሮ የቪዛ ጉዳይ፣ የጦር ምርኮኞችና የእስረኞች ልውውጥ፣ የአየረ መንገድና ታሪፍ ማውጣትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በመነጋገር መፍትሔ እንደሚሰጥ ታውቋል።ወደብን በጋራ ማልማት ወይስ በኪራይ መጠቀም የሚለውን በመፈተሽ ውሳኔ ያሳልፋልም ተብሏል።

በኢትዮጵያና ኤርትና መካከል ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው መደበኛ ስልክ አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩን ኢትዮ_ቴሌኮም አስታውቋል።የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ አስመራ ቀጥታ መደበኛ በረራ እንደሚጀምር ተበስሯል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም  በማስመልከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በአዲስ አበባ መነጋገራቸው ተገልጿል።

  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ም/ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳም ኢትዮጵያ በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል።

LEAVE A REPLY