/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮ_ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 100 ቀናት አስመልክተው ትናንት በሰጡት ቃለ_ምልልስ የቀድሞው የደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በስራቸው ጣልቃ ይገቡባቸው እንደነበረና አሁንም ለሚካሄደው ለውጥ እንቅፋት እንደሆኑ በግልፅ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ ለክልሎች መሪ እንደሚሾም፣በሙስና ለተከሰሱ ሰዎች ከለላ እንደሚሰጥ፣ በአጠቃላይ ስራው ተንኮልና ሰው መንወንጀል ብቻ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አብዲ መሐመድ በክልሉ ህዝብ ላይ ለተፈፀሙ ስህተቶች የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ኃላፊነት እንደሚወስዱ በመጥቀስ፣የክልሉን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን አቶ አብዲ መሐመድ የኦብነግ መሪዎች ‘የይቅርታና የፍቅር መንገድን ተቀብለው’ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሱማሌ ክልል በነፍስ ማጥፋትና በአስገድዶ መድፈር ከታሰሩ የህግ ታራሚዎች በስተቀር ሁሉንም ታራሚዎች እየተፈቱ መሆኑን የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ እድሪስ እስማኤል ለኢቢሲ ዜና የተናገሩ ሲሆን ከተለቀቁት መካከልም 17 እስረኞች የኦብነግ አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል።