ጥያቄው ተነስቷል!! አገር ገና በህዝባዊ ዓመጽ ስትናጥ በነበረበት ትላንትና፤ ያመጹ አቅጣጫ በቅጡ ባለየበት፤ በገዥና ተገዥዎች መሀል የነበረው የሀይል ሚዛን ከተመጣጣኝነት አልፎ ተገዥዎች አንጻራዊ የበላይነት ካሳዩበት ቅጽበት አንስቶ ተጠይቋል፤ አሁንም ባንዳንድ ወገኖች እየተጠየቀ ቀጥሏል።
ያኔ! ከዛሬ ሶስት ወራት በፊት ወያኔ መራሹ መንግስት በተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የተነሳ ተሽመድምዶ አመጹን መግታት አይደለም መቋቋም በተሳነው ወቅት የመጨረሻውን የመፍጨርጨር ሙከራ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” የህዝቡን አመጽ በጠመንጃ ሀይል ለማስቆም በዳዳበት ጊዜ፤ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለመተካትና ህዝባዊውን አመጽ ወደተሻለ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር የሚያስችል ተቋማዊ መደላድል ለማበጀት ፤ ወይም በተፈጠረው የስልጣን ክፍተት የተነሳ ሊከሰቱ የሚችሉ የህግና ስርዓት አልበኝነት አደጋዎችን ለመመከት ወይም በሰላም መደፍረስ የተነሳ የሚከሰት ሁከትን ለመቀነስና፤ አላስፈላጊ ግጭቶች የተነሳ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ፤ የዜጎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እክል እንዳይገጥማቸው፤ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ከመንግስት መፍረስ ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል የሚችል አቅም ያለው “የቀውጢ ጊዜ መንግስት” ወይም “የሽግግር ወይም ባለአደራ መንግስት” እንዲቋቋም መጠየቁ ተገቢና ወቅታዊም ነበር።
ሁለተኛ የተጀመረውን ህዝባዊ ማእበልና የለውጥ እንቅስቃሴ በትክክል መርቶ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካም ለማድረግ በሁሉም የለውጥ ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑ ሃይሎች ሙሉ እውቅናና ተቀባይነት የሚኖረው “የለውጥ አራማጅና አስፈጻሚ” ተቋም መፍጠር የግድ ነበር።
“የሽግግር ወይም የቀውጢ ጊዜ መንግስት” የምባለውን ጥያቄ ለማንሳት የግድ የሚሉ ሌሎች ሁኔታዎች ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜው የሀገራችን ተጭባጭ ሁኔታ አንጻር ስናየው ወቅቱ፦
የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ መራሹ መንግስት ላይ ያለው እምነት ሙሉ ለሙሉ ተሟጦ ያለቀበትና፡ ወያኔ መራሹም መንግስት በህግና በስርዓት ሳይሆን ማናቸውንም የህዝብ ጥያቄና እንቅስቃሴ በሀይልና በጉልበት ብቻ ለመጨፍለቅ እየተፍጨረጨረ የነበረበት፤
የተነሳው ህዝባዊ አመጽ በርካታ መሪዎች ያሉት የመሆኑን ያክል የተነሱት ጥያቄዎችና የማታገያ መፈክሮች የዚያኑ ያክል የተለያዩ መሆናቸው፤
በስልጣን ላይ የነበረውን መንግስት ተክቶ እንዲቋቋም ሲፈለግ የነበረው አሸጋጋሪ መንግስት ከላይ የገለጽኳቸውን ጥያቄዎች የመመለስ ወይም የማስተናገድ ተግዳሮቶች የተደቀኑበት መሆኑ፤
ከሁሉም በላይ ደግሞ የለውጥ ሃይሉ ወይም ህዝባዊ እንቅስቃሴው ውስጥ ተሳታፊ የሆነው ሃይል ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑትን የፖሊስና የጸጥታ አስከባሪ ተቋማትን የማደራጀቱና የመምራቱ ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪና መቋጫውም አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል ለውነትነት የቀረበ ግምት መኖሩ።
እንዲቋቋም ጥሪ የተደረገበት የቀውጢ ጊዜ መንግስት በስልጣን ላይ የነበረውን መንግስት የሚያካትት እንኳ ቢሆን፤ ባንድ በኩል የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በፍጹም ጠላትነት የፈረጀው ሃይል ተግዳሮትን መቋቋም እንዳለ ሆኖ ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ላይ ተመስርቶ ያንድን ፓርቲ የበላይነት ለማስከበር ሲያስር፤ሲገልና ሲቀጠቅጥ የነበረን የፖሊስና የደህንነት ሀይል የሽግግሩ መንግስት መሳሪያ ለማድረግ ቢያስፈልግ እንኳ ቀላል የማይባል የአደርጃጀት፤ የመዋቅርና የመርህ ለውጥ ለማድረግ የሚጠይቀው ጥረት በዋዛ የሚታይ አለመሆኑ ዋና ዋና ተጠቃሽ ተግዳሮቶች ነበሩት።
