መሓሪ ዮሃንስ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ ነው። በፌስቡክ ገጹ እሱ የሚያምነው ኢትዮጵያ እየፈራረሰች እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ ጨርሳ እንደጠፋች ነው። ህልም አይከለከል! እሱና መሰሎቹ አንቀጽ 39ን በትልቁ አጽፈውና ታቅፈው ፎቶ ተነስተዋል። የትግራይ ሪፑብሊክ በቅርቡ እውን ትሆናለች ይላል መሃሪ።
ግለሰብ ስለሆነ እስቲ ይሁን ብለህ ማለፍ ይቻላል። ችግሩ ግን መሓሪ ዮሃንስ በቅርቡ መቀሌ በተካሄደ ስብሰባ የትግራይ ወጣቶች በአዲስ መልክ ማደራጀት አለብን እያለ ሲጣራ አይተነዋል። ያደረገው ጥሪ እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ፊት ስለሆነ ደግሞ፣ መሓሪ ዮሃንስ የህወሓት ልዩ ድጋፍ እንዳለው አያጠራጥርም። ደብረጽዮን ራሱ “ተከባብረን መኖር ካልቻልን፣ መበታተን ነው” ካለ በኋላ ትግራይ በማን እጅ እንዳለች ግልጽ ሆኗል። መለስ ቢሞትም፣ ልጆቹ ደርሰውለታል።
ኢትዮጵያዊነት በደቡብ በኩል አብቦ፣ እንደነ ዶ/ር አቢይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ የመሰሉ ሀገራችን ከመበታተን አደጋ የታደጉ፣ እጅጉን ተስፋ የሆኑብን መሪዎች ሲያፈራ፣ “የኢትዮጵያ ማህፀን” (The Womb of Ethiopia) ተብላ በታሪክ ምሁራን የምትወደሰው ትግራይ ግን ኢትዮጵያን አፈራርሰው፣ ትግራይን ገንጥለው ለመጥፋት ያሰፈሰፉ ግለሰቦች ተቆጣጥረዋት ይገኛሉ።
እንዳው ያለፈው ሲገርመኝ፣ ዛሬ ደግሞ ግለሰቡ በጅጅጋ አከባቢ ሰላምና መረጋጋት ለማስከበር የተንቀሳቀሰውን የሀገራችን መከላከያ ኃይል “ሽንፈትን” ሲመኝለት አነበብኩኝ። ካበዱ ላይቀር እንዲህ ነው እንጂ።
በርግጥ የህወሃት መሪዎች – እና ካድሬዎች – የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ሆነው ኑረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ደግሞ በምንም መስፈርት የትግራይ ህዝብ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። አንተ የትግራይ ህዝብ አስብበት! በጠላት ተከበሃል! አዋርደውሃል! 27 አመት ሙሉ የዘረፉት አልበቃ ብሏቸው፣ በተአመር ከእጃቸው ያፈተለከችውን “ስልጣን” እንደለመዱት አንተን ቤዛ አርገው ለማስመለስ ከመቀሌ “ውፈር ተበገስ” ማዘፈን ጀምረዋል። ተዋቸው። እነሱ የጫሩት እሳት፣ እነሱ ይንደዱበት።
ክብር ለኢትዮጵያችን!