አቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ 31ኛ ከንቲባ እና ውዝግቡ

አቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ 31ኛ ከንቲባ እና ውዝግቡ

አቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ 31ኛ ከንቲባ ሆነው መሾማቸውን ተክትሎ ሰፊ ውዝግብ አስነስቷል። ቢቢሲ አማርኛ አቶ ታከለን አነጋግሮ የመከተለውን አጠናክሯል።

____

”አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ናት” ከንቲባ ታከለ ኡማ

አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በንቲ (ኢንጂነር) የድሃውን ማህረሰብ ፍላጎት ለሟሟላት ተግተው እንደሚሰሩ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በሥራ ዘመናቸው የከተማዋ ነዋሪ ዋነኛ ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ጨምሮ፣ የውሃ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በመካከለኛ እና ዝቀተኛ ገቢ ለሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለማዳረስ ሀሳብ መሰነቃቸውን አክለው ገልጸዋል።

የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆኑት አቶ ታከለ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ስላልሆኑ በምክትል ከንቲባነት የተሾሙ ቢሆንም የከንቲባውን ሥራ እንደሚሰሩ ተገልጿል።

ሹመታቸው ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆነውም ቆይተዋል። ሹመታቸውን የሚቃወሙ ወገኖች ከሚከራከሩባቸው ምከንያቶች መካከል፤ የከተማዋ ተወላጅ ስላልሆኑ ከተማዋን ለማስተዳደር የውክልና ጉድለት አለባቸው፣ ብሔር ዘመም አቋማቸው የበርካታ ብሔረሰቦች መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባን ካለ አድልዎ ለመምራት ያላቸው አቋም አጠራጣሪ ነው የሚሉት ይገኙበታል።

በሌላ በኩል ሹመታቸውን የሚደግፉ ሰዎች የሥራ አፈጻጸም ችሎታቸው እንጂ ብሔራቸው ከጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፣ ተሰናባቹን ከንቲባን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ለተከታታይ በርካታ ዓመታት ከተማዋን አስተዳድረዋል የኢንጂነር ታከለ ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይሆንም ሲሉ ይከራከራሉ።

በእነዚህ ሀሳቦች ላይ ያላቸውን ምላሽ የተጠየቁት አዲሱ ከንቲባ ታከለ ኡማ ለተሰነዘሩት የድጋፍ እና የነቀፌታ አስተያየቶች አክብሮት እንዳላቸው ገልፀዋል።

”አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ፣ የሁላችንም ከተማ ናት ብዬ አምናለሁ። ከኢትዮጵያዊነት አልፎም የአፍሪካዊነት መገለጫ ናት፤ ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫም ናትና። ይህ እምነቴ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮን ያደገ ነው” ብለዋል።

አዲሱ ከንቲባ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቁ መወለዳቸውና ማደጋቸው በከተማዎ ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል እና ሥነ-ልቦናን እንዲረዱት እንዳገዛቸው ተናግረዋል። ለወደፊቱ የከተማዋን ነዋሪዎች በእኩል ዐይን የማስተዳደር፤ በተለይ ደግሞ የድሃውን ማህበረሰብ ፍላጎት ከምንጊዜም በላይ ለማሟላት የተቻላቸውን እንደሚያደርጉም አክለዋል።

አቶ ታከለ እስከ ከነቲባ ሆነው እሰከ ተሾሙበት ጊዜ የኦሮሚያ የትረስንፖርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ከዚያ ቀደምም የተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በመላው ኦሮሚያ ተቀጣጥሎ ለነበረው ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለው የመንግሥት እቅድ ነበር። ዕቅዱ ለህዝብ ውይይት ሳይቀርብ የመንግሥት ሃላፊዎች በእቅዱ ላይ ተወያይተው ነበር።

አቶ ታከለም በኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን በተላለፈ ውይይት ላይ ስለ እቅዱ የሰጡት አስተያየት የብዙዎችን ቀልብ የያዘ ነበር። አቶ ታከለ በሰጡት አስተያየት ”የአንድ ከተማ ፍላጎት ሳይሆን ይህ የማንነት ጥያቄ ነው። አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የመገኙ ከተሞችን ሊያሳድግ የሚችል ዕቅድ ሲታሰብ የኦሮሞን ማንነት፣ ፖለቲካ፣ ባህል እና ታሪክ ሊጎዳ በማይችል መልኩ መሆን አለበት። አርሶ አደሮችን እየገፋ የሚያድግ ኦሮሚያም ሆነ አዲስ አበባ እኔ በግሌ አልፈልግም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።

አቶ ታከለም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማስተር ፕላኑን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት የበርካቶች የተቃውሞ ምክንያት መሆን የለበትም ብለዋል።

”በወቅቱ የሰጠሁት አስተያየት በተለየ መልኩ መተርጎም የለበትም፣ የስጋት ምንጭም መሆን የለበትም” ይላሉ። ”አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን የትኛውም ከተማ ደሃውን ህብረተሰብ መግፋት የለበትም።”

አሁንም ቢሆን ”ጥቂት ግለሰቦች የአርሶ አደሩ መሬት ላይ ባለጸጋ ሆነው አርሶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ልጅ ጥበቃ እና የጉልበት ሰራተኛ ሆኖ ማየት አልፈልግም። ይህ ደግሞ ኦሮሞን ብቻ የሚመለከት ብቻ ሳይሆን በከተማዋ እና በዙሪያዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሚመለከት ነው” ብለዋል አቶ ታከለ።

ከሳምንታት በፊት ከንቲባ ድሪባ ኩማን የተኩት ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ 32ኛው ከንቲባ ናቸው።

ታከለ ኡማ ማ ን ናቸ ው ?

አቶ ታከለ 1976 ዓ.ም በምዕራብ ኦሮሚያ አምቦ አቅራቢያ ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎሮ ሶሌ እና ቶኬ ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጉደር እና አምቦ ተከታትለዋል።

የ12ኛ ክፍል ማልቀቂያ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ በኋላ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመረቁ። በ2000 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ምህንድስና (ኢንቫሮመንታል ኢንጂነሪንግ) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

አቶ ታከለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ ነቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው። በተማሪነት ዘመናቸው በዶ/ር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ደጋፊ እንደነበሩ ይናገራሉ፤ በኋላም በ1999 ኦህዴድን ተቀላቅለዋል።

አቶ ታከለ የአዲስ አበባ ምክትል ከነቲባ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ፣ የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ እና የሆለታ ከተማ ከንቲባ ሆነው ማገልገላቸው ይጠቀሳሉ።

LEAVE A REPLY