እንግዲህ እንዲህ ባለው ያለየለት አስጨናቂና አጠያያቂ ሁናቴዎች ላይ እያለን ነው ለአብዛኞቻችን ድንገቴና ያልተጠበቀ በሚመስል ረገድ ከራሱ ከአሸባሪው ወያኔ መንግስት ውስጥ “ቲም ለማ” የተባለ የለውጥ ሀይል ብቅ ያለውና በጭንቅ ተወጥሮ የነበረውን የለውጥ አየር ወደ
ብሩህ ተስፋ የተቀየረ ድባብ ውስጥ የከተተው። (ዶክተር ካሳ ከበደ ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ግልጽ እንዳደረጉት በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ ሃይል ድንገቴ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጅና አመች ሁኔታ እስኪፈጠር ጠብቆ የተነሳ መሆኑን አብራርተውልናል፤ ማን ያውቃል ወደፊት ሌላ ተጨማሪ መረጃም ከራሱ ከቡድኑ እንሰማ ይሆናል)
ይሁንና መቶ ቀናት የዘለለው በዶር አብይ የሚመራው የለውጥ ሀይል አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላ ደግሞ የወሰዳቸው እና እየወሰዳቸው ያላቸው እርምጃዎች በጥቅሉ ሁለት ዋና ዋና ባህሪዎች ታይተውበታል፤ የሽግግር መንግስትነትና – የለውጥ አራማጅነት።
አንደኛውና ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ከሆነው ጉዳይ ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ያለው “የሽግግር መንግስትነት” ባህሪው ነው። ጸጥታና ሰላም ማረጋጋትና የለውጡ ሂደት ሳይታወክ ወይም ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል የማድረግ ሀላፊነትን ተረክቦ ከማስኬድ አልፎ በርካታ የህዝባዊ እንቅስቃሴው ጥያቄዎችን የመለሰበት ፍጥነትና የተጠቀመበት ስልት “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ከሚባለው የወያኔ መራሹ ፖለቲካዊ መርህ በእጅጉ የራቀ ብቻ ሳይሆን ተጻራሪነቱ ያመዘነ መሆኑን አስመስክሯል። በዚህም “የመሸጋገሪያ ወይም ባላደራ ወይም ቀውጢ ጊዜ መንግስት” እንዲፈጽማቸው የሚጠበቁ ተግባራትን እያከናወነ ቀጥሏል።
በሁለተኛው የለውጥ አራማጅነት ሚናው በህዝባዊ ማእበሉ ለተነሱ ጥያቄዎች ጆሮውን በመስጠት ተጭባጭ እርምጃዎች እየወሰደ መቀጠሉ ነው፤ ባለፉት የመቶ ቀናት እድሜው ውስጥ በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ጸረ-ለውጥ አራማጆችን በማንሳትና ለውጡን ተፈጻሚ ለማድረግ ያግዛሉ የሚላቸውን ግለሰቦች ከመተካት ጎን ለጎን ለግጭትና ለጭቆና መሳሪያ ሆነው ሲያገለገሉ በነበሩ የህገመንግስት አንቀጾች፤ ህጎችና ያደረጃጀት ቅርጾች ላይ ጥናት የሚያደርጉ ኮሚሽኖችን በማቋቋም ስራ ተጠምዷል። የመንግስት ሚዲያዎች ላለፉት ፪፯ ዓመታት ከነበራቸው አሰራር ወጣ ብለው የህዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያጠናክሩ ዜናዎችን በነጻነት ማሰራጨት ጀምረዋል። ከተራ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ወደ መረጃ አቀባይነት ሚዲያ ሽግግር እያደረጉ ይገኛሉ።
በተጨማሪ የአብዛኛውን ህዝብ ይሁንታ ወይም ቅቡልነት ባጣው አነጋጋሪ ህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈሩ ከፋፋይና ዘረኛ አንቀጾችን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ እርምጃዎችን በመውሰድ የተጀመረው ህዝባዊ የለውጥ ሂደት እስከየት ድረስ ዘልቆ ሊሄድ እንደሚችል በተግባር አመላክቷል።
ባጠቃላይ በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ ሀይል ሀገሪቱን ወደ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር የሚያስችል ፅኑ ፍላጎትና አቅም ያለው ቡድን ከመሆኑ ባሻገር ቁርጠኝነቱን በተግባር እያስመሰከረ በመቀጠሉ ፤ በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፤ ባብላጫዎቹ ተቃራኒ ፖለቲካ ድርጅቶችንና ቡድኖች እምነት የተጣለበት መንግስታዊ ቡድን ሆኖ ለመውጣት ችሏል።(መንግስታዊ ቡድን ለማለት የተገፋሁት ድጋፉ ባጠቃላይ ኢህኣዴግ ለሚባለው ዘረኛና ፋሽስታዊ የዎሮበላ መንግስት የተሰጠ ሳይሆን ከኢህኣዴግ ውስጥ አይሎ ለወጣው የለውጥ ሃይል ወይም በሌላ አነጋገር ለዴሞክራሲያዊው አንጃ የተደርገ እውቅና ስለሆነ ብቻ ነው)
