ለውጡና ሞልቃቆቹ! /ደረጀ ደስታ/

ለውጡና ሞልቃቆቹ! /ደረጀ ደስታ/

ባለፈው ጽሁፌ አዲስ አበባ ደርሼ አንዳንድ ነገር አጠቃቅሼ ተመልሼ መምጣቴን በመግለጽ ይቀጥላል ብዬ ነበር። እንቀጥል።

ያው እንግዲህ ሲባል እንደተኖረው ኑሮ ተወዷል። የብር ቁጥር ከመቶ እሚጀምር ይመስላል። አንዳንድ ቦታ አልፎ አልፎ አስር ብር ብልጭ ስትል አይቻለሁ። ባለ አምሳ ብርም ያየሁ መሰለኝ። አንዲቷ ብርማ ወረቅትነቷ ቀርቶ ሳንቲም ከሆነች ዓመታት አለፈ። የኔቢጤ ለማኝ ከመጣ መኪና ውስጥ የተጠራቀመውን ባለ አንዳንድ ብር ሳንቲምን እንደቆሎ ዘግኖ መስጠት የተለመደ ይመስላል። ምግብ በልቶ ምናምኒት ጠጥቶ በትንሹ አንድ አራት መቶ ብር መክፈል አያስደንቅም። አንድ ሁለት ሶስት ሁነው ከበሉ ከጠጡ አንድ ሺ ብር በላይ ሊከፍሉ ቢችሉ አለመገረም ነው። በተረፈ ምግባችን እንደዋጋችን ይወደዳል። ዋጋው ቢመርም ምግብነቱ ይጣፍጣል። እንደውጫገሩ እንጀራው ሆድ አይነፋም። የወጡ ሽታ ከልብስ ቀርቶ አይከረፋም። እንደ አረንቻታው ዘመን ኮካኮላው አሁንም ይጣፍጣል። ኮካ ሚሪንዳ ስፕራይትና ፋንታ በጣዕማቸው ትዝታ ኢትዮጵያዊነታቸውን አልቀየሩም። ኮካላውን እንደቢራ ደጋግሜ ስጠጣ ሰዎች ሳይታዘቡኝ አልቀሩም። በተቀረው ያየሁት መብል ቤት ሁሉ በሰው እንደተመላ ነው። ልጅነቴን ለማስታወስ ከተራው ሻሂ ቤትም ገብቼ ፉል በዳቦ በልቻለሁ። ከጎኑ እርጎ ጣል ተደርጎ ቃርያው ተከትፎ ባቄላው ተገንፎ ከፈላ ሻይ ጋር እኔነኝ ያለ ቁርስ ነው። እድሜ ለወዳጄ እሼው፣ በተመጋቢ ብዛት ከተጨናነቀው የመንደር ሉካንዳ ቤትም ገብቼ ከአግዳሚው ወንበር ተጠጋግቼ ብሩንዶውንም ሆነ የዳቢቱን ጥሬ ሥጋ በአዋዜ ጠቅሼ በአምቦውሃ እያወራረድኩ ትዝታን ተመግቤያለሁ። ከአፍ እሚቀልጠው ያገሬ ሥጋ እንኳን ተበልቶ ተጨምቆ ቢጠጣ ምን ይወጣዋል ያሰኛል።

ለነገሩ እንኳን የሥጋውን ሊመኙት የአትክልቱን ጭማቂ ዓይነት ማን ጠጥቶ ይጨርሰዋል? ማንጎው ፓፓዬው አቮካዶው አናናሱ ስፕሪሱ ለጉድ ነው። ሁሉ ነገር እናት ኢትዮጵያ ወይም ተፈጥሮ እንደወለደችው (ኦርጋኒክ) መሆኑ ደግሞ ውጭ አገር ለሚኖር ሰው አስገራሚ ነው። እዚህማ ዋጋውንስ ማን ይችለዋል? ኢትዮጵያም ቢሆን ሁሉም ሰው ይችለዋል ማለት አይደለም። መቸም ሰው ሳይበላ አያድርምና ግን በልቶ እሚያድረው ሁሉ ኦርጋኒክ መመገቡን ግን መካድ አይቻልም። አገር በልቶ ማድሩ ግን ያልተመለሰ ጥያቄ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም ከምግብ ቤት ወደ ደጅ ሲወጣ እሚታየው ትዕይንት ሌላ ነው።

