አዲስ አበባን በሚመለከት ሰሞኑን አዲስ ውዝግብ ተነስቷል። በመሆኑም “አዲስ አበባ፣ ከየት ወደየት?” በሚል ዶ/ር ሺመልስ ቦንሳ ከወራት በፊት የፃፉትን ታሪካዊ ትንታኔ እንድታነቡት በድጋሜ ለጥፈነዋል።
=============
“አዲስ አበባ፣ ከየት ወደየት?” /ዶ/ር ሺመልስ ቦንሳ/
“የድሮዋ በረራ (የአሁኗ አዲስ አበባ) የአምሃራ፤ ጉራጌ እና ጋፋት ክርስትና ተከታዮች ይኖሩባት የነበረች ከተማ ነች”
በመጀመሪያ
የዛሬ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ አመት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1878 ንጉሰነገስት ምንሊክ ወደ አርሲ ሰራዊታቸውን ይዘው ይዘምታሉ። ባልተቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እንጦጦ የነበረውን የመንግስት መቀመጫ ወደ አሁኗ አዲስ አበባ ያዛውራሉ። ለጤና ተመራጭ የሆነው ፍልውሃ ፊንፊን ይልበት የነበረው ቦታ ለከተማው መቀየር አንዱ ግብዐት ቢሆንም የአድዋ ድል፣ የመንግስቱ መረጋጋት፣ የእንጦጦ ቀዝቃዛነትና ባካባቢው የነበረው የማገዶ እንጨት እጥረት የአገሪቷን ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመቀየር ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነው አገልግለዋል። ንግስቲቷ የአገሪቷን መናገሻ አዲስ አበባ ብለው ሲሰይሟት ሌላ ፡ ማለትም ስድስተኛ፡ ምክንያት እንድንፈልግ እንድንመረምርም ያደርገናል፣ ታሪክ ።
በስም ወይም ስያሜ ውስጥ ምን አለ? አዲስና አበባ አዲስ አበባ የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፣ አዲስ እና አበባ። የቦታውን ልምላሜና ውበት ከሚወክለው አበባ ከሚለው ስያሜ ይልቅ እንደገና መጀመርን፣ መታደስን፣ መነሳትን የሚያሳየው አዲስ የሚለው ቃል የተለቀ ትርጉም የተሸከመ ስም ይመስላል። ባንድ በኩል ስያሜው የውጭ ወራሪ ጠላትን በማሸነፍ ከመጣው መረጋጋትና እርግጠኝነት በተጨማሪ ስለወደፊቱ የነበረውን ብሩህ ተስፋን፣ ወደፊት ማደግን መመንደግን፣ በአለም ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አግኝቶ መከበርን ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ ወደሁዋላ ተመልሶ ማስታወስን፣ የጠፋን መመለስን ፣ የፈረሰ መገንባትን፣ እንደገና መታደስን ያሳያል። እስቲ በሁለተኛው ትርጉም ላይ በማተኮር ወደሁዋላ ተመልሰን የከተማዋን ታሪክ መረጃዎቹ በሚሉት መሰረት እንመርምር።
ከተማና ታሪክ፣ ከበራራ እስከ አዲስ አበባ
የከተሜነት ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊነቱን ለመረዳት በትንሹም ቢሆን የአገሪቷን ታሪክ ማንበብ ከተቻለም የከተሜነት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ የከተሞች ፍርስራሾችን {ለምሳሌም የሃን፣ አዱሊስን ፣ ቆሃይቶን}፣ ወይንም እስካሁን ያልጠፉትን ፣ ህይወት ያለባቸውን እነአክሱምን፣ ሃረርን፣ ጎንደርን መመልከት ይበቃል። በስነህንጻ፣ በስነጽሁፍ፣ በስነመንግስትና በኪነጥበብ አክሱም የደረሰችበትን የስልጣኔ ከፍታ የተረዳው ማኒ የተባለው ፐርሻዊ ጸሓፊ አክሱማዊት ኢትዮጵያን ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በአራተኛው ክፍለዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዷ ናት ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሃረርና ጎንደርም የከተማነት ዝናቸው በብዙ ቦታ የናኘ መሆኑ ሰፊው ታሪካቸው ቆመው የሚታዩትም የስነሕንጻ ቅሪቶችም ማረጋገጫዎች ናቸው።
