/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስምንት ሰዎችን የቦርድ አመራሮች አድርጎ ሾሟል። ማህበራዊ ሒሶችን በማቅረብ የሚታወቀው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም የቦርድ አባል ሆኖ እንዲያገለግል ተሰይሟል።
ም/ቤቱ አቶ ካሳሁን ጎፌ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ ወ/ሮ ጀሚላ ሽምቢሩ፣ ወይዘሮ አበበች ሸከቻ፣ አቶ በቀለ ሙለታ፣ አቶ ዮናስ አስናቀ፣ አቶ ወንድወሰን አንዷለም፣ አቶ ተካ አባዲና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የድርጅቱ የቦርድ አባል በመሆን ተመርጠዋል።
በሌላ በኩል ም/ቤቱ በዛሬ አስቸኳይ ስብሰባው የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተለያዩ የወንጀል ድርጊት ለተሳተፉ ላላቸው ሰዎች ምህረት ለመስጠት የቀረበውን “የይቅርታና የምህረት” ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁ ታውቋል።
አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት በተዘረዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በህግ የሚፈለጉም ሆነ ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ያለና የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ወይም የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ምህረት የሚሰጥ ይሆናል።ከዚህ ባለፈ ግን አዋጁ ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ ምህረትን የማይሰጥ መሆኑን የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ተናግረዋል።
በአዋጁ መሰረትም ምህረት ያገኙ ሰዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ካፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ማድረግ ይኖርባቸዋል።በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ያላደረገ ግለሰብ ወይም አካል መንግስት በልዩ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር የምህረቱ ተጠቃሚ እንደማይሆን ተገልጿል።
አዋጁ የፖለቲካ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት መንግስት በወንጀል ተጠያቂ ሊያደርገን ይችላል በሚል ስጋት፥ ከሃገር ወጥተው በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያስችላልም ተብሏል።