እርግጥ ነው ከመንገድና ከመንደር እሚንገላወደው ወጣት እንደበዛው ሁሉ ሥራ ወዳድ የሆነው ወጣትም በዝቷል። ትጋታቸው ያስደንቃል። ከመጽሐፍና ሎተሪ አዟሪ አንስቶ መፋቂያና ልብስ መስቀያ ሳይቀር እስከሚይዙት ወጣቶቹ ድረስ ያለውን ነገር ሲያዩት ይገርማል። እማይሸጥ እማይዞር ነገር የለም። መጠኑ አምስትምት ስድስትም አምሳም መቶም ይሁን በወጣቶቹ እጅ ሸቀጥ ይዞራል። በየመንገዱ በቆሎ ከሚጠብሱት አንስቶ ድንች አንቸስችሰው “ቺፕስ” እስከሚሸጡት ድረስ ያለው የሥራ ትጋትና ጥረት ተስፋ ይሰጣል። ሠርቶ መብላት እሚፈልገው ሰው ብዛቱ በራሱ አገር ሊቀይር እሚችል ኃይል መሆኑን ማሰብ ይቻላል። ሰነፎችና ዋልፈሰሶች
ሳይሆኑ እነዚህ ራሳቸው ብቻ እንኳ በወጉ ቢያዙና ቢታገዙ አገር ምንኛ በተለወጠች ማለት ያስችላል። በለተይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመለወጥ ረገድ ይህን ታታሪ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል መያዝ በተለይ ኢንፎርማል ሴክተር የሆነው የኢኮኖሚው ኃይል ለዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማድረግ ይችላል እሚባለው ለዚህ ይመስለኛል። ችግሩ ግን ባለፈውም ሆኖ እንደታየው ወጣቶችን ለኢኮኖሚው እድገት ከማሰልፍ ፈንታ ለፖለቲካው ካድሬነት መልምሎ ከሙያና ከእጃቸው ይልቅ በምላሳቸው የቀለጠፉ በሰከንድ ብዙ ቃላትን እሚተፉ ወጣቶች አገር ላይ የተበተኑ ይመስል ኮሽ ባለ ቁጥር እየወጡ እሚንጣጡ መብዛታቸውንም ማስተዋል አያዳግትም።

ከአገራቸውና ከሁኔታዎች አቅም በላይ እሚቀናጡ ብርቱዎች ታግለው ባመጡት ለውጥ እሚቀብጡ ነጻነት ልቅነት የሚመስላቸው ያገኙትን ማውደም መሰባበር ትግል እሚመስላቸው ከአይዲዎሎጂ ወይም ከንባብና ውይይት ከተገኘ ዓላማና አመለካከት በፊት አመጽ እሚቀናቸው ዋልጌና ሞልቃቆችም የሉም ማለት አይቻልም። ማንም ሳያስተምራቸው ደርሶ ሊወቅሳቸው አይገባም እሚል የሐቅ ምላሽ ወዲያው ፈጥኖ አንቆ ባይዝ ኖሮ ትንሽ በጨንገርና በቁንጥጫ ልክ ቢያገቧቸው ያስብል ነበር። ዳሩ አገር ጥይት እንጂ ጨንገር ስለማታውቅ፣ ቁንጥጫም ስለተዘነጋት፣ እምታደርገው ጠፍቷት ከጤፍ ይልቅ የለብ ለብ አርበኛ እዚህም እዚያም እያፈራች መከራዋን እያየች ይመስላል። አገራችን ልጆቿን መግራትም ማስተማርም ካልቻለች ቱግ እያሉ በሚያፈጡ ልጆቿ ፣ ለውጡም መገልበጡ፣ ሰላሙም መናወጡ አይቀርም። አዲስ አበባን ሳያት ይህንንም አይቻለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀገራዊ ስሜትንና የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን ያጎለብታል በሚል 1ሺ እሚደርሱ ወጣቶችን ሰብሰበው መምከርና ትምህርታዊ ማብራሪያ መስጠታቸው ከዚህ አንጻር ሊታይ ይችላል። ከወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ባለፈ በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት ወራት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ 13 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ መባሉም ጥሩ ነገር ነው። ከችግሩ ግዝፈትና አሳሳቢነት አንጻር ግን ገና ይመስለኛል። የአገሪቱ አማካይ እድሜ 19 ከሆነ የወጣት አገር መሆናዋ ነው። ከዚህ ሁሉ ወጣት መካከል ስንቱ ሥራ ይዟል? ካልያዘስ እሚኖረው እሚተዳደረው በምንድነው? በልቶ ማደሩስ እንዴት ተቻለው? በዚህ ሁኔታ ይቀጥል ይሆን? ካልሆነስ ምንድነው መደረግ ያለበት? እሚለውን መነጋገር ተገቢ ይመስለኛል። ካለበለዚያ በሽተኞቹ ብሔርተኞች መርዘው የለቀቁት ከሆነ መጠቀሚያ መሆኑ አይቀርም። ፍሬ ነገሩ ሞልቃቆቹ ሊታዘንላቸው እንጂ ጥርስ ሊነከስባቸው እማይገባ፣ ባህሪያቸውም የጥንካሬያችን ሳይሆን የድክመታችን ማስረጃ መሆኑን ማወቃችን ላይ ነው። (ይቀጥላል)

LEAVE A REPLY