ይህንን ስንመለከት የአሁኗ አዲስ አበባ የዚህ ጥንታዊና ጥልቅ የከተማ ስልጣኔ ወራሽ እንጂ
ጀማሪ እንዳይደለች እንረዳለን ማለት ነው። እስቲ ስለአዲስ አበባ ትንሽም ቢሆን ታሪክን ወደሁዋላ እንበል። የኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳናትም፣ ሆነ የውጭ ሀገር ጸሐፍት የሚያረጋግጡት አሁን ሸዋ ተብሎ የሚጠራውና የአገሪቱ መናገሻ አዲስ አበባ የሚገኝበት አካባቢ ከዛሬ 700 አመት በፊት ማለትም የሰለሞናዊው መንግስት ከተመሰረተበት ከ13ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የአገሪቱ ቁልፍ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚና፣ የባህል ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደነበረ ነው። በጊዜው የነበረው ማዕከላዊው መንግስት ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪ ቢሆንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተሞችን የመሰረተ ሲሆን ትልቁና በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ግን በራራ የተሰኘው ከተማ ነበር። ወረብ በራራ የምትገኝበት ቦታ ሲሆን በመሐከለኛው ዘመን ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት እና የነገስታቱ ቤተመንግስት የተሰራበት የነበረ በ16ኛው ክፍለዘመን ደግሞ ብዙ የውጭ ሀገሮችን የጎበኙት ፣ አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴም ከኢየሩሳሌም ጋር ሁሉ ያመሳሰሉት ሀብታም አካባቢ ነበር። ሺሃብ አድ ዲን {በቅጽል ስሙ አረብ ፋቂህ} የተባለው የመናዊ የፍቱህ አል ሃበሻ {የሃበሻመወረር} መጽሃፍ ጸሐፊ የግራኝ አህመድን ጦር በማጀብ ወረብንና በራራን ያየ ሲሆን ወረብን የሀበሾች ገነት ብሎ ጽፎላታል።
የበራራ ከተማ በአሁኗ አዲስ አበባ አካባቢ በተለይም እንጦጦ ላይ የተመሠረተ ሲሆን የኢትዮጵያ መዲናነት ታሪኩ የሚጀምረው በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት {እኤአ1380-1413} ሲሆን የሚያበቃውም በአህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋአዚ {በቅጽል ስሙ ግራኝ አህመድ} ጦር በሚቃጠልበት የአጼ ልብነ ድንግል {እኤአ 1508-1540} ዘመን ነው። እኤአ በ1450 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማው ፍራ ማዉሮ የተባለ ቬኒሲያዊ {ጣልያናዊ} ባዘጋጀው የዘመኑ ፈር ቀዳጅ በሆነው የአለም ካርታ ላይም ለመስፈር በቅቷል። ካርታው መሬት ላይ ባሉ መረጃዎች ተመስርቶ የተሰራ ሲሆን እነሱም አዉሮፓ ከነበሩ ኢትዮጵያዉያንና በተለያየ ወቅት በተለይም በአጼ ይስሀቅ {እኤአ 1414-1430} እና አጼ ዘርዓ ያዕቆብ {እኤአ 1434-1468} ዘመን ኢትዮጵያን ከጎበኙ አዉሮፓዉያን የተገኙ ነበሩ። ሰዓሊ ማዉሮም ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፣
“…{በካርታው ላይ የተመለከቱትን ስለአፍሪካ} ደቡባዊ ክፍሎች ማዉራቴ ለአንዳንዶች አዲስ ነገር ሊሆን ስለሚችል በጥንቶችም {በባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ስለማይታወቁ ከሰይቶ ጀምሮ ወደላይ ያለውን ጠቅላላ ስዕል ያገኘሁት ከቦታው ተወላጆች ነው ብዬ እመልሳለሁ። እነርሱም ቄሶች ሲሆኑ {በካርታው ላይ ያሉትን} ክፍለ ግዛቶች ፣ ከተሞች፣ ወንዞችና ተራሮችን ከነስማቸው በእጃቸው ለእኔ የሳሉልኝ እነርሱ ናቸው። ካርታው አሁን ድረስ ያሉ፣ እንዲሁም ስማቸው የማይታወቅ ቦታዎችን የጠቀሰ ሲሆን አቀማመጣቸውንም በመረጃ አስደግፎ ለማሳየት ሞክሯል። ለምሳሌም ከዘረዘራቸው ውስጥ የየረር፣ የዝቋላ፣ የመናገሻና የወጨጫ ተራሮች፣ የዱከምና አዋሽ ወንዞች፣ በወጨጫ ተራራ አካባቢ የሚገኙ የቤተመንግስት ፍርስራሾች፣ ይገኙባቸዋል።”
ከማዉሮ ካርታ በተጨማሪም በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያዉያንና የውጭ ሰዎች ስለበራራና አካባቢው ብዙ መረጃዎችን ትተውልን አልፈዋል። አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል አሌሳንድሮ ዞርዚ የተባለ የቬኒስ ጣልያናዊ {15ተኛዉና 16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ የመናዊው ሺሃብ አድ ዲን {16ተኛው ክፍለዘመን} ፣ እና አዉሮፓ የነበሩ የኢትዮጵያ መነኮሳት ፡ አባ ዞርጊ፣ አባ ሩፋኤል፣ አባ ቶማስና አባ እንጦንዮስ {15ተኛዉና 16ተኛዉ ክፍለዘመን} ይገኙበታል። እኤአ በ1529 ሽምብራ ኩሬ {በደብረዘይት ወይም ቢሾፍቱና ሞጆ መሃል ያለ ቦታ} በተደረገ ጦርነት ንጉስ ልብነ ድንግል መሸነፉና ወደሰሜን ማፈግፈጉ ወረብንና የአገሪቱ መዲናን በራራን ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን እኤአ በ1530 ቦታዎቹ በግራኝ አህመድ ጦር ለመያዝ ከተማዋም ለመቃጠል በቅተዋል። እንደሺሃብ አድ ዲን ትረካ ከሆነ የግራኝ ሰራዊት በአስር ቀናት ውስጥ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ {የአሁኗ ግንጪ} ተነስቶ በራራ በመድረስ አጭር ቆይታ አድርጓል፣ ከበራራም ሆኖ ግራኝ የተወሰኑ ወታደሮቹን የስድስት ቀን የእግር መንገድ ወደሚፈጀው ደብረ ሊባኖስ ልኮ እንዳቃጠለ ይዘረዝራል። የተቃጠለው የኢትዮጵያ መዲና የነበረው በራራ ከተማ የሚገኝበትን የወረብ ግዛት እንዲያስተዳድር ሙጃሂድ የተባለውን ታማኙን መሾሙንም ይጽፋል።
ከዚህ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ስለበራራ የሚዘግብ ምንም የጽሁፍ መረጃ አልተገኘም። በ19ተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ግን የጥንቱን በራራ ታሪክ የሚያስታዉሱ ግኝቶች መታየት ይጀምራሉ። እኤአ በ1881 በንጉስ ምኒልክ የሚመራው የሸዋ ፣ እኤአ ከ1889 በሁዋላም የኢትዮጵያ መንግስት መዲናውን እንጦጦ ላይ ያደርጋል። እንደዘመኑ ትርክት ከሆነ {ድርሳነ ራጉኤል ላይ እንደተጻፈው} የንጉስ ምንሊክ እንጦጦ ላይ መከተም ከስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ታሪካዊ ትርጉም ነበረዉ፣ እሱም ታሪክ የዘከረዉን የጥንቱን የአጼ ዳዊት ከተማን እንደገና መገንባት፣ ወደአገሪቱ መዲናነትም መመለስ ነበር። ንግርቱም ታሪካዊ መሰረት እንደነበረው የሚያመላክቱ መረጃዎች በእንጦጦ {የጥንቱ በራራ ክፍል} የተገኙ ሲሆን ይህንንም በጊዜው ሀገሪቷን የጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች {ዲፕሎማቶች፣ ተጓዦችና ወታደራዊ ባለሙያዎች} ዘግበዉታል። ቻርለስ ማይክል፣ ሲልቬይን ቪኘራስ፣ ሻለቃ ፓወል ኮተን፣ አልበርት ግሌይቸን፣ እና ቸዛሬ ኔራዚኒ፣ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሁሉም በቦታው የነበረዉን ጥንታዊ የመከላከያ ቅጽሩን ተመልክተው
