በዋሽንግተን ዲሲ ጉብኝትዎ ብገኝም፤ ነገር ግን ዕድል አግኝቼ ልጠይቅዎት ያልቻልኩትን ጥያቄ ምናልባት ፈጣሪ ፈቅዶ ለጆሮዎ ይደርስ ይሆናል ብዬ ይህን ለመፃፍ ተነሳሳው። ጥያቄዬ የሚያጠነጥነው በአመፅ ተፀንሶ፤ በፍቅር የተወለደው ይህ የለውጥ ጅማሬ እንዴት እናስቀጥል እንችል ይሆናል ከሚል ጭንቀት ውስጥ የወጣ ነው። ሁላችንም በእርስዎ ድንቅ አመራር፥ የፍቅርና ትህትና አካሄድ ተማርከን የዛሬው ደስታችን ላይ አተኩረን በታላቅ ደስታ ላይ ነን። ግን ይህ ምናልባት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቸኛውና የመጨረሻው ዕድል ሊሆን እንደሚችል እየተገነዘብን ከሚያንዣብበው አደጋ ለማምለጥ ለስህተት አንዳች ፈንታ እንዳይኖር ሁላችንም እርስዎን ጨምሮ ራሳችንን መፈተሽ የዕለት ዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል።
በመጀመሪያ ሀገር በቀል አዲሱን የኢትዮጵያ ርዕዮተ ዓለም ፅንሰ አሳብ ጀማሪ ስለሆኑ ፈጣሪን ስለ እርስዎ እናመሰግናለን። ይህ አዲሱ በይቅርታና በፍቅር የመደመር አካሄድ ኢትዮጵያን የሚያድን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን የሚታደግና ብሎም ለዓለም ተስፋ የሚሰጥ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ነው። ግን ይህ አሰተሳሰብ በፅንስ ደረጃ ያለ እንጂ ገና አላዳበርነውም። ይህንንም አስተሳሰብ የማዳበር ሃላፊነት የሁላችንም ሲሆን እርስዎም የመማርና የማስተማር ልብ ስላለዎት ይሳካልናል።
ሰው የጨነቀው የሚቀነሰው (negative) ከሌላው ጋር ሲደመር ውጤቱ ባዶ ይሆናል ብሎ ነው። እርስዎ ደግሞ የሚቀነሰው (negative) ጥቂት ከሆነ ከመቶ ሚሊዮን ጋር ሲወዳደር ምንም አይጎዳም ነው የሚሉት። የኔ ጥያቄ ለምን የማይደመር ነገርን በማባዛት ለመቀመር ዕድል እንሰጠዋለን ነው። ለቀመር ከበቃ ሁሉንም ነገር ዜሮ ለማግባት አንድ ዜሮ በማባዛት ስሌት ትበቃለች። ለቀመር ከበቃ (-1) ሁሉንም ነገር ኪሳራ ማድረግ በማባዛት ስሌት ትችላለች። ምክንያቱም እርስዎ የዘነጉት እኩይ ተግባር ያለው ሰው የሚመርጠው የማባዛት ቀመርን ነውና። ጥቂት መሆኑን ሲንቁና ችላ ሲሉ፤ በማባዛት ቀመር በመጠቀም አንዷ ዜሮ ወይም ትንሷ (-1) ጉድ እንዳያደርገን ይነቁ ዘንድ ይገባል። ስለዚህ እንደመር ማለት ብቻ ሳይሆን፥ የማይደመር ነገር በማባዛት አይቀመር የሚለው አስተሳሰብ ቦታ እንዲሰጠው ያስፈልጋል። ምክንያቱም መደመር እንዲሳካ ጠላት የማባዛትን ቀመር እንዳይጠቀም በእጅጉ መከላከል ይገባል።
ለውጡን ለመቀላቀል የሚያመነቱትና አንደመርም የሚሉትን ከማግለል ይልቅ ለማስረዳትና በፍቅር ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረት እጅግ መልካም ነው። መሆንም አለበት። ምክንያቱም ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ አንደመርም ብለው መከራከር የዲሞክራሲ መብታቸው ነው። ነገር ግን ለውጡን በአመፅ ለመቀልበስ ደም እስከማፍሰስ በመሄድ በማባዛት ቀመር የሚንቀሳቀሱትን ግን በዝምታ እና በቆይታ ማየት ከማስተዋል መጉደል እንዳይሆን መፍራት ደግሞ ያስፈልጋል። እነዚህን በማስረጃ ሕግ ፊት አቅርቦ እርምጃ መውሰድ ለመደመር እሴት ዘብ እንደመቆም ይቆጠራል። የማይደመር በማባዛት አይቀመር።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይባርካታልም።