/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ በተፈጸመው ድርጊት የሰው ህይዎት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ። ከጅጅጋ ሌላም በድሬዳዋ ከተማ በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ የሰዎች ህይወት መጥፋቱ እንዳሳዘናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ሀላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠ/ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ባለፉት ሁለት ቀናት በተከሰተው ግጭት በርካታ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከሰባት በላይ ቤተክርስቲያናት በእሳት ተቃጥለዋል።ቀሳውስት ተገለዋል።የንግድ ድርጅቶች፣ባንኮች፣መኖሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል፤በእሳትም ተቃጥለዋል።
ዛሬ ከሰዓት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከገቡ በሗላ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በድሬዳዋ ከተማም ትናንት 10 ዛሬ ደግሞ 4 ሰዎች መገደላቸውን የድሬዳዋ ፖሊስ አስታውቋል።