/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በተለያዩ የክልልና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በተነሳ የእሳት ቃጠሎ በሰውና ነብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ። በወልዲያ፣ ፍኖተ ሰላምና አርባ ምንጭ ማረሚያ ቤቶ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱ እንዲሁም ከፍተኛ ግጭት መፈጠሩ ታውቋል።
በፍኖተ ሰላም ለተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ከትናንት በስትያ የሰጡት መግለጫ እንደሆነ የማረሚያ ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ረዳት ሳጅን ግርማ ሙሉጌታ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል። በእሳት አደጋው 26 የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች መውደማቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
በወልዲያ ማረሚያ ቤትም ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ እሳት መነሳቱንና ሙሉ በሙሉ የወንዶች ማደሪያ እንዲሁም የስልጠ ማዕከሉ መውደሙን ማረሚያ ቤቱ አስታውቋል።
የአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት በነሳው የእሳት ቃጠሎ እስር ቤቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።
በሌላ በኩል በቂሊንጦ እስር ቤትም ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ጩኸት እየተሰማ መሆኑንና የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ማ/ቤቱን መክበባቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የዓመፁ መነሻም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን የሰፀደቀውን “የይቅርታና ምህረት” አዋጅ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በቴሌቪዥን ማብራሪያ መስጠታቸውን ተከትሎ በይቅርታና ምህረት አዋጁ ያልተካተቱ እስረኞች ቅሬታ መፍጠራቸው መሆኑ ታውቋል።