ያልተቀነሰው የቀን ጅብ፣ የማነ አስፋው /ጌታቸው ሺፈራው/

ያልተቀነሰው የቀን ጅብ፣ የማነ አስፋው /ጌታቸው ሺፈራው/

ኢቲቪ የቀን 7 ሰዓት ዜና ላይ ስለ ሸዋሮቢት እስረኞች ሰቆቃ አንድ ዘገባ ሰርቷል። ከእስረኞች አስተያየት በኋላ የሸዋሮቢት ኃላፊ እስረኞች ልብሳቸውን እያወለቁ ስላሳዩት ሰቆቃ መልስ መስጠት ጀመረ። የማነ አስፋው ነው።

የማነ “አንድም እስረኛ ጉዳት ደርሶበት ተመትቶ አያውቅም” እያለ ስለመገረፋቸው ልብሳቸውን አውልቀው ያሳዩት የእስረኞቹን ሰቆቃ ለማስተባባል ሲሞክር ሸዋሮቢት እስር ቤት ጉልበቱን በሚስማር የተመታው አግባው ሰጠኝ ከጎኔ ነበር። ወዲያውኑ ደግሞ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ደውዬ ጠየኩት።

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ከደረሰበት ድብደባ በላይ የማነ “እገድልሃለሁ” ብሎ እንደዛተበት አጫወተኝ። “ማን እንደነገረው አላውቅም፣ ብቻ ገብቶ ማስረሻ የምትባለው በሕይወትህ ፍረድ፣ እገድልሃለሁ ብሎኛል!” ይላል ማስረሻ!

ወደናትናኤል ያለምዘውድ ደውዬ የማነ ሸዋሮቢት እስረኛ አይደበደብም ማለቱን ስነግረው “የማነ ራሱ ደብድቦኛል” አለኝ። ናቲ ስለ ሸዋሮቢት የስቃይ እስር ቤት አንድ አሳዛኝ ፅሁፍ ፅፎ ነበር። በወቅቱ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ አትመነዋል።

ይህን ፅሁፍ የፃፈው ከሸዋሮቢት ወደ ቃሊቲ ከተመለሰ በኋላ ነው። እንደገና ቅጣት ብለው ወደ ሸዋሮቢት መለሱት። ሸዋሮቢት የቅጣት እስር ቤት ስለሆነ “ቅጣት” ተደርጎ ይላካል። ይህ ፅሁፍ ኢሳት ላይ ሲተረክ ያየው የማነ ናትናአል ከቃሊቲ ሲመለስ ጠብቆ ደብድቦታል። “ከእሱ በፊት የነበረው አቡ የሚያስደበድብህ በሌላ ሰው ነው። የማነ ግን ቆሞ ነው የሚያስደበድብህ፣ ራሱ የማነ ደብድቦኛል” አለኝ ናትናኤል።

አንጋው ተገኘም የማነን ያውቀዋል። በድብደባ ተሰባብረው በወደቁበት ቤት ከፍቶ ገብቶ “ምን ችግር አለ?” ይላል የማነ። ቆሞ ነውኮ ያስደበደባቸው። አንጋውም “እንዴት ተሰባብረን ወድቀን እያየህ፣ የምንጠጣው ውሃ አጥተን እያየህ ምን ችግር አለ ትላለህ? አንድ ምሳሌ ልንገርህ፣ መፅሃፍ በሳንሱር በሚገባበት ማዕከላዊ ያገኘሁት መፅፋህ ላይ ያነበብኩት ነው። ደርግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ማረሚያ ቤት እኩል በጀት ይጠይቁታል። እኩል 500 ሺህ። መንግስቱ ገመቹ ይህን ለመንግስቱ ሀይለማርያም ይነግረዋል። መንግስቱ ሀይለማርያም ግን ለማረሚያ ቤቱ 500 ሺህ ጨምርለት ይለዋል። አማካሪው መንግስቱ ገመቹ ለምን ብሎ ሲጠይቀው «ሞኝ አትሁን! እኔና አንተ ከዚህ ስንወጣ ዩኒቨርሲቲ አንገባም። የምንገባው እስር ቤት ነው” አለው። እናንተ እንዴት ከእነ መንግስቱ እንኳ አትማሩም?” ይለዋል አንጋው ተገኘ።

የሸዋ ሮቢቱ የማነ ተናደደ! ብዙ ዛተ። ስለ ድርጅቱ ትህነግም ተናገረ። “ጓደኞችህ ልክ ልኩን ነገርከው ሊሉህ ይችላሉ። እኔ ግን ለድርጅቴ መትረየስ አልፈራም። ግንባሬን እሰጣለሁ! እኔ ድርጅቱን የተቀላቀልኩት በ17 አመቴ ነው፣ ለድርጅቴ ስል አልፈራም፣ እንተያያለን!” ብሎ ዝቶ ብዙ ነገር ተናግሮት እንደሄደ አንጋውም አጫውቶኛል። እስረኛ ሰቅሎ መደብደብን፣ በሚስማር መምታትን፣ ጨለማ ቤት ማሰርን ለትህነግ፣ ለድርጅቱ እንደመስራት ያየዋል። የማነ!

ሸዋሮቢት እስር ቤት የሰው ልጅ ተሰቅሎ ተገርፎበታል። በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰው ስቃይ ለመስማትም ይቀፋል። የማነ በዛሬው ዘገባ የተሟላ ህክምና አለ ብሎ ሲከራከር ነበር። ሸዋሮቢት እስር ቤት የታመመ እስረኛ እንደ እድለኛ ይታያል። በተለይም ህመሙ ወደ አዲስ አበባ የሚያስመጣው ከሆነ። ሸዋሮቢት ህክምና ስለሌለ የባሰበት ወደ አዲስ አበባ ይላካል። በልመና!

እነ የማነ ግን ያለውን ህክምናም ይከለክላሉ። እነ አግባው እግራቸውን በሚስማር ተመትተው የቲታኖስ መርፌ እንዳይወጉ የከለከለው የማነ ነው። በእነ የማነ ትዕዛዝ የኤች አይ ቪ መድሃኒት የተቀሙ እስረኞች እንዳሉም ሰምቻለሁ።

የማነ በኢቲቪ ቀርቦ እስረኞች የተናገሩትን ሰቆቃ ማስተባበሉ አይገርምም። የሚያሳዝነው የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተቀይረዋል ተብሎ እየተወራ የሸዋሮቢቱ የቀን ጅብ አሁንም በእስረኞች ቁስል ላይ በርበሬ እየነሰነሰ መቀጠሉ ነው። ለወሬ ብቻ እነ ዶክተር አብይ በእስረኞች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙት የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ከስልጣን ተነሱ ይሉናል። እውነታው ግን እነ የማነ አሉ። አልተነሱም። እነ የማነ ሳይነሱ፣ አሁንም የገረፏቸውን እስረኞችን ሰቆቃ እያስተባበሉ ስለ ሰብአዊ መብት መከበር ማውራት አይቻልም። በእስር ቤት የሚፈፀመውን ሰቆቃ ለመቀነስም ቁርጠኝነቱ የለም ማለት ነው፣ እነ የማነ እያሉ? እስረኞቹ በኢቲቪ እንደተናገሩት ጨለማ ቤቶቹ ኢቲቪ ይመጣል ሲባል ነው መብራት የተዘረጋባቸው፣ ፍራሽ የገባላቸው። እነዚህ የቀን ጅቦች እያሉ መደመር የሚሉት ስላቅ ነው። መጀመል፣ መንጋጋት ካልሆነ በስተቀር!

LEAVE A REPLY