ስለዚህም ነው ለእውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ የማምጣት ተስፋ ሲባል፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊባል በሚችል የፖለቲካ፤ የብሄር፤ የሲቪልና የሚዲያ ተቋማት፤ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች በሙሉ ኢትዮጵያን ወደውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ነጻና ፍትሃዊ የዲሞክራሲ ተቋማትን በመገንባቱ ሂደት ላይ ከአብይ ቡድን ጋር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን እያረጋገጡ የሚገኙት።
ስለዚህ ከመቶ ቀናት በፊት ዋናና አንገብጋቢ የነበረው “የቀውጢ ጊዜ ወይም ያውጫጭኝ የሽግግር ጊዜ መንግስት” የማቋቋም አስፈላጊነት ጥያቄ ዋና የማታገያ መፈክርነቱ ያረጀበት በመሆኑ ከእሱ ይልቅ በምትኩ “ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ” ፤ የተጀመረውንም ለውጥ ከፈጻሜ ለማድረስ በሙሉ ሃላፊነት፤ በትጋትና ከሁሉም በላይ በባለቤትነት ስሜት ለመጨረሻው ዴሞክራሲያዊ ስረዓተ ማህበር ምስረታ ለማሸጋገር አስፈላጊ የሆኑትን የፍትህና የዲሞክራሲ ተቋማት ምስረታ ላይ ተግቶ የሚሰራ “ብሄራዊ የሽግግርና እርቅ ጉባኤ” እንዲቋቋም ግፊት ማድረግ የጊዜአችን ተመራጭ መፈክር ሊሆን የሚገባው።
የሽግግር ጉባኤው ስልጣንና ሃላፊነት በዶክተር አብይ የሚመራውንና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያገኘውን የለውጥ አሸጋግሪ መንግስት የሚተካ ሳይሆን ዋና ተልዕኮው ከላይ በገለጽኩት ዓላማ ላይ ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ የሀገሪቱ የሽግግር ጉዞ ሁለት በስልጣን ተገዳዳሪነት ባላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠሪነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሆኑ የሽግግር ተቋማት እንዲኖሩት ያስችላል።
ባንድ በኩል መንግስታዊ ስልጣኑን የያዘው የዶክተር አብይ ቡድን የውጭ ጉዳይን ጨምሮ ፤ የሃገሪቱን ደህንነት፤ ጸጥታና ሰላምን፤ የለት-ተለት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን አሁን በያዘው መንገድ እየመራ ሲቅጥል ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲቋቋም የሚጠየቀው ብሄራዊ ሸንጎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩ ተቋማትን ለማደራጀት የሚያስችሉ ጥናቶችን በማዘጋጀት የችግሮቹን ምንጭ ከስር መሰረቱ ለማድረቅ በመመካከርና በማጥናት በረቂቁ ላይ ህዝብን በማወያየትና ባብዛኛው ህዝብ ተቀባይነት ያገኙ ሃሳቦችን መሰረት ያደረገ ህግ እንዲወጣና ህጉንም ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ተቋማት እንዲመሰረቱ በሚያስችል ስራ ላይ ያተኩራል ማለት ነው።
ከሁሉ ሁሉ የሽግግር ጉባኤው ተዋጽዖ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያካትት በመሆኑና መነሻውና መዳረሻውም የተጀመረውን ለውጥ በሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ጎዳና ለፍጻሜ ማብቃት ስለሆነ ነጻ ሆኖ ከመደራጀቱ ባሻገር የለውጡም ባለቤት መሆኑ በህግ ሊረጋገጥ ይገባዋል።
ሁለቱ ተነጻጻሪ ተቋማት በመተባበርና በመደጋገፍ መስራት ደግሞ በተጀመረው የለውጥ ጎዳና እጅግ አብዝሃኛውን ኢትዮጵያዊና የህብረተሰብ ክፍል በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ስለሚያደርገውና በሂደቱም ሆነ ባፈጻጸሙ የዳር ተመልካች ስለማይኖር የማታ ማታ ሁሉም ህዝብ ከውጤቱ ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላል።
ስለሆነም ከሽግግር መንግስት ይልቅ “ብሔራዊ የሽግግር ጉባኤ ይቋቋም!!” የሚለው መፈክር ከወቅታዊነትም በላይ ለለውጡ መቀጠልና አስተማማኝ መሰረት ለመጣል እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ሊሆን ይገባል። እናንተስ ምን ትላላችሁ?