ልማትና አንድነት -አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ልማትና አንድነት -አክሎግ ቢራራ (ዶር)

የኔ ትውልድ በህልሙ ያላሰበውን ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ እየለገሱት ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። በአብዛኛው “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት” አገር አቀፍ እሴቶች መሆናቸውን በማያሻማ ደረጃ የሚያስተጋቡ መሪዎች ማግኘታችን ተዓምር ነው። ከሁሉም በላይ አስደናቂና ተዓምራዊ ሆኖ ያገኘሁት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በህወሓት መራሹ ቡድን አማካይነትና መሰሪነት፤ ሆነ ተብሎ የአገራችን መለያና መታወቂያ የሆነውን የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስትያን ለሁለት የከፋፈለውን ሲኖድ አንድ ያደረጉት ዐብይ ታሪካዊ ስራ ሰርተዋል። ጠ/ሚንስትሩ ምን ውጤት አግኝተው ተመለሱ የሚለውን ጥያቄ የምመልሰው ማንም ለማድረግ ያልቻለውን ሁለቱን ሲኖዶች አንድ ማድረጋቸው ነው እላለሁ። በዚህም መሰረት፤ ፓትርያርኩን፤ ብጹሕ አባታችን መርቀሪዮስንና ሌሎችን የታወቁ አባቶቻችን አጅበውና ወደፊት አስቀምጠው ወደ ኢትዪጵያ ሲገቡ ደስታ ያልተሰማው ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም።

እውነትም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ፈጣሪያችን ይወዳቸዋል!! በፈተናቸው ወቅት ደርሶላቸዋል።

እርቅ፤ ሰላም፤ ፍቅር፤ አብሮነት፤ መደመር፤ የጋራ እድገት ከሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ዋናውና ወሳኙ፤ የእያንዳንዱን ሰው ሰብእነትና ክቡርነት ተቀብሎ፤ ለህሊና ተገዥነትና የመንፈሳዊ አንድነት መታገል ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥን እንደሚጠይቅ በተደጋጋሚ ለማሳሰብ ሞክሬአለሁ። ግን፤ ሁሉም ሰው ይለወጣል ማለት አይደለም። ትኩረታችን ራሱን ለመለወጥ ከወሰነው ላይ እንጅ “እኔ ብቻ አውቃለሁ” ከሚለው ላይ አይደለም።

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የታዘብኩት ክስተት ሌላው ቀርቶ ኃይማኖትና መንፈሳዊነት ሲነገድበት መቆየቱ ነው። ኃይማኖት እንደ ሸቀጥ ሲነገድበት አሉታዊ ውጤቱ የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን፤ የመንፈስ ውድመት ስር ይሰድና ሌብነትና ቅጥፈት፤ ጭካኔና ዘረኝነት እንደ ተራ ነገር መታየት ይጀምራሉ። ይህ ውድቀት ለሕግ የበላይነት፤ ለአብሮነት፤ ለዘላቂና ለፍትሃዊ ልማት ዋናውና ወሳኙ ተግዳሮት ይሆናል ማለት ነው። እስካሁን የታየው እድገት ቀፎ የሆነበት ምክንያት ለዚህ ነው። ጥራት የሌለው፤ ነገ የሚፈርስ ፎቅ ወይንም መንገድ ወይንም ሃዲድ ሰርቶ እድገት አለ ማለት ፋይዳቢስ ነው።

ራሳቸውን ያልቀየሩና በአብዛኛው ዘረኛ፤ ትእቢተኛና ቀመኛ የሆኑ የፖለቲካ ነጋዴዎች አንዱን ዘውግ ከሌላው ጋር በማናከስና በማጋጨት ዛሬ ኦሮሞውን፤ ነገ አኟኩን፤ ከነገ ወዲያ ዐማራውን እየለዩ ይገድላሉ፤ ያስገድላሉ፤ ከቀያቸው እንዲባረሩ ያደርጋሉ። ማንነትን የማይቀበል ዜጋ አለመኖሩ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ በማንነት ስም የሚካሄደው የፖለቲካ ንግድ ግን አሁንም አልጠፋም። በአንዳንድ ቦታዎች እየተባባሰ ሄዷል። ይህ የከፋፍለህ ግዛው ስልት በግልጽ የሚታይበት በደቡብ በኦሮሞና በሶማሌ ኢትዮጵያዊያን መካከል፤ በሰሜን በዐማራውና በትግራዩ ህዝብ መካከል ነው። ይህ ግጭት ለማንም አይጠቅምም፤ መቆም አለበት። አብሮነትና ፍትሃዊ እድገት አብረው አይሄዱም የምልበት መሰረታዊ ምክንያት ይኼው ነው። ማንነታችን እንዳለ ሆኖና ተከብሮ፤ መቅደም ያለበት ነጻነታችን፤ ሰብእነታችንና ሰብአዊ መብታችን ነው።

ከጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ጉብኝት ምን ተማርን?

ዋሽንግቶን ፖስት “Thousands of Ethiopians come out for ‘Abiy–mania,” July 29, 2018, የጉብኝቱን መንፈስ አግባብ ባለው አምድ አስቀምጦታል። “In the three months since his rise to power, the 41-year old politician has introduced sweeping changes in Ethiopia, lifting a state of emergency, brokering peace with neighboring Eritrea, and releasing hundreds of political prisoners. These dramatic steps towards liberalization have sparked “Abiy-mania” in the United States, which for decades, stood among the fiercest critics of the ruling party’ s autocratic regime.” ከJuly 27-29, 2018 በዋሽንግቶን ዙሪያ ከጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ፤ ከአቶ ለማ መገርሳና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የተካሄዱት ስብሰባዎችና ውይይቶች በአገራችን ታሪክ ታይተውና ተሰምተው አያውቁም። የለመድነው ታሪክ መቃወምን እንጅ መሪዎችን እልል እያልን መቀበልን አይደለም። ይህ እልልታ የሚያሳየው የለውጥ ጭላንጭል ስር እየሰደደ መሄዱን ነው።

በተለይ መረሳት የሌለበት የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ለመሰረታዊ ለውጥ ቆርጦ መነሳቱን ነው። ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ ስር እየሰደደ የሄደበትና በማንም ኃይል ወደማይቀየርበት ደረጃ የደረሰው በብዙ ሽህ የሚገመት ወጣት ትውልድ መስዋእት ሰለሆነና ዲያስፖራው ሳያቋርጥ ድምጹን ስላሰማ ጭምር ነው። ግን፤ ይህ ወጣት ትውልድ የሚጠይቃቸው መሰረታዊ የፖሊሲና መዋቅራዊ ለውጦች ገና ስላልተፈቱ፤ ወደፊት ስኬታማ እንደሚሆኑ አምናለሁ። ስኬታማ የሚሆኑት ሕዝባዊ እምቢተኛነቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥል ነው።

ጥንቃቄው ግን ሰርጎ ገቦችና አፍራሾች እድሉን ተጠቅመው ለውጡን እንዳይቀለብሱት ስልቶችን ከመንደፉ ላይ ነው።

የዲያስፖራው ሚና ወደፊትም ይቀጥላል ማለት ነው። ሆኖም፤ ከእልልታው ባሻገር ይህ በመሬት ላይ የሚታይ፤ ለምሳሌ የስራ አለመኖር፤ የኑሮ ውድነት፤ የድህነትና ሌላው ሃቅ መረሳት የለበትም። ጠ/ሚንስትሩ ብቻቸውን አይወጡትም።

ጉብኝቱንና እልልታውን በሚመለከት፤ አጠቃላይ ስእሉን ከመግለጽ በስተቀር በዚህ ሃተታ ብዙም ለመጻፍ አልችልም። ታሪክ የመዘገበው አስኳል ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን በአንድ አዳራሽ መሰብሰባችንና ትኩረታችን ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ላይ መሆኑ ነው። ጠ/ሚንስትሩና አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ተቀብለን፤ በአንድ አዳራሽ እንድንሰበሰብና ሃሳባችን እንድንገልጽ ማድረጋቸው አስደናቂና የተለዩ መሪዎች ያደርጋቸዋል።

የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በሶስትና በአራት ደቂቃዎች ጥያቄ ወይም አስተሳሰብ እንፈታለን ብለን ካሰብን ችግሩ የራሳችን እንጅ የጠ/ሚንስትሩ አይደለም። እሳቸውና ቡድናቸው ግልጽ የሆነ ራእይ፤ ተልእኮንና ፕሮግራም እንዳላቸው አይተናል። ሊሸምቱት የፈለጉትም አስኳል ስራ ግልጽ ነበር። ያልተዘጋጀነው እኛው ነን። ለምሳሌ፤ ሃያ ስድስት “ተቃዋሚ ፓርቲዎች” በተሰበሰቡበት መድረክ የዓላማ አንድነት ለማቅረብ አለመቻሉ ያሳየኝ ትምህርት ተቀናቃኝ የሚባለው ክፍል የራሱን ስራ

