/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- አቶ በረከት ስምዖን ደብረ ማርቆስ ከተማ ገብቷል መባሉን ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ውለዋል። በረከትና ግብረ አበሮቹ ሲንቀሳቀሱባት ነበር የተባለች V8 መኪና በዝህብ ቁጥጥር ስር ውላ የተፈተሸች ሲሆን ካሜራዎች፣ላፕቶፕ፣ሲዲዎችና ሁለት የተለያዩ የመኪና ታርጋ ሰሌዳዎች መገኘቱን በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች ገልፀዋል።
ህዝቡ መኪነዋን ያቃጠላት ሲሆን በረከት ስምዖን አርፎበታል የተባለው ሆቴልም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል።በረከት ስምዖን በሆቴሉ ውስጥ ስለመኖሩ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ወደ አደባባይ የወጡት የከተማዋ ነዋሪዎች “ከህዝብ ለተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች ተላልፎ እንዲሰጥና ህግ ፊት እንዲቀርብ መጠየቃቸውም ተነግሯል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽፈራዉ አየለ አቶ በረከት ደብረማርቆስ ገብተዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ለአማራ ቲቪ ተናግረዋል። ሕዝቡ እንዲረጋጋም አደራ በማለት ተማፅነዋል።
አቶ በረከት ስምዖን አሁን የተፈጠረውን ለውጥ ለመቀልበስ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ሌት ተቀን እየዞረ ለውጡን ይደግፋሉ በሚባሉት በእነ አቶ ገዱ አዳርጋቸው ላይ እያሴረ እንደሚገኝ ሰሞኑን ሲገለፅ መቆየቱ ይታወሳል።