ስለጥንካሬዉና ግዙፍነቱ አድናቆታቸውን በጽሁፍ አፍረዋል። እንጦጦ ላይ የፔንታገን ቅርጽ {አምስት ጫፎች ያሉት} ያለው በዙርያውም 12 መመልከቻ ማማዎች የያዘ እንደመከላከ የሚያገለግል ቤተመንግስትና ግንብ የተገኘ ሲሆን ርዝመቱም 520 ሜትር ከፍታውም እስከ 5 ሜትር እንደሚደርስ ታውቋል። የስነህንጻና አርኪዎሎጂ ባለሙያዎች {ለምሳሌም ዴቪድ ፊሊፕሰን፣ ማይክል ዎከርና ማርክ ቪጋኖ እንደተነተኑት ግንቡ እኤአ ከ1550 በፊት የነበረዉን የፖርቱጋልና ስፔን የመከላከያ ግንብ አሰራር ዘዴ የተከተል ሲመስል ቢያንስ የ400 አመት ወይም በላይ ዕድሜ ያለዉና በ16ተኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አጋማሽ ምናልባትም በአጼ ልብነ ድንግል የተገነባ እንደሚሆን ነው።
የአዲስ አበባ ምንነት
እንግዲህ በጥንቷ በራራና በአሁኗ አዲስ አበባ መሐከል ታሪካዊ ግኑኝነት እንዳለ ካየን አሁን ደግሞ የሁለቱን ከተሞች በተለይም የአዲስ አበባን መልክ ወይንም ዋና መገለጫ ባህርይ ምን እንደሚመስል እንመልከት። የኢትዮጵያ ከተሞችና መዲናዎች {ለምሳሌም አክሱም፣ ጎንደር} ልክ እንደአገሪቷ ህብረብሄራዊ ገጽታ የነበራቸው ሲሆን በውስጣቸው የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የተለያየ እምነትና ባህል ተከታይ የሆኑና፣ በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዉያን እንዲሁም የዉጭ ሀገር ተወላጆች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ነበሩ። ጥንታዊቷ አክሱም በሶስት ቋንቋ {ግዕዝ፣ግሪክ፣ ሳባ} የምትጽፍ፣ ከሶስት ቋንቋ በላይ የምትናገር፣ ከኢትዮጵያዉያን በተጨማሪ ግብጻዉያን፣ የመረዌ {ሱዳን} ሰዎች፣ የመናዉያን፣ የምስራቅ ሜድትራንያን {ፊንቄያዉያን፣ ግሪኮች፣ የጥንት ሶሪያዉያን} ተወላጆች እንዲሁም ህንዶችና ቻይናዉያን የኖሩባት ወይም ደግሞ የሰሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች። ጎንደርም ብትሆን የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ እምነት ተከታዮች አብረው ኖረው {ተለያይተው የሰፈሩ ቢሆንም} ፣ በስራና በህይወት ተስተጋብረው መልኳንና ታሪኳን ውብና ዥንጉርጉር አድርገው የቀረጿት ከተማ እንደነበረች ታሪኳ ይመሰክራል። ሀረርም ከአራቱ የእስልምና ቅዱሳን ቦታዎች አንዷ ስትሆን በብዝሀነቷ እና በእምነት ማዕከልነቷ የምትታወቅ፣ በመቻቻል ታሪኳ የተመሰገነች በዚህም እንደ ታዋቂዉ የፈረንሳይ ገጣሚ አርተር ራምቦ እና እንግሊዛዊዉ ሪቻርድ በርተን ያሉ የውጭ ሰዎችን ለመማረክ የቻለች ምስራቃዊ እንቁ ነበረች፣ ነች።
የበራራም ታሪክ ቢሆን በብዝሃነት ያሸበረቀ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። በከተማዉም ሆነ በዙሪያው ባሉ እንደ ወረብ ባሉ ግዛቶች ይኖር የነበረው ማህበረሰብ በብዛት ከአምሃራ፣ ከጉራጌ እና ከጋፋት {ሶስቱም ተቀራራቢ ቋንቋዎችን ይናገራሉ } የተዉጣጣ እና የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችና እምነት ተከታዮች ይገኙ እንደነበረ ይታሰባል። ለዚህም ምክንያቱ ከተማው ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከምስራቅ ኢትዮጵያ<s