አለመስራቱንና ለምርጫዎች አለመዘጋጀቱን ነው። ከመቶ በላይ የሚቆጠር ተቀናቃኝ ወይንም ተቃዋሚ ፓርቲ ለማንኛውም ምርጫ ብቃትና ጥራት ያለው አቋም ለሕዝብ ለማቅረብ አይችሉም። የቤት ስራችን ብንሰራ መልካም ነው የምለው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ ከሶስትና ከአራት ተቀናቃኝ (ተቃዋሚ) ፓርቲ በላይ አያስፈልጋትም። ቢቻል ውህደት፤ ባይቻል ህብረት ወሳኝ የሚሆነው የፖለቲካው ምህዳር መርካቶ እንዳይሆን ነው።

ይህና ሌሎች ድክመቶች እንዳሉ ሆነው፤ ግን፤ የጠ/ሚንስትሩ ጉብኝነት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍ አድርጓቸዋል። እኔና ባለቤቴ እድለኞች ነን እላለሁ፤ ይኼን ታሪክ በአካል ማየታችን።

ስብሰባዎቹና ውይይቶቹ ለዲያስፖራው ከአገሩ መሪዎች ጋር እንዲተዋወቅና እንዲቀራረብ ሰፊ እድል ሰጥተዋል። በአብዛኛው ሲገመገም፤ ምንም እንኳን የሚታይና አስፈላጊ ያልሆነ “አሻጥር”፤ ውድድርና ልታይ-ባይነት ቢኖርም፤ ስብሰባዎቹ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስርጭት በሚወክል ደረጃ መንፈሳዊ አባቶችና እናቶች፤ ሴቶች፤ ወንዶች፤ ወጣቶች፤ ህጻናት፤ ምሁራንና ሊሎች በአንድ አዳራሽ ተሰብስበን ጉብኝቱን ደማቅ አድርገነዋል።

በዋሽንግቶንና በሎስ አንጅለስ የሕዝባዊ ስብሰባ ቀኖች “የኢትዮጵያ ቀን” ተብለው መሰየማቸው የዲያስፖራውን ጥንካሬና አስተዋፆ ያሳያል። ስለዚህ፤ የዐብይና ቡድኑ የአሜሪካ ጉብኝት በጣም የተሳካለት እንደነበር የአይን ምስክር ነኝ።

ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይና አቶ ለማ መገርሳ ለሕዝብ ያደረጓቸው ንግግሮች ያጠናከሩልኝ ጽንሰ ሃሳብ እኛ ከመተባበርና አብሮ አገራችን ከማሳደግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ነው። በየሄዱበት ያሳዩት ባህርይና ጸባይ ትህትና የተሞላበት ስለሆነ እኛም በበኩላችን ወደፊት ማድረግ የሚገባን መደማመጥና መከባበር፤ ልዩነቶችን በጨዋነት ማስተናገድ ይሆናል።

ጠ/ሚንስትሩና አቶ ለማ ለቀረቡ አስቸጋሪ ጥያቄዎች ሁሉንም የሚያስደስር መልስ ሰጥተዋል ለማለት ባልችልም (ሁሉንም ለማስደሰት አይቻልም)፤ ጥያቄዎችን አዳምጠዋል፤ ማስታወሻ እንደያዙ እገምታለሁ፤ መልሶችም ተሰጥተዋል። ለምሳሌ፤ በሚኒሶታ ከወቅቱ የአብሮነት ሂደት ጋር የማይጣጣሙ ጉዳዮች ተነስተዋል። ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። የአስተሳሰብ ለውጡ ገና ስር አልሰደደም።

ቁም ነገሩ ግን፤ ጠ/ሚንስትሩ ከአቋማቸውና ከእሴቶቻቸው ዝንፍ ሳይሉ የኦሮሞውን፤ የትግራዩን፤ የዐማራውንና የሌላውን ሕዝብ ጥያቄ አግባብ ባለውና በጨዋነት መልሰዋል። ከማንኛውም ክፍል ቢመጣ፤ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ለማንም ብሄር ወይም ኃይማኖት እንደማያዋጣ አስምረውበታል። የወደፊቱ የኢትዮጵያ ፈጣንና ፍትሃዊ እድገት ስኬታማነት መሰረት አብሮና ተባብሮ መስራት መሆኑን በተደጋጋሚ አቅርበዋል።

“ግንቡን እናፍርስ! ድልድዩን እንገንባ”! የሚለው ጥሪ ቀላል አይደለም። የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን አስተዋጾና ተሳትፎ ይጠይቃል። ሌላው፤ እኔ ከጠ/ሚንስትሩና ከአቶ ለማ የተማርኩት ቁም ነገር መሪዎች ኢትዮጵያንና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያስቀድሙ በዓለም ፊት ሁለቱም እሴቶቻችን ከፍ ይላሉ የሚል ነው።

“ታላቅ አገር ታላቅ መሪዎች ያስፈልጓታል” ያልኩበትም መሰረታዊ ምክንያት ይኼው ነው

LEAVE A REPLY