ሃምሌ 2018 ዓ ም
ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት አሰቃቂና አሳፋሪ ሁኔታ ላይ ያስቀመጣት ነገር ብዙ ቢሆንም ሁላችንም የዚህ አስከፊ ሁኔታ መቀጠል ባለድርሻ መሆናችንን መዘንጋቱ ወደ መፍትሄው አይወስደንም። ነፍሳቸውን በገነት ያኑረውና ኩሩው ኢትዮጵያዊ አሰፋ ጫቦ ከሃያ ዓመታት በፊት ጦቢያ ላይ “ድርሻ ድርሻችንን እናንሳ” ብለው ራሳችንን እንድንመረምር ምክረውን ነበር። ጥሩውን ነገር ሁሉ አደረግሁ ለማለት የምንሽቀዳደመውን ያህል ኢትዮጵያን በመሰናክሏ የነበረንን ድርሻ አምነን ለለውጡ ስንነሳ ነው ድሉ ዋስትና የሚኖረው።
አሁን ህወሃቶች ለግል ስልጣንና ለዘረፋ ሲሉ ያጠፏትን ኢትዮጵያን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለመመለስ ቅን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚጥሩበት ጊዜ ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታት የተቀጣጠለው ህዝባዊ ትግል ስልጣንን ሙጭጭ ብለው የያዙ ዘረኞችንና ዘራፊዎችን እንዳይነሱ አድርጎ ያደቀቃቸው ቢሆንም ያፈረሱትን ለመገንባት፣ በአዲስ ራዕይም ለመጓዝ መረባረብ ያስፈልጋል። በአገዛዙ ውስጥ የለውጥ ኃይል ሆኖ የተነሳው የነ ዶክተር አብይ ቡድን እስካሁን የሄደበት መንገድ የሚያስደንቅ ብዙ ጊዜና መስዋዕት የሚያስጠይቀን የነበረውን ድል በአጭር ጊዜ ያጎናፀፈን ነው። ይህንን ድል ለማስጠበቅና የበለጠም ወደፊት ለመሄድ ቅን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጭፍን ድጋፍና ከጭፍን ተቃውሞ ወጥቶ የእንቅስቃሴው አካል መሆን ይኖርበታል።
በሰው ልጅ ላይ ይደርሳል ያልተባለ ግፍ የተፈፀመባቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከእስር ተፈተዋል። የቀሩትም እንዲፈቱና ዳግም ማንም አምባገነን እየተነሳ ዜጎችን የሚያሰቃይበት ሁኔታ እንዳይኖር የማድረግ መሰረቱንም መጣል አለብን።
የአገርን ዳር ድንበር መጠበቅ የሚኖርበት ሰራዊት የአምባገነኖች ስልጣን ጠባቂ ሆኖ ሰላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ይገድል የነበረው አብቅቶ ህዝቡንና ህገመንግስቱን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት እየተነገረው ቢሆንም ብሄራዊ ተዋፆውና አላማው ተስተካክሎ አገር የሚኮራበት ሰራዊት እንዲሆን ብዙ መሰራት አለበት።
በሁለት አምባገነኖች እብሪት በመቶ ሺህ ዜጎች የተቀጠፉበትና ኢትዮጵያንና ኤርትራን መቀመቅ ውስጥ የከተተው ጦርነት እንዲያበቃ አብይ አህመድ የወሰዱት ደፋርና የጀግና እርምጃ ሁላችንን ያስደመመ፣ ህዝቡን ከልቡ ያስደሰተ መሆኑን መዘርዘር ተገቢ አይመስለኝም። የህዝቡን እድል በመዳፉ ያደረገ አምባገነን እየተነሳ ለእልቂት እንዲዳርግ ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ እድል ሊሰጠው አይገባም። ከኤርትራ ጋር የሚኖረን ግንኙነትትና አንድነት በፍቅርና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ መሆን ቢኖርበትም፤ ከሆይሆይታ ወጥተን ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅምን፣ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ትውልድ እጣ ሁሉ ባገናዘበ መሰረት ላይ የተጣለ ፍትሃዊ ግንኙነት እንዲኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአፅንዖት ሊከታተለውና ሊተገብረው ይገባል። በሻዕብያ የፖለቲካ ሞቅታ የተገፋፉ አንዳንድ ኤርትራውያን ያሳዩት እብሪትና የነመለስ “የዐይናችሁ ቀለም አላማረንም” ፋሺስታዊ እርምጃ ምን ዋጋ እንዳስከፈለን ትውልድ አይዘነጋውም።
ዛሬ ኤርትራ ካላት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ሃብት ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ነበራቸው። የዐይናቸውን ቀለም የጠሉት የወያኔ ባለስልጣናት ንብረታቸውን አልጠሉትም። ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው አከፋፍለው ያም አልበቃ ብሏቸው ኢትዮጵያን በሙሉ ሲዘርፉ በቃችሁ ተብለዋል። ያልተጠቀመው ኤርትራዊና ኢትዮጵያዊ ውድ ዋጋ እንደከፈለው ሁሉ የወያኔ ዘራፊዎች ትናንት ያላዩት የትግራይ ህዝብ እንዲያድናቸው ጉያው ውስጥ ሊሸጎጡ ተሯሩጠዋል። የት ታውቁኝ ነበር እንደሚላቸው እርግጠኛ ነን።
ለአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ንፁህ ኢትዮጵያውያንን ያፈነው፣ ያረደው፣ ደብዛ ያጠፋው፣ ጥፍር የነቀለው፣ የሰለበው፣ ህሊናን ለመስበር ግብረሰዶም እስከመፈፀም የዘለቀው ጨካኙ የደህንነት መስሪያ ቤት ድርጊቱ ተጋልጦ አገራዊ ተልዕኮ ብቻ እንዲኖረው እየተነገረ ነው። የዚህ ተቋም ዋና ተዋንያን ተጠያቂ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትውልድ ዳግም ወደዚያ ሁኔታ እንዳይመለስ ድርጊቶቹ ተመዝግበው፣ መሳርያዎቹ ባሉበት ተቀምጠው መማርያ ሊሆኑን ይገባል። ናዚዎች የፈፀሙት ሁሉ ለጀርመኖች ሃፍረት ቢሆንም ለዜጎቻቸውና ለዓለም መማርያ እንዲሆኑ አስችለዋልና እኛም በአሳፋሪ ታሪካችን መማር ይኖርብናል።
ህወሃት የሃይማኖት ተቋማትን አራክሶ፣ ታሪካችንን አጠልሽቶ የሙስሊሙንና የኦርቶዶክሱን ሃይማኖት በከሃዲ ካድሬዎች ሞልቶ አዋርዶናል። በግፍ የታሰሩና የተሰቃዩ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ዛሬ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ከህዝባቸው ክብር ተችሯቸው ወደመንፈሳዊ ስራቸው ተመልሰዋል። የጥንታዊቷን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶችበማስወገድ በካድሬና በጎጠኞች አስሞልችቶ ከፋፍሎን የዓለም መዘባበቻ አድርጎን የቆየው ታሪክ ሊያበቃ ጫፍ ላይ ነን። ዶክተር አብይ እየተጫወቱት ያለው ሚና ቀላል አይደለም። ያለሁላችን ድጋፍ በሚፈለገው ፍጥነት መሄድ አይቻላቸውምና ምዕመኑ ብቻ ሳይሆን በአገሩና በታሪኩ የሚኮራ ዜጋ ሁሉ መተባበር አለበት።
ከድንቁርና የተጣባው ህወሃት ኢትዮጵያ በሌለ ሃብቷ ያስተማረቻቸውን ምሁራን በግፍ በማባረር ትውልድን ገድሏል። ዛሬ እነዛ ምሁራን በዓለም ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ውለታ ያልዋለላቸውን የውጭ አገር ህዝብ ሲያስተምሩ ልባቸው እየደማ ነው።
ከሰላሳ በላይ ዩኒቨርስቲ ከፈትሁ ብሎ ባዶ ህንፃ በካድሬውና በቂ እውቀት በሌላቸው ሰዎች ሞልቶ ያመረተው ትውልድ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የማያውቅ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባረሩ የቀድሞ ዩኒቨርስቲ መምህራንን ይቅርታ ጠይቀን እንመልሳቸዋለን ያሉት በጎ ጅምር ስርዓተ ትምህርቱንም በመቀየር ትውልድን ለመገንባት መሰረት እንደሚጣል ተስፋ ብቻ ሳይሆን ጥረትም እናድርግት።
በለውጥ ኃይሉ የተያዘው ትናንት ገዥዎቻችን ያፈራረሱትን ተቋማት መመለስ፣ አዳዲስ ተስፋ የሚሰጡ ጅምሮችን ማቀድና መሰረት መጣል፣ ሰላምና እርቅ እንዲሰፍን ሁኔታውን ማመቻቸት ቢሆንም ይህ ቡድን አቅጣጫ ከማሳየት የዘለለ አቅም አይኖረውም። አቅሙና ጉልበቱ ያለው ህዝቡ መሃል ነው። ህዝቡ፣ ተቃዋሚዎች፣ አክቲቢስቶች ወዘተ. አሁን አንጋጥጠን ዛሬስ አብይ ምን ሊያደርግ ነው? ብለን በመጠበቅ ወይንም ይሄን ይሄን ለምን አያደርግም? የሚል የነጭናጫ ልጅ ዓይነት ጥያቄ ላይ የተጠመድን ይመስላል። ባንዲራ ይዞ መደገፉ፣ በተገቢ መልክ መንቀፉ ባልከፋ! የራስን ድርሻ ለነቲም ለማ አስረክቦ ተመልካች የመሆን አባዜ (አብይ ሲንድሮም) አየሩን መበከሉን ካላስተዋልን አዳጋ ላይ ነን። የጫጉላው ሽርሽር ያብቃና እነዶክተር አብይ የራሳቸውን ድርሻ ይወጡ እኛ ደግሞ የበኩላችንን።
ህዝቡ ተዘናግቶ እያለ የምር ሥራቸውን በመስራት ላይ ያሉት መቀሌ የመሸጉና በየቦታው የተኙ የትናንት አገዛዝ ናፋቂዎች (sleeping cells) እንዲሁም በአጋጣሚው መጠቀም የሚፈልጉ ዘረኛ ፅንፈኞች እየተመጋገቡ የትግሉን ፍሬ ለመንጠቅና ሰላማችንን ለመንሳት እየተሯሯጡ ናቸው። ትኩረት ከነፈግናቸው አደገኛ የሆኑትን ያህል በአንድነት ቆመን ከተነሳንባቸው የጥዋት ጤዛ ናቸው። ስለዚህም ሁለት ተግባራዊ ሥራ እንዳለብን አንዘንጋ። የለውጡን ኃይል በተግባር መደገፍና አደናቃፊዎችን ነቅተን መጠበቅ። ይህንን በሚገባ ከተወጣን አገራችን ተስፋ አላት።